Friday, July 11, 2014

ትግል!!! ማንን? ለምን? ለማን? በማን? በምን? መቸና የት?

ትግል!!! ማንን? ለምን? ለማን? በማን? በምን? መቸና የት?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
struggle


ሀገራችን እድሜ ጠገብ፣ እድሜ እረጅም መሆኗን እናውቃለን፡፡ ከኖሕ ዘመን (ከጥፋት ውኃ) በኋላ ያለውን ብቻ እንኳን ብንይዝና ከመጀመሪያው ንጉሥ ከሰብታህ ጀምረን ብንቆጥር ከ4500 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የመንግሥት መልክ የያዘ የአሥተዳደር ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህች ሀገር ከዚህ ረጅም ታሪኳ ጋር እንደ ፀሐይ የሚያበራና አድማስ ተሻግሮ የሚሞቅ ብርቅዬ የነጻነት ታሪክ አላት፡፡ ሀገራችን ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ ይሄንን ዘውዷም ለመንጠቅ የሞከሩ እጅግ ከባባድ ፈተናዎችን አሳልፋለች፡፡ ፈተናው ያንን ያህል የከበደ ቢሆንም ያ ሕዝብ ከጠላቶቹ ከፈታኞቹ ከተገዳዳሪዎቹ ሁለንተናዊ አቅም የላቀ ጥንካሬ ብስለት ንቃት ወዘተ ስለነበረው ዘውዱን ሳያስነጥቅ ጠብቆ ለመቆየት ችሏል፡፡ ነገር ግን በመራር ጽናት ነጻነቱን ጠብቆ መቆየት ይቻል እንጅ ከጥንት ጀምሮ የነበረበት ፈተና ድምር ውጤት ይሁን ወይም ምድሪቱ አርጅታ አይታወቅም ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ ያለውን ትውልድ ስናይ ከትውልዱ የሚበዛው ምርኮኛና ምንደኛ የሆነ ትውልድ አፍርታ ቁጭ ብላለች፡፡
እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም አሳማኝ አይደለም ትንሽም እንኳን የሚመስል ምክንያት ሳይኖረው ለገዛ ማንነቱ፣ ታሪኩ፣ ሥልጣኔው ወዘተ. ከጠላቶቹ በላይ ጠላት የሆነን የትውልድ አካል እንደምን ባለ ቃል ሊገለጽ ይቻላል? ገና ሳስበው የሚያቅለሸልሸኝ ነገር ቢኖር ይህ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ጨርሶ መልካምና ክፉውን መለየት አይችልም፡፡ ገደልም ይሁን ምን ማንም ቢሆን ና እያሉ መርተው ቢከቱት ዓይኑን ጨፍኖ የሚወረወር ሆኗል፡፡ እናት አባቶቹ ተነግሮ ሊያልቅ በማይችል መሥዋዕትነት ጠብቀው ያቆዩትን ነጻነት (ነጻነት ስል እንድታስቡት የሚፈልገው የግዛት ነጻነትን ብቻ ሳይሆን ከግዛት እስከ ሥነ-ልቡናዊ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የነጻነት ዓይነቶችን ሁሉ ነው) እናም ይሄንን ነጻነቱን አውላላ ሜዳ ላይ ያለ ጠባቂ ቁጭ አድርጎ ለቀማኛ ለሌባ ለዘራፊ አጋልጦታል፡፡ ከፊሉን ሌቦች ወስደውታል ከፊሉን ደግሞ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ የሚወስድለት ቢያጣ አይሁድ በክርስቶስ መስቀል ላይ እንዳደረጉት ሁሉ የቆሻሻ ዓይነት እላዩ ላይ ሲደፋበት ሲደፋበት የቆሻሻው ክምር እንደ ተራራ ገዝፎ የነጻነት ዘውዱን ቀብሮታል፡፡ አውጥቶ የሚያከብረው ተቀዳጅቶ የሚያቀዳጅ እንደ እሌኒ ንግሥት ያለ አርበኛ ይፈልጋል፡፡
ከዚህ ትውልድ ራሱን ለጠላት ቀጥሮ የገዛ ማንነቱን በማውደም በማጥፋት ከተጠመደው አንሥቶ የእነኝህን ቅጥረኞች፣ ባንዶች የጥፋት ሥራ ልክና ቅጥ ባጣ እራስ ወዳድነት ፍርሐትና እንደ ዜጋ ሀገር የጣለችበትን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኝነትና ፍላጎት በማጣት እጁን አጣምሮ በዝምታ እስከ ሚመለከተው ድረስ ከትውልዱ የሚበዛው ቁጥር በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ጃርቶች የተሞላ ሆኗል፡፡ “ምድር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል ወይም እሳት አመድን ወለደ” ይሏቹሀል እንዲህ ነው፡፡ እነዚህ እንከኖቻችን አንባገነን ገዥዎቻችንን ለመፍጠር ከመመቸቱም በላይ ለግፍ አገዛዛቸውም ምቹ መደላድል ሆኗቸዋል፡፡ በተለይም ከሁለት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በዓይነቱ አዲስ እንግዳና የተለየ ፍላጎት ጥቅምና ዓላማ የያዘ ገዥ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለትውልዱ ከድጡ ወደማጡ ሆኖበት ወደከፋ የሰብእና ደረጃ ለመዝቀጥ ግዴታ ሆኖበታል፡፡ ከዚህ አገዛዝ አስቀድሞ በነበረው ትውልድ ዘንድ ይዘቱና ዓይነቱ ያነጋግር ካልሆነ በስተቀር የነበረው የሀገር ፍቅር ጨርሶ የሚያጠያይቅ አልነበረምና፡፡ አሁን ያለው ገዥ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ወዲህ ግን ሊያሠራኝ አይችልም ብሎ ያሰበውን ለዜጎች ለትውልዱ እንደ ጋሻና ጦር ሆኖ የማንነት ፈተናዎችን ለመቋቋም ለመከላከል ይረዳው የነበረውን የሀገር ፍቅር ስሜቱን በየሕሊናው ረሽኖ ከገደለበት ጊዜ ወዲህ ግን የዘቀጠ የሰብእና ደረጃ ላይ ለመገኘት ግዴታ ሆኖበታል፡፡
ገዝው ፓርቲ (ወያኔ) ይሄንን ካደረገ በኋላ የሥልጣን እስትንፋሱን ካራዘሙለትና እንዲያራዝሙለት ከተጠቀመባቸውና ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ዋነኞቹ ሕዝቡን በፍርሐት ቆፈን ጠፍንጎ ማሰርና አስቀድሞ ፋሽስት ጣሊያን እንዳደረገው ሁሉ በዘር በሃይማኖት በመደብ ከፋፍሎ እንዳይተማመን ማድረግ ነው፡፡ ለምን ቢባል በፍርሐት ገመድ የታሰረና የማይተማመን ኅብረተሰብ ተባብሮ ሊሠራራና ሊተባበር ቀርቶ አይናገርም መናገር ቀርቶ አያስብም አይመክርምና ነው፡፡ ጭራሽም እርስ በእርሱ ይፈራራል፡፡ ከመሀከሉ አንዱ ወይም ጥቂቶቹ ለማፈንገጥ ሲሞክሩም አስፈራሪው እሱው ራሱ ኅብረተሰቡ ወይም ከቅርቡ ያሉት የገዛ ወገኖቹ ይሆናሉ፡፡ ለታሪኩ ለነጻነቱ ለማንነቱ ለመለያው ቀናኢ አይሆንም፡፡ ስለዚህም እንደተፈለገ መርገጥ መጫወቻ መቀለጃ ማድረግ ይቻላል፡፡ በእርግጥ ገዥው ፓርቲ ከሚናገራቸውና በይፋ ሳይናገራቸውም ነገር ግን ለማስፈራራት በካድሬዎቹ በአባሎቹ በኩል ሆን ብሎ እንዲወሩና ወደ ሕዝቡ እንዲደርሱ ከሚያደርጋቸው ወሬዎች ሁሉ “አይ ለማስፈራራት እንጅ አያደርገውም” የሚባል አንድም ነገር የለውም፡፡
ምንም ዓይነት ድርጊት ቢሆን ምርጫው ላይ ያላካተተው የለም፡፡ ለሀገር ሳይሆን ለቡድኑ ሕልውና ሲባል ሰዎች መሞት ካለባቸው ሰዎቹ የማይተኩና ለሀገርም ዓይን ቢሆኑም እንኳ የትንኝ ነፍስ ያህል ዋጋ አይሰጣቸውም፡፡ ከዚህም አልፎ ሀገር መፍረስ ካለባት ያለ አንዳች ማመንታት ትፈራርሳለች፡፡ በሕገ መንግሥታቸው ሳይቀር ለህልውናቸው ዋስትና አድርገውት ይሄንን ቀርጸው እያስፈራሩን እንደኖሩትና እንዳሉት ሁሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ሊረዳውና ሊያውቀው ለራሱም ሊመልሰው የሚገባው ነገር ቢኖር፡-
1. እንዲህ ሰላሙንና ደኅንነቱን ከነሳው ዋስትና ካሳጣው ፍርሐትና ጭንቀት ነጻ ለመውጣትና የእፎይታ አየር ለመተንፈስ እንደ ሰው ኖሮ ለማለፍ የግድ ዋጋ መክፈል ያለበት መሆኑን፡፡
2. ከገዥው ፓርቲ ወጥመዶች ማለትም ከፍርሐት፣ እርስ በእርስ ከመጠራጠር፣ ካለመተማመን ወይም ከክፍፍል ሴራ ራሱን ማላቀቅ ናቸው፡፡
መቸም እንደ ሰው በተለይም እንደ ኢትዮጵያዊ ነጻነቱን አጥብቆ የማይሻ የማይፈልግ ይኖራል ብሎ ማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ትውልድ ያንን ነጻነት ማግኘት የሚችልበትን መንገድ ዐውቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ ላይ ግን እስከ አሁን አልተረዳም አልገባውምም፡፡ ለዚህም ዐቢዩን ሚና የተጫወተው የሥርዓቱ የማስፈራሪያ ቱልቱላ በሕዝቡ ሥነ-ልቡና ላይ በከፍተኛ ደረጃ መነፋቱ ነው፡፡ ማስፈራሪያው ገዥውን ፓርቲ ጨርሶ የሌለውን አቅም እንዳለው አድርጎ አሳምኖለታል፡፡ ከሕዝቡ አቅም አንጻር ቢገልጡና ቢያዩት ግን ባዶና አቅመቢስ ሸንበቆና ቀሽማዳ የሆነውን በወሬ ብቻ ገዝፎ ያለውን የቆመውን አገዛዝ አግዝፎ እንዲያየውና ጨርሶ የማይገፋ የማይገረሰስ የማይቻል ጭራሽም ከአየሩና ከነፋሱ ጋር ያሉ ሁሉንም ነገር ማወቅ መቆጣጠር የሚችሉ መናፍስት እንደሆኑ አድርጎ እንዲያስበውና በተጨባጭ ግን ፈጽሞ ባልሆነውና በሌለው አቅም ጉልበት ሕዝቡን አንቀጥቅጦና ቀጥቅጦ ለመግዛት እንዲችል አብቅቶታል፡፡
ደርግን አስወግዶ ሥልጣን ለመቆናጠጥ ያበቃውም ይሄ ስልቱ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ በዘመናዊ ወታደራዊ ዲሲፕሊን (አደረጃጀት) የተደራጀውን የደርግ ሠራዊት ከአንድ ሁለቱ በስተቀር በየግንባሩ ገና ውጊያ ከመጀመሩ በፊት እንዲበተን ያደርገው የነበረው ባዕዳንንና የተገዙትን የራሱን የደርግን አመራሮች ጭምር በመጠቀም በተለያየ አቅጣጫ ወያኔ አስቀድሞ በሚነዛውና ለሠራዊቱ እንዲደርስ በሚያደርገው የማስፈራሪያ ወሬ የሠራዊቱ ልብ እንዲፍረከረክ ያደርግ ስለነበር ከዐሥሩ አንዱ ብቻ መሣሪያ በታጠቀው ዘጠኙ ጀሌ (ያልታጠቀ) በነበረው በወያኔ ሠራዊት ሊገረሰስ ቻለ፡፡ እውነቱና የወያኔ ሠራዊት አቋም ወይም አቅም ግን የታወቀው ነገሩ ካለቀለት በኋላ በመሆኑ የደርግ ወታደሮች ያተረፉት ነገር ቢኖር የማይጠቅም ጸጸት ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የወያኔ ሠራዊት ስንቅና ትጥቅ በሙሉ ማለት ይቻላል ከደርግ የተወረሰ ነበርና፡፡ ነገሩ ግልጽ ተአምር ነው፡፡ እግዚአብሔር ኢአማኒውን ደርግ በቃህ ሊለው ስለወደደ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብና የማይገመት ነገር እውን ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ይሄ ጉዳይ እጅግ አስገራሚና አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የስለላን ሥራ አቅም እጅግ እጅግ ወሳኝነት በሚገባ የሚያሳይ ነው፡፡ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚባለውስ ለዚሁ አይደል?struggle1
እኔ ይህ ጉዳይ እጅግ ትኩረቴን ስለሳበኝ የወያኔን ሠራዊት “ጀግንነት” ለማየት ፈልጌ ነገሩን መርምሬው ነበር፡፡ ያገኘሁት ወይም የተረዳሁት ነገር ግን ያልጠበኩት ማለትም የወያኔን ሠራዊት ጀግንነት ሳይሆን የደርግን ሠራዊት ደካማነት ነው፡፡ የደርግ ሠራዊት በሕዝቡ ካለመወደዱ ከመጠላቱ ተቀባይነት ከማጣቱ ካለመደገፉ በተጨማሪ በተቀናጀ መልኩ ከውጭ (CIA) እና ከውስጥ በተሠራበት ሥራ ልክ ምስጥ እንደበላው እንጨት ላይ ላዩን ሲያዩት ደኅና መስሎ ነገር ግን በቀላሉ ሲነኩት ፍርክክ በሚልበት የነቀዘ አቋም ላይ የነበረ ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም እንኳን የሚዋጋው እራሱን ያደረጀ ሠራዊት እያለ ቀርቶ በነፋስ ሽውታ ሁሉ ሊደረማመስ ይችል የነበረ ሠራዊት ነበር፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታ ነው ወያኔን ለድል ያበቃው፡፡
ከዚህም የተነሣ ነው ከአቶ መለስ፣ ከጀኔራል ሳሞራ፣ ከአቶ ሥዩምና ከሌሎቹም አንደበት ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር በተደጋጋሚ ሲሉት እንደሰማነው “ምንም እንኳ ስንሠራው የነበረው ሥራ ልክ ሥልጣንን ለመያዝ እንደሚችል ያለመ ያሰበ ያወቀ ቢያስመስለንም እስከ 1982(83) ዓ.ም. ድረስ ምንአልባት በትውልድ ይሆን ይሆናል እንጅ በእኛ እድሜ ደርግን ጥለን ሥልጣል እንይዛለን የሚል ሕልምና ተስፋ ለቅጽበት እንኳን ታስቦን የማያውቅና ጨርሶም ያልጠበቅነው ነበር እኛ በረሀ የገባነው እንቢ አሻፈረኝ አንገዛም ለማለት ነበረ እንጅ ለዚህ እንበቃለን ብለን አልነበረም” በማለት የሚናገሩት፡፡ ጀግንነትስ የሚታየው አሁን ነበር! ወያኔ ትግል ላይ እያለ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ሁሉ እንደማያደርገው ስለሚታወቅበት ሕዝቡም ይሄን በተረዳ ጊዜ ሊወስደው የሚችለውን እርምጃ ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ ነው አስቀድሞ በታሪኩ እሱ ከሱዳንና ከሌሎችም ያገኘውን ሰፊ ድጋፍና ምቹ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያገኝ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ሁሉ አሳልፎ በመስጠት ጎረቤት ሀገሮችን ሁሉ በጠበቀ ወዳጅነት የያዛቸው፡፡ እሱ ከሱዳን አግኝቶት የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ሩብ ያህል ይሄም ቀርቶ ተገን ብቻ እንኳን የሚሰጥ ጎረቤት ሀገር አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያገኝ እነሱ የፈጀባቸውን 17ና 30 ዓመታት  አይደለም አንድ ዓመት እንኳን ሳይፈጅ ድራቸውን እንደሚያጠፋቸው ያውቃሉና፡፡
የአንድን መንግሥት በይነ-ሕዝባዊነት (ዲሞክራሲያዊነት) ወይም አንባገነንነት የሚያረጋግጡት ሦስት ነገሮች ናቸው፡፡
1. የራሱ “መንግሥት” የተባለው አካል ሥራ ወይም ድርጊት
2. ስለ ሥርዓቱ ማንነት ሕዝቡ የሚገልጸው
3. የሦስተኛ አካላት ነጻና ትክክለኛ ምስክርነት ናቸው
እንጅ ራሱ “መንግሥት” ሊሆን አይችልም በራሱ ላይ የሚመሰክር የለምና፡፡ እንደዛማ ቢሆን ኖሮ ደርግም እኮ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ነበር፡፡ እስካሁንም እኔ አንባገነን መንግሥት ነኝ እንዲህ እንዲህ ዓይነት የመብት ጥሰቶችን፣ እረገጣዎችን፣ ሰቆቃዎችን፣ ወንጀሎችን በሕዝቤ ላይ እፈጽማለሁ ያለ መንግሥት በዓለም ላይ ኖሮ አያውቅም፡፡ በየትም ያለ መንግሥት በይነ ሕዝባዊ መንግሥት ሆኖ እያለ ሥራው ወይም ድርጊቱ የከፋ ሆኖ አያውቅም፣ በገዛ ሕዝቡ ላይ ሰቆቃ ወይም ግፍ አይፈጽምም፣ ሕዝቡም በሚፈጸምበት የከፋ የሰብአዊ መብት አያያዝ ወይም እረገጣ ለማማረር አይገደድም፣ ነጻ ሦስተኛ አካላትም በክስ የሚጠመዱበት ምክንያት አይኖርም፡፡
አንድ ሕዝብ በሰላማዊ ትግል ለውጥ የማምጣት ዕድል እያለው ሳይቸግረው የግድ ደም ተፋስሸ፣ ተቸግሬ ወጥቸ ወርጀ፣ አላስፈላጊ መሥዋዕትነት ከፍየ፣ ተዋግቸ ሊል የሚችልበት አንዳችም አመክንዮአዊ ማስረጃ የለም ኖሮም አያውቅም፡፡ ስለሆነም የሕዝቡ ትግል ምን ዓይነት መልክ ይኑረው የሚለውን ወሳኝ ጉዳይ የሚወስነው እራሱ ሥርዓቱ ማለትም የራሱ “የመንግሥት” አስተዳደራዊ ገጽታ ነው ማለት ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ግፍና በደልን የመቃወም ለእውነትና ለፍትሕ የመቆም ሕይዎት የተለያዩ ተሞክሮዎችን አሳልፈዋል እኔን ጨምሮ፡፡ በዚህ የዜግነት ግዴታ በሆነው የሕዎት ተሞክሮ ብዙ ዓይነት አማራሪ ፈተና ይደርሳል ዋጋም ያስከፍላል በግሌ እያስከፈለኝም ይገኛል፡፡ ባለፉት ዘመናት ብዙ የተማረርኩባቸው ወቅቶች ቢኖሩም ግን አስቀድሜ ባደረኩትና ለዚህ የግፍ ቅጣት ባበቁኝ ነገሮች ሁሉ በአንዱም አልጸጸትም ለማንና ለምን እንዳደረኩት አውቃለሁና፡፡ ሥጋዬ ቢጎዳም የለመለመና የረሰረሰ ኅሊና እንጅ ወቃሽና ከሳሽ በጸጸት እሳት የሚለበልብ የሕሊና ጥያቄ ወይም ዕዳ የለብኝምና አልጸጸትም፡፡ ሆዴ ቢራብም ሕሊናዬ ግን የጠገበ ነው፡፡ ሰው ደግሞ ሰው እንጅ እንስሳ አይደለምና ክፉውና ጎጅው ረሀቡ የሕሊናው እንጅ የሆዱ አይደለም፡፡ በመሆኑም አልቆጭም፡፡ ከደረሱብኝ ፈተናዎች በወያኔ በቀጥታ ከደረሱብኝ ይልቅ በወያኔ ማስፈራሪያ ጭንቅላታቸው ከልክ በላይ በፍርሐት ከተሞላና ከተበከሉ ዜጎች የደረሰብኝ ይከፋል፡፡ በዚሁ ምክንያት ከ13 ዓመታት በላይ ከሠራሁበት ድርጅት ተሸኝቸ ያለምንም ሥራ ከመቅረት አንሥቶ ቅርቤ ናቸው ከምላቸው ሰዎች ዓይተው እንዳላዩ በመሆን የእግዚአብሔርን ሰላምታ እስከመነፈግ የደረሰ ፈተና፤ ከኔ ጋር በመቆማቸው ወያኔን ያስቆጣብናል ብለው በሚያስቡ ሁሉ ነገር ግን ደግሞ እንደማንኛውም ዜጋ የወያኔን ህልውና በማይፈልጉ ዜጎች ደርሶብኛል፡፡ የማደርገው ትግል ለእነሱ መሆኑን መገንዘብ ተስኗቸው ከዜጎች እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲደርስ ምን ያህል ስሜትን የሚነካና ቅስም የሚሰብር ተስፋም አስቆራጭ እንደሆነ በቃላት ለመግለጽ እጅግ እቸገራለሁ፡፡
ለእንደነዚህ ዓይነት ዜጎች ባጠቃላይ ለሕዝቡ ማስገንዘብና በቅጡ እንዲያጤነው የምፈልገው ነገር ቢኖር ወያኔ በረሀ ትግል ላይ እያለ አሁንም ቢሆን በመላ ሀገሪቱ ያሉ ደጋፊዎቹ ወይም ወገኖቹ በያገባኛልና በባለቤትነት ስሜት በቁርጠኝነት በከፍተኛ ምሥጢራዊነት ይሆናል ተብሎ ሊገመት በማይቻል ድብቅነት ብልጠትና ብስለት የተሞላበት ሁለንተናዊ ድጋፍና እንቅስቃሴ ወያኔን ለሥልጣን እንዳበቁትና አሁንም በሥልጣን ላይ ለመዝለቅ ዋነኛ አቅሙ እነሱው መሆናቸውን እንዲያስብና ከዚህ ተሞክሮ ምን እንማራለን በማለት እራሱን እንዲጠይቅ ከራሱ ጋር እንዲመክር፤ የሚመኘውን ነጻነት ለማግኘትም እሰከ አሁን ባለው ሁኔታ እንደምናየው አማራጭና ተስፋ ስለሌለ በተሻለ ብቃት እራሱን በማዘጋጀት ነገሩን እንዲያውቅበት፤ ከሚጠላውም የግፍ አገዛዝ በተመኘው ፍጥነት ነጻ መውጣት እንዲችል እያንዳንዱ ዜጋ ባመቸው መንገድ እንዲታገል አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ ከላይ እንዳልኩት ብስለት ብልጠትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ምናልባትም በአንድም በሌላም ምክንት የአንዳንዱ ዜጋ የዜግነት ግዴታ እንቅስቃሴ ቢደረስበትና እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚጠየቅበት ሁኔታ ቢፈጠር የሚመጣውን ምንም ዓይነት ነገር በድፍረት ለመጋፈጥና ለሌላው አርዓያነት ባለው ጽናት ዋጋ ለመክፈል እራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
ምንጊዜም ቢሆን ታላቅ ድል ታላቅ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርምና፡፡ በዚህ ዓይነት ዝግጅትና አተገባበር መንቀሳቀስ ካልተቻለ የዘለዓለም ባርነት ውስጥ እንዳለ ይወቀው፡፡ መንቀሳቀስ ከቻለ ግን ሕዝቡ ትግሉን በጣም በአጭር ጊዜና በቀላሉ ለስኬት ማብቃት የሚችልበት በጣም ሰፊ ዕድልና አቅም አለው፡፡ አንድ ነገር ግልጽ ነው ሕዝቡ አገዛዙን እጅግ ተጸይፎታል ጠልቶታል እንዲወድቅለት እንዲወገድለትም በእጅጉ ይፈልጋል፤ ወገኔ እንግዲውስ ይሄ ከሆነ ፍላጎታችን ፍላጎታችንን ልናሳካ የምንችለው ቁርጠኝነት ድፍረት ብስለትና ብልጠት የተሞላበት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ስናደርግ ጊዜ ብቻና ብቻ ነው፡፡ እንደ ጋንዲ ወይም እንደ ማንዴላ እንደ ቸጉቬራ አልላቹህም፡፡ ነገር ግን አገዛዙ እንደተወልን እንድናደርገው እንዳስገደደን አማራጭ ሁሉ እንጅ፡፡
struggle2የአንድ ለእናቱን የመይሳውን መንፈስ ግን ታጠቁ፡፡ ትልቁ ስንቃቹህ እሱ ይሁን፡፡ ባልተሰጠ ወይም በሌለ መንገድ ለመሄድ የሚፈልግ የሚሞክር ካለ ይሄ የሀገርና የትውልድ ኪሳራና ብክነት ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ጅልነትም አለ ብየ አላስብም፡፡ ሰላማዊ የለውጥ አማራጭ መንገድ የሌለ ያልተሰጠ የተዘጋ ሆኖ እያለ ባለው አገዛዝ ሀገርና ሕዝብ እየጠፉ እየወደሙ እየፈራረሱ እየተሰቃዩ “አይ በቃ ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ ሌላ አማራጭ ተገቢ አይደለም” ብሎ እጅና እግርን አጣምሮ የሀገርንና የሕዝብን ሞትና ጥፋት በዝምታ ለመመልከት መምረጥ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለውና ያልበሰለ ኢትዮጵያዊም ያልሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሀገራችን በነጻነቷ ህልውናዋ ተጠብቆ ከእኛ የደረሰችው በዚህ ፈጽሞ ዋጋ ለመክፈል በማይፈልግ ሽባ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ይሄ የመከኑና ፈሪነታቸውን እራስ ወዳድነታቸውን በሰበብ መደበቅ የሚፈልጉ ዜጎች አገደኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብ ሲጠፉ ዝም ብለን እንመልከት ማለት ታዲያ ምን የሚሉት ብስለት ነው ወገኔ?
ለ23 ዓመታት ያልተሰጠ ያልተፈቀደ ዕድል ከዚህ በኋላ ይሰጣል ይፈቀዳል ብላቹህ ታስባላቹህ? ነው ወይስ ለ23 ዓመታት ተታልላቹህ ተጃጅላቹህም አሁንም የማትነቁ ተላላና የዋሀን ናቹህ? በእነዚህ ሁሉ ዘመናት ለወያኔ የፕሮፖጋንዳ (የልፈፋ) ፍጆታ መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ምን ትርፍ አስገኛቹህ? በዚህ ንቃት ነው አሁን ሀገር እንመራለን ብላቹህ የተሰለፋቹህ? በዚህ ወቅት ደግሞ የወያኔ ባለሥልጣናት በወንጀል በግፍና በሀገር ክህደት እስከ አፍንጫቸው የተነከሩበት ወቅት በመሆኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ በሥልጣን መቆየታቸውን የሚፈልጉበት ወቅት ነው፡፡ ለ23 ዓመታት በእብሪትና በማናለብኝነት በሠሩት ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ጠንቅቀው ያውቁታልና፡፡ በመሆኑም በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መንገድ ከወያኔ ሥልጣንን መረከብ የሚቻልበት ዕድል ጨርሶ ዝግ ነው፡፡
እናም ሕዝቡ በዚሁ በተተወልን የትግል አማራጭ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ራሱን አነቃቅቶ ሥራውን ይሥራ፤ ነገ ሳሆን ዛሬ ከዛሬም ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ፡፡ ይሄንን ማድረግ በጀመረ ጊዜና በቁርጠኝነት በተንቀሳቀሰ ቁጥር የዛኑ ያህል ነጻነቱን ወደ ራሱ እያቀረባት እየሳባት መሆኑን ይወቅ፤ በዚህም ይደሰት ይጽናና፡፡ ይሄንን ባላደረገ ጊዜ ደግሞ ውጤቱ የዚህ ግልባጭና እጅግ የከፋ የማይወደውም መሆኑን ይወቅ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ማድረግ ያለበትን ዐውቆ ትግሉን በቀጠለ ጊዜ እራሳቸውን ግልጽ ይፋ አውጥተው በተለያየ መንገድ ሥርዓቱን እየታገሉ ያሉ ዜጎች ከሚያገኙት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በበለጠ ዜጎች በዚያ የመነቃቃት ደረጃ መንቀሳቀሳቸው ከፍተኛ የሆነ ብርታት ጉልበትና ወኔ ይሰጣቸዋል፡፡ “ለማንና ለየትኛው ወገን ብየ ነው በከንቱ የምደክመው” የሚለው ቀቢጸ-ተስፋ አይፈታተናቸውም፡፡ ከፍተኛ መነቃቃት ያገኛሉ፡፡ በዓለማችን ታሪክ የትኛውም የትግል እንቅስቃሴ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ለስኬት በቅቶ አያውቅም፡፡ ምኞት ብቻ ከሆነ ግን ውጤቱም እንደምኞትነቱ ሁሉ ምናባዊ ወይም ቅዥት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የሚጨበጥና በዓይን የሚታይ ነገር አይወጣውም፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ለራሱ ነጻነት ራሱ ካልተሳተፈ በስተቀር የዳር ተመልካች ሆኖ በጥቂቶች እንቅስቃሴ የሚመጣ ምንም ዓይነት ነጻነት ወይም ስኬት አይኖርም፡፡
ሕዝብ ያልተሳተፈበት ትግል ወይም እንቅስቃሴ በየትም ሀገር ለስኬት በቅቶ አያውቅምና፡፡ ይሄንን ከተረዳን የሚከፈለውና የግድ መከፈል ያለበት መሥዋዕትነት በተከፈለ ጊዜ የመጨረሻው ግብ ሀገርንና ሕዝብን ነጻ ማውጣቱ በጣም በተፋጠነና ቅርብ በሆነ ጊዜ እውን ይሆናል፡፡ የሀገራችን እጣ ፋንታ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሄንን ማድረግና መላውን ሕዝብ በዘር በሃይማኖት በመደብ ሳይለያይ በማሳተፍ ሀገሪቱ እንድትጠቀም የሚፈቅድ በይነ-ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) መንግሥት መመሥረት የቻልን ጊዜ ሀገራችን በዓለም ታይቶ በማይታወቅ እጅግ አስደናቂ ፍጥነት የማደግና ትንሣኤዋን የማረጋገጫ አቅም፣ ዘርፈ ብዙ የሆነ እጅግ ሰፋፊ ዕድሎችም አሏት የሕቧ ወኔ ትልቁ አቅሟ ነው ይህ ሕዝብ ሌሎች ሀገራት የያዙትን የመልካም አስተዳደርና በይነ ሕዝባዊ የመንግሥት ሥርዓት ቢያገኝ ባለው የሀገር ፍቅርና ወኔ የት ሊደርስ ይችል እንደነበር ሳስብ ቁጭት ያንገበግበኛል፡፡ ይሄ ሳይሆን ቀርቶ እንደ እስካሁኑ ሁሉ አገዛዙ በየጊዜው እንደፈለገ ማነቆውን ወይም ሸምቀቆውን እንዲያጠብቅብን ከፈቀድን ግን ማነቆው እየጠበቀ በሄደ ቁጥር እስትንፋሳችን ድንገት ታንቃ ለሕልፈት መዳረጋችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ሄንን የጥፋት ውጤት የሚፈልግ አንድም ዜጋ ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እውነታው ይሄ ከሆነ ደግሞ እንዴት ነው ታዲያ ነቃ ነቃ ነቃ ነቃ ነዋ!! የምን መንገላጀጅ  የምን ማንቀላፋት ነው? ለመበላት??? እባካቹህ ከዶሮ እንኳን አንነስ፡፡ ዶሮ እግሩን ብታሥሩት የታሰረበትን ገመድ በአፉ እየነቆረ ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አያርፍም፡፡ መብላትን ሁሉ ይረሳል፡፡ እንዴት ከዶሮ እንኳን እንነስ? ኧረ እባካቹህ እንፈር? ይሰማን? የመጨረሻ ወረድን እኮ! ምንም ቢያደርጉት የማይሰማው በድን እሬሳ ሆንን እኮ! እንደዚህ ሆነን እራሳችንን አመቻችተን ሰጥተን ምንም ቢያደርጉን በእነሱ ይፈረዳል እንዴ? ሰው እንዴት ለሆዱ ብሎ በዚህ ደረጃ ማንነቱን ያዋርዳል? ለሰው ልጅ እንደ ሰው ከሆዱና ከነጻነቱ ከክብሩ ከማንነቱ ማን ይበልጥበታል? ኧረ ሀፍረት ይሰማቹህ? እንዴ! ምንድን ነው የሆናቹህት? በተለይ የተማርን ነን የምትሉ ወገኖች ላልተማረው ወገናችን መጥፎ ምሳሌ ሆናቹህ እያሰናከላቹህብን ነው እባካቹህ? ነጻነታቹህን ክብራቹህን ማንነታቹህን አስቀድሙ ተባለ እንጅ አትብሉ መቸ ተባለ? እንደ እናት አባቶቻችን በነጻነታቹህ አትደራደሩ ተባለ እንጅ እያማረጣቹህም ቢሆን አትብሉ አትጠቱ ማን አለ?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment