Saturday, July 19, 2014

ሀገር የኮምፒዩተር ቫይረስና ሀከር ነው እንዴ?

ከዓመታት በፊት የቅንጅት አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አባሎችና ሌሎች ሰዎች ተከሰው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ”የቅንጅት አመራሮች የፍርድ ቤት ውሎ” በሚል ርዕስ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ተከታታይ ዘገባ አቀርብ ስለነበር ችሎቱ እስኪጠናቀቅ አንድም ቀን ከፍርድ ቤት ቀርቼ አላውቅም ነበር። በዚህም የተነሳ ክሱና የክርክር ሂደቱ ምን እንደሚመስል መናገር የሚያስችል መረጃ አለኝ ለማለት እደፍራለሁ።

በወቅቱ ዐቃቤያነ ሕግ ሽመልስ ከማል፣ አብርሃም ተጠምቀና ሚካኤል ተክሉ (እንዲሁም በስነ ምግባር ጉድለት ከዳኝነት ተባሮ ዐቃቤ ሕግ የኾነ ሰኢድ መሐመድ የተባለ ዐቃቤ ሕግ ነበር በኋላ መምጣት አቆመ) ”ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ሀገሪቱን ለማተራመስና ለማናወጥ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል” የሚል የሀገር ክህደት ክስ ይዘው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የክስ ቻርጁ ይዘትና የተጠቀሱት አንቀፆች የሞት ፍርድን ጭምር የያዙ ስለነበሩ ለማሰብ የሚከብዱ እጅግ አስፈሪ ነበሩ።


ተጠርዘው በማስረጃነት የቀረቡት ሰነዶችም የገጽ ብዛት ለሸክም የከበዱ ስለነበሩ የታደላቸው ዕለት ”ምን ተገኝቶባቸው ይኾን? እነዚህ ሰዎች ዘንድሮ አለቀላቸው” በሚል ስጋት ውስጥ ያልገባው ሰው አልነበረም። ነገር ግን የሰነድ ማስረጃዎቹ ፓርቲው በግልጽ ሲሰጣቸው የነበሩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ የፓርቲው ግልጽ ማኒፌስቶ፣ በግልጽ ታትመው ሲሰራጩ ነበሩ የጋዜጣ ቅጂዎች፣ በኢንትርኔት ላይ ታትመው የወጡ ጹሑፎች ብቻ ነበሩ። ቀኑን ሙሉ ፍርድ ቤት ሲታዩ ይውሉ የነበሩ የምስል ማስረጃዎቹ ደግሞ ፓርቲው በግልጽ ለጋዜጠኞች ሲሰጣቸው የነበሩ መግለጫዎች ነበሩ። በእነዚህ ተከሳሾች ላይ እንደ ክሱ አቀራረብ ሊያስረዳ የሚችል አንድም የሰነድም ኾነ የምስል ማስረጃ አልቀረበባቸውም። የክሱና የክርክር ሂደቱ ግን አንዳች የተለየ ድብቅ ዓላማ ሲራመድ የተደረሰበት ይመስል እጅግ የተካበደ ነበር።

ከዓመታት በኋላ ደግሞ ልክ እንደ ቅንጅቶቹ ክስ ስለ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ አካብደው እየነገሩን፤ ”በህዕቡ ተደራጅተው አገር ሊያተራምሱ” ሲሉ ተደረሰባቸው ይሉናል። ወጣቶቹ ራሳቸውን ደብቀው ሲያሴሩ በደህንነት የስለላ መረብ የተገኙ ይመስል፤ በሰላምና በግልጽ ከተማ ላይ የሚንቀሳቀሱትን ልጆች ”ሽብርተኛ” ይሏቸዋል። እስረኞቹን ይዘው ሲጠይቋቸው የነበረው ጥያቄ ግን ”እዚህ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብላችሁ ጽፋችኋል፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ እንዲህ ብላችሁ አውጥታችኋል፣ እንዲህ ቦታ ላይ እንዲህ ዐይነት ሥልጠና ወስዳችኋል” የሚል ነው። ወጥተው አደባባይ ላይ ሲናገሩና ክሱን በፍርድ ቤት ሲያቀርቡት ደግሞ ሌላ ነገር አስመስለው ልክ እንደ ኩይሳ (የጉንዳኖች ቤት ወደላይ ተቆልሎ የሚሠራ ሲፈርስ ውስጡ ባዶ) ቆልለው ትልቅ አድርገው አዲስ በመጣው ፋሽን በዶክመንተሪ አዋዝተው ያቀርቡታል።

ለምሳሌ ዛሬ ስለ ክሱ በከፊል ካነበብነው ላይ፤ ”ከተጠርጣሪዎቹ አንዷ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ የቡድኑ መሥራችና አስተባባሪ በመሆን ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. መቆየቷና ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በውጭ አገር አስተባባሪና የውጭ ግንኙነት ሆና ከመሥራቷም በተጨማሪ፣ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በማደራጀትና በመመልመል ስትሠራ ቆየች” ይላል። ይህ አንቀጽ ያነበበ ሰው በቃ የኾነ የተለየ የጦር መሳሪያ ምናምን የታከለበት ሥልጠና ጉድጓድ ቆፍረው ከመሬት ስር ተደብቀው ሲወስዱና ወይም ደግሞ የኾነ የኮድ ስም ኖሯቸው ተከታዮች አፍርተው ጦርነት የሚያዘጋጅ ሥልጠና ሲወስዱና ሲሰጡ የቆዩ ዐይነት ነገር ያስመስላል።

ሴኪዩሪቲ ኢን ኤ ቦክስ  የተባለው ይህ ሥልጠና ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ በጋዜጠኞች ዐቅም ግንባታ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለጋዜጠኞች ሲሰጡት የነበረ በኢንተርኔት ሴኪዩሪቲ ስር የሚሰጥ፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት ግንኙነት እንዲኖረን፣ ኮምፒዩተሮቻችንና ስልኮቻችን ከቫይረስና ከሀከሮች የተጠበቀ እንዲሆን፣ ፋይሎች 

ከኮምፒዩተሮቻችን ላይ ሲጠፉብን እንዴት ማግኘት እንደምንችል በአጠቃላይ የኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ለጋዜጠኞች የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ሥልጠና ነው። መቼም ጋዜጠኛና ሥልጠና አይተጣጡምና እኔ እራሴ ከሦስት ዓመትና ከወራት በፊት ናይሮቢ ከተማ ሁለት ጊዜ ይህን ሥልጠና ወስጃለሁ። ሥልጠናው ለጋዜጠኛ ብቻ ሳይኾን ለማንኛውም ኢንተርኔት ተጠቃሚ እጅግ ጠቃሚ የኾነ ሥልጠና ነው። ሥልጠናው ተደጋጋሚ የሚኾነውም አዳዲስ ቫይረስና አዳዲስ ሃክ ማድረጊያ ሶፍትዌሮች ስለሚፈጠሩ እነሱን ለመከላከል የሚረዱ ሌላ አዳዲስ ሶፍትዌሮች ስለሚሠሩ ነው።

ሥልጠናውን የሚያዘጋጁት በጋዜጠኞች ዐቅም ግንባታ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትም አሰልጣኞቹን የሚያመጧቸው የጦር መሳሪያ አገጣጠም፣ አፈታትና አተኳኮስ ልምድ ካላቸው ታጋዮች መካከል መልምለው ወይም ከአንድ ስለላ ድርጅት መርጠው ሳይኾኑ ከማይክሮሶፍት ኦፊስ ልምድ ያላቸው ሶፍትዌር ኢንጅነሮችና ከሞያው ጋራ የተያያዘ ዕውቀት ያላቸው ባለሞያዎችን ነው። እንዲህ ያለውን ሥልጠናም በርካታ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ክሱን ይዘው ከቀረቡት ዐቃቤያነ ሕግና ዳኝነት ሊሰጡ ከተሰየሙት ዳኞች መካከልም ብዙዎች ሠልጥነዋል።                       

ይህ ኮምፒዩተሮችንና ስልኮችን ከቫይረስና ከሀከሮች ለመጠበቀ የተሰጠ ሥልጠና ወጣቶቹ ጋር ሲደርስ ”ሀገርን በአመፅ፣ በሁከትና በብጥብጥ ለመለወጥ” የተወሰደ ሥልጠና ተብሏል። እኔ የምለው ሀገር የኮምፒዩተር ቫይረስና ሀከር ነው እንዴ?

No comments:

Post a Comment