Friday, July 25, 2014

በውጭ ያለነው ኢትዮጵያዊያን ምርጫዎች አሉን! – አንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ አርብ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት

ዛሬም እንደሳምንቱ መብታችንን እያሉ ኢትዮጵያዊያን በየመስጊዱ ተሰብሰበዋል። በየቀኑ በየቤተክርስትያኑ ጸሎታቸውን ያደርሳሉ። በየትምህርት ቤቱ በራቸው ተንኳኩቶ እንዳይወሰዱ ተደብቀው ያጠናሉ። መምህራን በፍራቻ፤ ለተማሪዎቻቸው ሳይሆን ለካድሬዎቹ ይሽቆጠቆጣሉ። አርሶ አደሮች ለሚያርሱበት መሬት፣ ለማዳበሪያና ለካድሬ ሲሉ አንገታቸውን ደፍተዋል። ላብ አደሮች የሥራ ዋስትና አንገታቸውን አንቆ ወገባቸውን አጉብጦታል። ነጋዴዎች ከኤፈርት ጋር ውድድሩ ራቁታቸውን አስቀርቷቸዋል። ጋዜጠኞች ዓይኖቻችሁን ጨፍናችሁ እኔ የምላችሁን ካላደረጋችሁ ተብለው እስር ቤቱን ሞልተውታል። ማን ተርፎ? የፖለቲካ ምኅዳሩን ማነቆ የጨበጠው መንግሥት አምልኩኝ ብሏል። ሀገራችን ባለችበት የፖለቲካ ሀቅና እኛ አሁን ባለንበት ድንዘዛ፤ አንድ የሚያነቃ ብራቅ ብልጭ ሊልብን ይገባል። የአንድነት ውይይት የግድ ነው። ይቺ ሀገራችን ትልቅ ውጥረት ውስጥ ገብታለች። እኛም በያለንበት መሯሯጣችን አልቀረም። ነገር ግን በአንድ ላይ ሆነን፤ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ለመወያየት አልቻልንም። ለምን አንችልም? ታዲያ ምርጫችን ምንድን ነው? እኒህን ሁሉ እኮ ለመነጋገር መንገድ መፈለግ አለብን። እስከዛሬ ሌሎች ምን አደረጉ? ማለቱን ትተን፤ እያንዳንዳችን ምን 

አደረግን? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ይህ ግን ለአንድነት መጠይቁ መንገድ እንዲከፍት አንጂ፤ እያንዳንዳችን ለየራሳችን የምንሠጠው መልስ አለን። ያ መልስ ያጠግባል? ወይንስ አያጠግብም? የየራሳችን መመዘኛዎች አሉን። ያ በቂ አይደለም። በስብስብ የአንድነት ጥያቄዎች ናቸው ወሳኞቹ። በአንድነት ወደ የት እየሄድን ነው? ወይስ የት ላይ ተገትረናል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። የሚቀጥለው የኢትዮጵያ መንግሥት ምን መሆን አለበት? ያ ፍላጎታችን በምን መንገድ ይሳካል? ብለን አንድ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን። በሀገር ውስጥ፤ የወገንተኛውን አምባገነን መንግሥት የግር ሠንሠለት እየፈተጉ፤ የሚቻላቸውን ያህል እየተራመዱ ነው። እኛስ አንጻራዊ ነፃነት ያለን፤ ምን ማድረግ አለብን? ጥያቄው ይህ ነው።


በምንናገረው የምንደረድረውና ተጨባጩ ሀቅ ምን ያህል ዝምድና አላቸው? ምኞታችንና ፍላጎታችን ከያዝነውና ልናደርገው ከምንችለው ነጥለን ማየት እንችላለን ወይ? በየቦታው፣ በየድረገፁ፣ በየፓልቶክ ክፍሉ፣ በየሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በየስብሰባው፤ አንድነት! አንድነት! አንድነት! እያልን ነው። አንድነት ደግሞ ቁጭ ብለው ሲጠብቁት የሚመጣ አይደለም። ወደ አንድነት በሚወስደው መንገድ አንድ እርምጃ መሰንዘርን የግድ ይላል። እስኪ አስቡ፤ አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሀገራዊ አስተባባሪ ድርጅት የለንም። የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ብዙ የተለያዩ ድርጅቶች አሉን። ሀገርን የሚያድን ራዕይ፣ ያን የሚዘውር አንድ ድርጅት፣ ይህ ድርጅት የሚያስተባብረው የኢትዮጵያዊያን ሕዝባዊ ንቅናቄ፤ እኛን እየጠራን ነው። አሁን ባለው የፖለቲካ ሀቅ ሥር፤ እየሾለ የመጣ የእሳተ ጎመራ ረመጥ ውስጡ ግሏል። መጨረሻው የማይታወቅ ፍንዳታ አሰፍስፏል። የግለሰብ ማንነትና የሀገር ሕልውና ተፋጧል። የዕለት እንጀራችንን ብቻ በመመልከት ቀኑን ልንገፋ አንችልም። የተግባር ደወል አቃጭሏል። ምን ማድረግ እንዳለብን በአንድነት መነጋገር አለብን። የሚከተሉት አምስት ምርጫዎች ከፊታችን ተደቅነዋል።

፩ኛ. እስካሁንና አሁንም የያዝነውን መንገድ እየተከተልን መቀጠል፤
የመጀመሪያው ምርጫችን፤ ግፈኛው መንግሥት በደል በፈፀመ ቁጥር ሆ! ብለን ተነስተን ተመልሰን ወደ እንቅልፋችን መሄድ፣ ሀገር ቤት ያሉ ቆራጦች ከሞትና ከእስር ያመለጡት መሰደድ፣ እኛም እስረኞችን መቁጠር፣ ለውጭ መንግሥታት ልመናችንን ደግመን ደጋግመን ማሰማት፣ ይኼ ነው እስከ አሁን ያደረግነው። በዚሁ መቀጠል የትም ሌላ ቦታ አይወስደንም። እናም የኛ ምርጫ መሆን የለበትም።

፪ኛ. የሚታገሉ ድርጅቶችን በሙሉ ጥፋተኛ ብሎ ኮንኖ፤ አዲስ ድርጅት በመመሥረት መታገል፤
ድርጅቶች በሙሉ ወደ አንድነት ካልመጡ ሁሉን ባንድ ላይ ጥፋተኛ ብሎ ኮንኖ፤ አዲስ ድርጅት መስርቶ፣ የነበሩ ድርጅቶችን አባላት በሙሉ አውግዞ፤ አዲስ ድርጅት በአዲስ ታጋዮች መመሥረት ነው። እንግዲህ እስከዛሬ ተደብቀው ወደ ትግሉ ያልመጡ አባላት ከየት እንደሚገኙ አላውቅም። እስከዛሬ በየድርጅቶች ተካተው ሲታገሉ የነበሩትን አባላት ወደ ጎን ተብሎ የሚኬድበት መንገድም የት እንደሚገኝ አላውቅም። ይቺ ሀገራችን፤ እስካሁን የታገሉትንና አዲስ ታጋዮችን ትፈልጋለች። የተደራጁትም ሆነ ያተደራጁትን ትፈልጋለች። ድርጅቶች ሳይሆኑ ሀገራችን ናት አደጋ ላይ ያለችው። በአንድነት አቤት ካላልን፤ ሰሚ ያጣው ወገናችን ስቃዩ ይቀጥላል። ስለዚህ አንድነታችን፤ ከግለሰብ ፍላጎት፣ ከድርጅት መርኀ-ግብር በላይ ነው። ትግሉ ለሀገር እንጂ ለሥልጣን አይደለም። ስለዚህ ይኼኛው አማራጭ የኛ ሊሆን አይገባም።

፫ኛ. አንዱን ድርጅት መርጦ፤ ሁላችን እዚያ ላይ መረባረብ፤
ሶስተኛው ምርጫ ደግሞ ካሉት የትግል ድርጅቶች ሁሉ አንዱን መርጠን ሁላችን ወደዚያ በመግባት መታገል ነው። ይኼ ደግሞ በጣም የከፋ፤ አቸናፊና ተቸናፊን የሚያስመርጥ፣ ቡድናዊ ስሌትን የሚያጎለብት፣ ከመሰባሰብ ይልቅ መራራቅን የሚያጸና፣ ሀገራዊ ከሆነው ጉዳያችን ይልቅ የተመረጥእውን ድርጅት መርኀ-ግብር የሚያመልክ ይሆናል። ይህ በመሠረቱ ሁላችን እንሰባሰብ የሚለውን ተጻራሪ ነው። እናም የኛ ምርጫ ሊሆን አይገባውም።

፬ኛ. እጆቻችንና እግሮቻችንን ሰብስበን፣ አጣጥፈን፣ አርፈን መቀመጥ፤
አራተኛው ምርጫ ሌሎች ይታገሉ እኔ በቃኝ እያልን የግል ኑሯችንን ለማቅናት፤ እጅና እግሮቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ ነው። እንግዲህ ከታሪክ እንደተማርኩት፤ ትግል በግለሰቦች ፍላጎትና ምኞት የሚመጣና የሚቀጥል ሳይሆን፤ በተጨባጩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀቅ ላይ የተመሰረተ ክስተት መሆኑን ነው። ታዲይ ማንም ተወው ማንም ሸሸው ትግሉ በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ሀቅ ላይ የተመሠረተ ስልሆነ፤ ሀገራችን የኢትዮጵያዊያን ሆና፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ሠፍኖ፣ በእኩልነትና በሕግ የበላይነት ላይ የቆመ የሕዝብ መንግሥት ኖሮ፤ እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት በግለሰብ ደረጃ በኢትዮጵያዊነቷ በሀገሯ የፖለቲካ ምኅዳር መሳተፍ ስትችል፤ ትግሉ በሰላማዊ መንገድ ይቀየራል። እስከዚያ ግን በተጨባጩ ሀቅ በሚደቆሱት ጭቁኖች ይቀጥላል። አርፎ መቀመጥ የፈለገ፣ የራሱን መኖር ብቻ ያነገበ፣ ተምሬ ወይንም ሀብት አካብቼ ሌሎች ታግለው ነፃ ሲያወጧት ያኔ ሀገሬ አገባለሁ ያለ፣ ዛሬ ለሀይለኛው አጎብጣለሁ ያለ፤ መርጫው የሱ ነው። ይህ ግን የታጋዮች ምርጫ ሊሆን አይችልም።

፭ኛ. ኢትዮጵያዊ የሆኑ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ሁሉ ወደ አንድ እንዲመጡ ከፍተኛ ግፊትና ጥረት ማድረግ፤
የመጨረሻው ምርጫ ታጋዮችንና ለመታገል የሚፈልጉትን በሙሉ ወደ አንድ ሠፈር በማሰባሰብ፤ በሀገር አጀንዳ አንድነት ፈጥሮ፤ አንድ ድርጅት መሥርቶ፣ አንድ ራዕይ ይዞ፣ አንድ ተልዕኮ ሰንቆ፣ መነሳት ነው። ይኼን ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት ለመጣልና በቦታው የኢትዮጵያ የሆነ፣ የሕዝቡን ሉዓላዊነት የጠበቀ፣ የሀገሪቱን አንድነት ያስከበረ፣ የያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የግለሰብ መብት በሕግና በተግባር ያረጋገጠ፣ የሕግ የበላይነትን ያሠፈነ መንግሥት እንዲተካ ማድረጉ የሁላችን ግዴታ ነው። ይህ ብቻ ነው የትግሉ ማጠንጠኛ ማዕከል። በየድርጅቱ ያሉ ታጋዮች በትግሉ ውስጥ መስዋዕትነት እየከፈሉ በመታገል ላይ ናቸው። ይሄኛው ድርጅት በዚህ ምክንያት አልተስማማኝም፣ ያኛው ደግሞ በዚያ ምክንያት አልተስማማኝም እያልን የቆየን ሁሉ፤ አሁን ሁላችንም የሚያቅፍ የኢትዮጵያዊያን ድርጅት በአንድነት ልንመሠርት ነውና፤ ወደ ታጋዮች ጎራ ብቅ ማለት አለብን። አሁን እርስ በርስ መጻጻፉ፣ ለየራሳችን መናበቡ ይብቃ። ተጽፎ አያልቅም። ትግሉ ደግሞ በትረካ ወደፊት አይሄድም። የተግባር ጊዜ ነው።

ይኼ አምስተኛው መንገድ ሁላችንን ከማሰባሰቡና በሀገር ቤትም ላሉት ተስፋ ከመሆኑ በላይ፤ ጉልበታችንን ያጠነክረዋል። ልናደርግ የምናስበውን ክብደት ይጨምርለታል። በአንድነት የምንፈጥረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ፤ ጉልበት ብቻ ሳይሆን፤ በትግሉ ሂደት ክፍተኛ የአእምሮ ተጽዕኖ በመፍጠር፤ በታጋዩ ወገን የሚዛን ደፊነት ጫና አለው። እናም በአንድነት፤ ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ምን እየሠራ ነው? ብለን የዕለት ተዕለት አካሂያዱን በተጨባጭ መረዳት እንችላለን። በውስጡ ስለሚካሄደው ክንውን በቂ መረጃ ይኖረናል። በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ስላለው ግፍ ዘገባውን መረዳትና መያዝ እንችላለን። አሁን በያዝነው መንገድ እየተጓዝን፤ አስካሁን ከደረስንበት የተለየ ውጤት መጠበቁ የዋህነት ነው። የያዝነው ጎዳና የትም አላደረሰንም። በመንገዱ ግን ብዙዎች ረግፈውበታል። ብዙዎች አካለ ስንኩል ሆነውበታል። ብዙዎች ማቅቀውበታል። ብዙዎች ተለውጠውበታል። እኒህ ሁሉ ይኼን የከፈሉት፤ አሁንም እኛ ለምንመኛት ሀገራችን ዋስትና ይሆናል ብለው ነበር። አሁንም ሌሎች መስዋዕትነቱን እየከፈሉ ነው። እኛስ በአንድነት ኃላፊነት የለብንም?

በአንድ ቆመን መገኘት ካልቻልን፤ አንድም የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ዕድሜ በማራዘም፤ የሕዝቡን ሰቆቃ እያባባስነው ነው፤ ሌላም የነገዋን የሀገራችንን ሕልውና ከጥያቄ ውጪ ወደ የሌሽነት እየቀየርነው ነው። መታገል ያለብን እኛ ነን። የውጭ ኃይሎች፤ ሀገሮችም ሆኑ ድርጅቶች፤ በኛ የውስጥ ሂደት ያላቸው ሚና፤ እኛ እንደፈቀድንላቸው ነው። እናም ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። የአሜሪካ መንግሥት፤ ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት፤ ሀገሪቱን ጠፍርቆ በመያዝ በአካባቢው ጥቅሜን ሊያስጠብቅልኝ የሚችል ኃይል ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ ከውጭ ሀገር መሪዎችም ሆነ ሕዝብ፤ ምንም አንጠብቅ። ኃላፊነታችንን ራሳችን እንውሰድ።

ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ዘለዓለማዊ ሆኖ ይቆያል በሚል ፍራቻ የተተበተቡት፤ ከሕልማቸው በራሳቸው መንቃት ካቃታቸው፤ ከመንግሥቱ ጋር አብረው ወደ ውድቀቱ ይጓዛሉ። ይህ መንግሥት ዘለዓለማዊ አይደለም። በጣም በጣም በጣም ጊዜያዊ ነው። ከፍተኛውን ዕድገቱን ጨርሷል። የቀረው ቁልቁለቱን መንደርደር ነው። ካሁን በኋላ እየደከመ መሄድ እንጂ፤ የነበረ ጥንካሬውን መልሶ የሚያገኝበት እውነታ ክዶታል። የዚህ መንግሥት የትውልድ ቆጠራ አስተዳደር፤ ሕዝቡን አልለያየውም፤ ይበልጡኑ ወደ አንድ ሠፈር አቀራርቦታል። ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ሁሉን በዳይ ቡድን ነው። ይህ መንግሥት አፍቃሪ የለውም። ይህ መንግሥት ከቡድኑ ጥቅም ውጪ፤ ማንንም አያምንም። ስለዚህ፤ መላ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም ኢትዮጵያዊ ነን ብለው ያመረሩትን፤ ይጠላል። እናም እነኚህ በአንድነት እየተጠቁ ያሉ በመሆናቸው፤ የአንድነት ድር ሰብስቧቸዋል። በነዚሁ ኃይሎች ይህ መንግሥት ይደመሰሳል።

ኢትዮጵያዊነት በገዥዎች እንቅፋትነት አለማደጉና በሁሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ አለመታቀፉ፤ ሀቀኛነቱን አይሰርዘውም። በርግጥ እኔ በድሜዬ ባየኋቸው የሶስቱ ሥርዓቶች ቁንጮዎች፤ የራሳቸውን ድሎት ብቻ መንገዳቸውና ግባቸው አድርገው፤ የሕዝቡንና የሀገሪቱን ጥቅምና ዕድገት ወደ ፊት ባለማስቀደማቸው፤ ጠንካራና ላላ ያለ ኢትዮጵያዊነት በሀቅ በሀገራችን ላይ ታይቷል፤ እየታየም ነው። ይህ ግን በምንም መልኩ ኢትዮጵያዊነት የለም አያስብልም። ኢትዮጵያዊነት ጭፅ የሆነ መሠረት ስላለው፤ ይለመልማል። የሚለመልመው ደግሞ፤ ሁሉም በእኩልነት ተነስተው እጅ ለእጅ ስለሚጨባበጡ ነው።

No comments:

Post a Comment