Thursday, July 24, 2014

ግንቦት 7 ለብሔራዊ አንድነትና ነፃነት ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል ያስፈልጋል አለ

ግንቦት 7 በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጣው ር ዕሰ አንቀጽ እንደሚከተለው ተስተናግዷል።
በአለፉት ጥቂት ሣምንታት በወያኔ የተፈፀሙ የእብደት ተግባራትን ስናጤን ከፊት ለፊት ኢትዮጵያችንን እየጠበቀ ያለው መንታ መንገድ አመላካች ነው። ይህ ከፊት ለፊት የሚጠብቀን መንታ መንገድ አንዱ ወደ ብሔራዊ አንድነት፣ ነፃነትና ብልጽግና ሌላው ወደ እርስ በርስ ትርምስና ውድቀት የሚያመሩ ናቸው። የአንድነት፣ የነፃነትና የብልጽግና መንገድ ለመያዝ መስመራችንን ማስተካከል ያለብን ከአሁኑ ነው።
ለመሆኑ ከላይ ያልነውን ለማለት ያስቻሉን በአለፉት ጥቂት ሣምንታት በወያኔ የተፈፀሙት ተግባራት ምንድናቸው?
አንደኛ፤ ወያኔ፣ ዓለም ዓቀፍ ህግንና ሥርዓትን በጣሰ መንገድ ከየመን ባለሥልጣናት ጋር በማበር የንቅናቄዓችንን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ማፈኑ በአለፉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ ውስጥ የተደረገ አብይ ክስተት ነው። ይህ የወያኔ የውንብድና ተግባር ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ አስቆጥቷል። ወያኔ፣ ለሀገር ነፃነትና ለእኩልነት የሚታገልን አንድ ታላቅ ሰውን ማፈንኑና ከእይታ ከልሎ እያሰቃየው መሆኑ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ቁጣ ወደ መገንፈል አስጠግቶታል። አቶ አንዳርጋቸው በጠላት እጅ ከወደቀም በኋላ ኢትዮጵያዊያንን አሰባሳቢ ኃይል ሆኗል።
ሁለተኛ፤ ሰላምተኞቹን ብሎገሮችንና ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት በመክሰስ በቋፍ ላይ የነበረውን የወጣቶች ትዕግሥት እንዲሟጠጥ አድርጓል። ስለኢንተርኔት አጠቃቀምና ጥንቃቄ ሥልጠና መውሰድ በክስ ቻርጁ ውስጥ መካከቱ ሥርዓቱ ከእውቀት ጋር የተጣላ መሆኑ በግልጽ አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ በህጋዊ ፓርቲዎች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ ወጣት መሪዎችን መርጦ በማሠርና በሽብርተኝነት በመወንጀል የወያኔ የአፈና መዋቅር ወጣቱ ላይ ማነጣጠሩ ግልጽ ሆኗል።


ሦስተኛ፤ እጅግ ሰላማዊና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ አቤቱታቸውን በማቅረብ ላይ የነበሩትን ሙስሊም ወገኖቻችንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመደብደብ እና በጅምላ በማሠር በወያኔ መድብለ ቃላት ውስጥ “ሰላማዊ ትግል” የሚባል ነገር አለመኖሩ፤ ተቃውሞ ሁሉ “ሽብር” እንደሚባልና በሽብርተኝነት እንደሚያስከስስ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። ይህም የሥርዓቱ አውሬዓዊ ባህሪ መገለጫ ሆኗል።

አራተኛ፤ አፈናውና እስሩ ወደ ትግራይም በመዛመቱ ወያኔ የቆመበት ምድር እየራደ መሆኑ አመላካች ሆኗል። ትግራይ ውስጥ የነበረው አፈና ድብቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከወያኔ የውስጥ ሽኩቻ ጋር ሲያያዝ ቆይቷል። አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው። አገራዊ ርዕይ ያነገቡ፤ ወያኔን በጽናት ለመታገል የቆረጡ የትግራይ ወጣቶች ወደፊት እየመጡ ነው። እነዚህ ወጣቶች የተጫነባቸውን ድርብርብ ጫና በመበጣጠስ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጎን መቆማቸውን በተግባር እያረጋገጡ፤ ለዚህም መስዋዕትነት እየከፈሉ ናቸው።

ከላይ የተዘረዘሩት አራት ጉዳዮች በጋራ ሲታዩ የተበታተነ የሚመስለው እና በተለያዩ ስልቶች የሚደረገው ትግል የሚሰባሰብበትና የሚቀናጅበት ወቅት ላይ መደረሱ አመላካቾች ናቸው። ዛሬ የምንገኘው የተለያዩ የትግል ስልቶች እንዲናበቡና እንዲደጋገፉ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ነው።

በተለይም ወያኔ፣ መሸሸጊያ ምሽጉ አድርጎ በሚቆጥረው ትግራይ ውስጥ እየዳበሩ የመጡት የአመጽም አመጽ-የለሽ ትግሎችም አስተዋጽኦ ከፍተኛነት ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲረዳ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው። የወያኔ የአፈናና የመጨቆኛ መዋቅሮች የህወሓት አባላት በሆኑ የትግራይ ዘውጌ ማኅበረሰብ አባላት የሚዘወሩ መሆኑ እውነት ነው። ይህ ማለት ግን ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ወኪል ወይም ጠበቃ ነው ማለት አይደለም። ትግላችን ከወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ጋር መሆኑ እና የትግራይ ሕዝብ የዚህ ትግል አጋር፣ የውጤቱም ተጠቃሚ መሆኑ ማስረገጥ ተገቢ ነው።

ከፊት ለፊታችን ካሉት መንታ መንገዶች መካከል የአንድነትን፣ የነፃነትና የብልጽግናን መንገድ ለመምረጥ የትግራይ ሕዝብ በስፋት ትግሉን እንዲቀላቀል ማድረግ ተገቢ ነው። ትግራይ የህወሓት የግል ጓዳ መሆኗ የማብቂያ ጊዜ ማፋጠን ይቻላል። በዲሞክራሲያዊ ትግል ውስጥ ያሉ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ ከያዙ ወያኔን ማንሳፈፍ የሚቻልበት እድል በስፋት ተከፍቷል።

ስለሆነም፣ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዘረኛውና ፋሽስታዊው ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል አንዱ የትግላችን ስትራቴጂ ሊሆን ይገባል ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment