Friday, July 25, 2014

ምንም ቢሆን ኢኮኖሚያችን በሁለት አሃዝ ማደጉ ይቀጥላል!!!

                                                                                                        ግርማ ሠይፉ ማሩ

“የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” በያዘነው ሳምንት መጀመሪያ በህግ የተፈቀደለትን ሰማኒያ ከመቶ ጊዜ አጠናቆ ተዘግቷል፡፡ ስራውን እንጂ ግዜውን አላልኩም፡፡ በቀረው 20 ከመቶ በሚሆነው ጊዜ ባለፉት አራት ዓመታት ያከናወናቸውን ዓይነት ተመሳሳይ ተግባራት ያከናውናል ብሎመጠበቅ አይቻልም፡፡ ለዚህ ዋናውምክንያት ኢህአዴግ፣ በገዢነት 

በማንኛውም መንገድ ሊቀጥል እንደሚችል እርግጠኛ ቢሆንም፤ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ግን መቀጠል አለመቀጠላቸውን የሚያረጋግጡበት ግልፅ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ ስጋት ላይ እንደሚወድቁ ስለማውቅ ነው፡፡ ይህ ስጋት ካሁኑ መታየት ጀምሯል፡፡ ስለዚህ አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት፣ አሁን በቀጣይ ዕጣ-ፋንታቸው ላይ የሚወሰነውን የሚጠባበቁበት እና በግላቸውም ቢሆን አማራጭ የሚመለከቱበት ጊዜ ነው፡፡


እነዚሁ የምክር ቤት አባላት የአራተኛውን ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቂያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ከደርዘን የሚበልጡ ጥያቄዎች መካከል፤ ገዢው ፓርቲ ያቀደውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ክፍተት እንዳለበት ማሳለቁ አያቋርጥም፡፡ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትም መልስ ‹‹ያሉትን
ችግሮች ተቀብሎ ቢሆንም›› በሚል ማገናኛ ቃል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት ዕድገት አስመዝግበናል የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ አንድ አንድ ነጥቦችን አንስተን እንመልከት፡፡

መንግስት፣ በዘመቻ ከሚሰራቸው የኮንስትራክሽን እና ሌሎች ግንባታዎች ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ያሉ እድሎች ወደፊት ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉት፤ በምርቱ ዘርፍ የግል ባለሀብቱ ሲሳተፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ዘርፍ ግን በሚፈለገው መጠን የስራ እድል ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ እየተስፋፋ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀብለውታል፡፡ ይህም ቢሆን የሀገራችን ኢኮኖሚ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሰረት በሁለት አሃዝ ማደጉን ግን አላቋረጠም፡፡ የምርቱ ዘርፍ የስራ እድል ቢፈጥርም ባይፈጥርም፣ ኢኮኖሚያችን ማደጉን ለነገሩ ኢትዮጵያዊያን አስማተኞች ሳንሆን አንቀርም፡፡ ስራ ቢኖረንም ባይኖረንም በልተን/ቀምሰን ማደርና ጠዋት ለስራ-ፈትነት አርፍዶ መንቃት የለመድን ይመስለኛል፡፡

መንግስት የደሞዝ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ፤ ስግብግብ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይገባቸው በተደጋጋሚ ከመገለፁ በተጨማሪ አሁን የሚመጣ የዋጋ ጭማሪ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው እንድናምን እየተነገረን ነው፡፡ የኢኮኖሚክስ “ሀሁ” እንደሚነግረን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ማለት የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ሲሆን፣ የኢኮኖሚክሱ “አቦጊዳ” ደግሞ እነዚህ ሁለቱን የሚያሳልጠው የገንዘብ አቅርቦት ተመጣጣኝ አለመሆን እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ክፍተት መኖሩን አምነው፣ ይህ ክፍተት የሚዘጋው፣ የበለጠ የከፈለ ያገኛል በሚለው መርህ መሆኑን እርሱት እያሉን ነው፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ካልሆነ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክንያት ለምን ሌላ እንደሚፈልጉ ለእኔ ግልፅ አይደለም፡፡ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር መንግስት በመሰረታዊ ዕቃዎች ላይ ድጎማ በማድረግ ዋጋ እንደሚያረጋጋ የነገሩን፣ በቂ አቅርቦት በሌለበት ድጎማ ዋጋ እንደማያረጋጋ ለማወቅ የኢኮኖሚ ሊቅ መሆን አይጠይቅም፡፡ በዚህ ጊዜ የሚኖረው በኮታ ማደል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥቁር ገበያ እና ለከፍተኛ ዋጋ ንረት መንገድ ይከፍታል፡፡

ለማንኛውም በደሞዝ ጭማሪ ምክንያት በሚፈጠር የዋጋ ንረት ሃላፊነቱን የሚወስዱት “ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች” ስለሆኑ፤ እነሱን ለመታገል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጠው አቅጣጫ “ተደራጁ” የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር፣ አሁን ባለው ሁኔታ የሚያዋጣ ስላልሆነ በየመስሪያ ቤታችን የዋጋ ንረትን በጋራ ለመቆጣጠር መደራጀት ሊኖርብን ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ግን ለምን አሁን ያለው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት አይረከበውም? ይህ አደረጃጀት፤ አንደኛ መንግስት በትክክል መደጎሙን ይከታተላል፤ እግረ-መንገዱንም ከ“ስግብግብ ነጋዴዎች” ጋር ግብይት እንዳናካሂድ አድማ ለማድረግ ይጠቅመናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “በነፃ ገበያ” ስርዓት ዋጋ ጨመርክ ተብሎ ማሰር ስለማይቻል ነው አድማ ማድረግን ያመጣሁት እንጂ አብዮት ለመቀስቀስ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስጠይቀው በሸማቾች ህግ ሳይሆን በፀረ-ሽብር ህግ ነው፡፡

መንግስት፣ በዕቅድ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ንግድ ለማግኘት አቅዶ ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ለዚህም ዋና ዋና የተባሉት እና በመንግስትም እንደችግር ከተጠቀሱት ውስጥ ቡና ማልማት ከሚችለው መሬት አንፃር ከሃምሳ በመቶ በታች፣ ከምርታማነት አንፃር ገና አንድ ሶሰተኛው አካባቢ ላይ መሆናችን ነው፡፡ በዕቅድ ዘመኑ የቅባት እህሎች ለማምረት ወደ ተግባር እንደሚገቡ የታሰቡት ክልሎች ወደ ስራ ያለመግባታቸው፤ የገቡት የአማራና የትግራይ ክልልም ቢሆኑ፣ ምርታማነታቸው ከሃምሳ በመቶ በታች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት የምርት ዘርፉ ገና ያልተጀመረ መሆኑ፣ በማዕድን ዘርፍ የወርቅ ዋጋ መቀነስ ብቻ ሳይሆን በባህላዊ አምራቾች ሊገኝ የታሰበው ያለመሳካቱ፣ እንዲሁም እጅግ ብዛት ያላቸው የንግድ ሰርዓት ማነቆዎች በመኖራቸው ምክንያት ዕቅዱ አልተሳካም፡፡ ይህን የሚያህል ሀገራዊ ዕቅድ ባልተሳካበት ሁኔታ፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት አንድ መድህን ግን አልጠፋም፡፡ ይኽውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዘመዶቻቸው የላኩት ገንዘብ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን የሀገሪቱ አጠቃላይ እድገት በሁለት አሃዝ ከማደግ የከለከለው አንድም ምድራዊ ሀይል አልተገኝም፡፡ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችን ከስልሣ በመቶ በታች ቢሆንም እድገታችን ግን ካቀድነው ፍንክች አላለም፡፡

የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው ዜጎች በትምህርት በሚያገኙት ክህሎት እና ይህንንም ክህሎት እሴት ለመጨመር ሲያውሉት እንደሆነ ይታመናል፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግብ ከትግራይ ክልል በስተቀር ያለመሳካቱ ጉዳቱን ያዩበት አቅጣጫ ምቾት ሰጥቶኛል፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ወቅት ከትምህርት ገበታ ከተገለሉ ለጉልበት ብዝበዛ የሚጋለጡበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተውናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያለ እድሜ ጋብቻ እና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚወድቁ መሆኑን ደምረን ስናየው፤ የዚህ እቅድ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ጉልህ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በትምህርት ዘርፍ ወደ ስልሳ ሁለት ከመቶ ለማድረስ የታቀደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ያልተሳካ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢታመንም፤ በእድገታችን ላይ አንድም ነጥብ ለመቀነስ ግን በቂ አይደለም፡፡

መንግስት፣ በገጠር ከተሞች እና ማዕከላት ለማስፋፋት አቅዶት የነበረው የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም፤ በባለሞያ ዕጥረት እና አንዳንድ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ባለመቻሉ እንደታሰበው ሊሄድ እንዳልቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡ መቼም የመብራት አስፈላጊነት ጨለማን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን መብራት በሚገባላቸው አካባቢዎች የሚፈጥረውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ሰዎች መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች የወሊድ ምጣኔም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ በእኛ ሀገር ግን ይህ እቅድ በታሰበው መጠን ባይሳካም፣ አጠቃላይ እድገታችን ላይ ምንም ጫና የለውም፡፡ ለዚህም ይመስላል በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሁለት አሃዝ ያደግነው፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አራተኛ ዓመት ማገባደጃ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አንድ የቱሪዝም ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በክልሎችም፣ በክልል መስተዳድሮች የሚመራ የቱሪዝም ምክር ቤት እንዲያቋቁሙ ከስምምነት ተደርሷል ብለውናል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት ለመጠቀም አቅጣጫ የሚያሳይ የተባለለት ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ገለፃ መሰረት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሴክትር ያላትን አቅም የሚያህል አንድም የአፍሪካ ሀገር የለውም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ልንጠቀም እንዳልቻልን ይስማማሉ፡፡ ይህን ባናደርግም ግን እድገታችንን ከሁለት አሃዝ ማን ሊያወርደው ይችላል? የሀገር እድገት በእምቅ ሀብት ሳይሆን በተግባር ላይ በዋለ ምርት የሚለካ ቢሆንም፣ ‹‹ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ›› የሚሉት ሹሞች ግን ‹‹አድገናል›› እያሉን ነው፡ ፡

የምክር ቤት አባላት ካቀረቡት ጥያቄ አንዱ ‹‹የኦዲት ሪፖርትን መሰረት ያደረገ ተጠያቂነት ለምን አይኖርም?›› የሚል ነበር፡፡ ክቡርነታቸው መልስ ሲሰጡ ዋናው ነገር ሪፖርት አቅራቢ መስሪያ ቤቶች ያለውን እውነት ማሳየታቸው ነው ብለውናል፡፡ ሌላው በሂደት የሚደረስበት ነው ማለታቸው ነው፡፡ ችግሮቹን ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ቢኖር አሳሳቢ ይሆን ነበር፡፡ ይህ አቅጣጫ መቼም የመንግስትን ሀብትና ንብረት ተገቢ ባልሆነ መስመር ለሚጠቀሙ ሰዎች፣ ጥሩ አረንጓዴ መብራት ይመስለኛል፡፡ ዘራፊዎቹ ዘረፋ ይቀጥላሉ፤ ሀብት ይባክናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የሀገሪቱን እድገት ከሁለት አሃዝ የሚያወርድ አይሆንም፡፡

በመጨረሻም በግሌ ያነሳሁት የግል ባንኮች ተሳትፎ በሚኖርበት ሁኔታ የማኑፋክቸሪንግን ዘርፍ ለማስፋፋት መንግስት ማበረታቻ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ የተሰጠው መልስ ለግል ባንክ የምንሰጠው ገንዘብ የለም የሚል ነው፡፡ የግል ባንኮች ገንዘብ መሰብሰብ ያለባቸው ከደንበኞች ቁጠባ ነው የሚል ሃረግም አክለውበታል፡፡ በግሌ ያቀረብኩት ሃሳብ፤ መንግስት ለግል ባንኮች ገንዘብ ይስጥ ሳይሆን፤ መንግስት ከግል ባንኮች የሚወስደውን ሃያ ሰባት በመቶ ያቁምና እራሳቸው ብድሩን ለግል ሴክተር ይስጡ ነው፡፡ መቼም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ባይጠፋቸውም፣ አጠቃላይ አድማጩን ህዝብ ለማሳሳት በሚመስል መልኩ ጥያቄውን ወደሌላ አቅጣጫ መርተውታል፡፡ አሁንም የግል ተሳትፎ እንዲጎለብት የግል ባንኮች ተሳትፎ መኖር አለበት ብንልም አይሆንም ብለዋል፡፡ የግል ሴክተሩ ለኢኮኖሚው ሞተር ነው እያሉ ሞተሩ የሚነሳበትን ባትሪ በመንቀል እንዳይሰራ እያደረጉት ነው፡፡ የግል ሴክተሩ ቢሳተፍ ባይሳተፍ በሁለት አሃዝ ማደጋችን ግን ይቀጥላል፡፡

አንድ ጥያቄ አለኝ! መንግስት የዚች ሀገር እድገት ሊቀንስ የሚችለው ምን ምን ሁኔታዎች ሳይሳኩ እንደሆነ ሊገልፅልን ቢችል እኛንም ከመደናገር ያድነናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ይህ እቅድ እንዲሳካ ታሳቢ ተብለው የተቀመጡት ነገሮች በአብዛኛው በታሰበው መሰረት አልነበሩም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን እድገቱ በታሰበው መሰረት ቀጥሏል ...... የጉድ ሀገር!

Girmaseifu32@yahoo.com
ግርማ ሠይፉ ማሩ

No comments:

Post a Comment