Tuesday, August 5, 2014

ኢህአዴግ በድሆች ጉሮሮ ላይ ቁማር መጫወቱን ቀጥሎበታል፡፡ የደመወዝ ማሻሻያ ርካሽ የፓለቲካ ትርፍና ተግዳሮቱ

ምንሊክ ሳልሳዊ


***የደመወዝ ማሻሻያ ርካሽ የፓለቲካ ትርፍና ተግዳሮቱ….***
በድሆች ጉሮሮ ላይ ፓለቲካውን የሚያካብተው ኢህአዴግ በተቀጣሪዎቹ ላይ ቁማር መጫወቱን ቀጥሎበታል፡፡

ተቀጣሪው የኢትዮጵያ ህዝብም ባርነትን ወዶ መኖሩን ተያይዞታል፤ የሰውን ልጅ ከጫማህ ስር በባርነት ለማኖር ከፈለግክ ቤተሰብ መጦር ድሮ ቀረን እያዜመ በቤተሰብ የሚጦረው የዘመናችን የመንግስት ሠራተኛ አያድርሰው እንጅ ቢታመም ጉድ ፈላ! ያው ጤና አዳሙን፣ዳማከሲዩን፣ዝንጅብሉን አጥር ያፈራውን ሐረግ ሬሳ ይታጠናታል እንጅ እንኳንስ የግል ሆስፒታል በቀበሌው ያለ ጤና ጣቢያ ሔዶ በሐኪም ሊታይ አይችልም፤ በዓመት በዓል እንኳን ከመንግስት ሠራተኛ ቤት የልኳንዳ ፌስታል እንጅ የበግ ቆዳ የገባው በደጉ ዘመን ነበር፤ለመማር እራስን ለመለወጥ ገንዘብ ያስፈልጋል፤ከተማርክ ደግሞ ጥያቄ ማንሳትህ አይቀርም! የዛሬን ካልቸገረህ ስለ ነገህ ትሞግታለህ! ማኩረፊያ ካለህ ምሰህን አስከብረህ ለእራትህም ትተርፋለህ! ቅሉ ግን ከምሳ ባሻገር እንድትኖር አይፈለግም፡፡ ከምሳ ያለፈ እንድታስብ አይፈለግም! ሆድህ ከሞላ ቁንጣንህ ወንበር ያሰይሃል ተብሎ ይታመናል-በኢህአህዴግ ቤት! እራትህን እርግጠኛ ከሆንክ መታረዝህ ያሳስብሃል! ቁርሳቸውን ላላሟሹቱ ማሰብ ትጀምራለህ! ሌሎች መብቶችህም ትውስ ይሉህ ይሆናል! ከራስህ አልፈህ አገሬ ብለህም ትነሳ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሆድህ ይሞላ ዘንዳ አይፈለግም፡፡ ደንደስህ ከወፈረ ለማነቆ አይመችም! የኢትዮጵያ የተቀጣሪዎች የደመወዝ እስኬል ዝቅተኛ ነው ብለህ ማንሾካሾ አትችልም፤ አደሃሪ ጓደኛህ 
ይቺ አገር ከዚህ በላይ ደመወዝ ለመክፈል አቅሟ አይፈቅድም ብሎ በሐገርህ ፍቅርህ ስስ ጎንህ በኩል ዘልቆ ይሞግትና ዝም ያሰኝሃል!
 አዎ! ይኢ አገር የተትረፈረፈ ደመወዝ መክፈል ያቅታት ይሆናል፤ እነ እንቶኔ ከጓሯቸው እንደ ባህር ዛፍ የሚያበቅሉትን ህንጻ መስሪያ
 የሚያክል ደመወዝ አልተመኘህም! ከእርሀብና ከእርዛት፣ከጥማትና ድቆሳ የሚያላቅቅ ገንዘብ ግን ኢትዮጵያ መክፈል አይሳናትም፤
 ደግሞስ የመሬቷ ኢትዮጵያ ይፋ የምትሆነው ደመወዝ ላይ ብቻ ነው እንዴ? የኢትቪዋ ኢትዮጵያ የት ገባች?

ካርል ማርክስና የሶሻሊስት ኮሚዩኒዝም ፅንሠ ሃሳብ አራማጆች “ያላቸው” በ “ሌላቸው” ላይ ካፒታሊስቶች በመሆን ላባቸውን እና 
ደማቸውን በመምጠጥ በድሆች ሞት ላይ ጉልበታቸውን እያጠናከሩ ነው፤በላብ አደሩ ሞት ላይ ካፒታሊስቶቹ እስትንፋሳቸውን እያራዘሙ
 ነው የሚል ክስ ነበር ይዘው የተነሱት፡፡ እዚህ አገር ግን ካፒታሊስት የሆኑት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ኢህአዴጋዊው መንግስት ነው፤ በቀን
 ለስምነት ሰዓታት ሠርተህ መንጋጋዎችህ ሁሉ ምግብ ረግጠው አያድሩም፤ ጉንጮችህ በምግብ ተጨንቀው የበላህበትን 
አታስታውሰውም፤ በተንደላቀቀ ቢሮ ውስጥ በመንግስት ወንበር ላይ ስትሽከረከር ውለህ ማታ ቤትህ ስትገባ የሚጠብቅህ 45 ድግሪ 
ያዘመመ ቤት ነው፤ እሱንም ከአይጦች ጋር ተዳልበህ የምትኖርበት ነው፤ አልጋ ብርቅህ ነው፤ ያው ኬሻ በጠረባህ ነው፡፡

በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ መስራት በፈቃደኝነት ድህነትን ለመውረስ ዝግጁ መሆን ማለት ነው፡፡ የመንግስት ተቋማቶች 
ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ድርቅ ተመትተዋል፡፡ ተስፋ የቆረጡ፤በሙያቸው የማይተማመኑ ወይም ሙያ አልቦዎች፣ በሠራተኛው 
ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ያልሆኑ የእውቀት የክህሎት፣ የዝግጅት እና የተነሳሽት ድኩማኖች መናኸሪያ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ 
አማራጭ አጥቶ የመንግስትን ቤት ሙጥኝ ያለ ፈጻሚ እንኳንስ አገር ሊገነባና የአፍራሽነት ሚና ነው የሚጫወተው፡፡ መንግስት 
በክህሎት አልቦ እና በሙያ ለምኔ ፈጻሚዎች ተከብቦ እንዴትስ ህዝብን ማገልገል ይችላል? የግሉ ዘርፍ በሰው ኃይል አደረጃጀቱ 
በልጦት ከተገኘ መንግስት የግሉን ዘርፍ መምራት ቀርቆ መንግስት በግሉ ዘርፍ ይመራል፡፡ መጨረሻ ላይም ፓለቲካል ሙስናና 
እና የሐገር ምርኮ (State capture) ገቢራዊ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያችን የቁልቁለት ሩጫውን ተያይዘዋለች፡፡ ሙያ አልቦ ፈጻሚዎችን 
ተይዞ እንዴት ያለ መልካም አስተዳደር ሊኖር ይችላል? የእለት ጉርሱ የሚያቃዠው ፈጻሚን አሰባስቦ እንዴት አገርን ከሙስና 
ማዕበል መታደግ ይቻልል? ከእለት ጉርሱ ባሻገር እንዳያስብ የተደረገ ሎሌ ሆዱ ስለሚጠግብበት የስርቆት አጋጣሚ ከማሰብ 
አይቦዝንም፡፡ በሩ ተከፍቶ ሞሰቡ ሳይከደን ባገኘም ጊዜ ተደብቆ ማሻማዱ አይቀርም፡፡ መና አገኝበታለሁ ወዳለሁ ሁሉ ማጮለቁ 
አይቀርም፡፡ ድሃ ሎሌ ሆኜ እቀር ዘንዳ ጥረዋል በሚል ቀበጸ-ተሥፋነትም ድሃ ሊያደርጋቸው ከመጣርም አይታቀብም፡፡ በሐገሩ 
ጥቅም ላይ ደርሻ የሌለው ሎሌ “ሺ ቢታለብ ያው በገሌን” እያዜመ ወተት ከመስረቅና ከመድፋት አይቦዝንም፡፡ ለሆዱ ጩኸት 
መልሽ ያጣ ፈጻሚ እንዴት የተገልጋይ ጩኸት ሊሰማ ይችላል? ከቶስ እንዴ ልማታዊ የለውጥ ሃዋሪያ ይሆን ዘንድ ይከጀላል? 
የባለፉትን ሁለትና ሦስት አመታት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰራተኛ ፍልሰት በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ነው፡፡ 
ታላላቅ የሚባሉትና ከፍተኛ ደመወዝ ይከፍላሉ የሚባሉት መስሪያቤቶች ጭምር በዚህ አለመረጋጋት ሲናጡ ነው የከረሙት፡፡
አንድ ሺህ የዩኒቨርሲቲ ወጣት አድስ ምርቆችን ጥቅምት ላይ የቀጠረው መስሪያ ቤት ታህሳስ ላይ አንድ ሺህ አምስት መቶ 
ሆነው እየለቀቁበት የተቸገሩ ባለስልጣን መ/ቤቶች በርካቶች ናቸው፡፡ይህን ተጨባጭ መዋጥ ያቃታቸው አመራሮች ገባያው በሥራ 
ፈላጊ የሰው ኃይል ተጥለቅልቋልና የፈለገ ይልቀቅ እያሉ ሲያቅራሩ ነው የከረሙት፡፡


እንዳይሞት እንዳይሽር እያደረግክ አፉ ላይ የእለት ጉርሱን ጣል አድርግለት” የሚለውን መርሕ የሚከተለው ኢህአዴግ መርሑ
 የሰመረለት ይመስላል፤ ከእለት ጉርሱ ባሻገር እንዳይኖር ቅጽር አበጀህለት ማለት ነው፤ የእንጨት ሆነ የብረት ቀንበር ጫንከው በሆዱ 
ከማልጎምጎም ባሻገር አንዳች ሳይላወስ ሰጥ ለጥ ብሎ ይኖራል- ወርሐዊ ምንደኛ፡፡ኢትዮጵያዊው ተቀጣሪ “እረኛ ቢቆጣ ምሳው 
እራቱ ነውን” እያዜመ ማነቆውን ለሚያጠብቁበቱ የኢህአዴግ አመራሮቹ ታማኝ ሎሌ ሆኖ መኖርን ሙዱ አድርጎታል፤አበሻ ካርቶን 
ሙሉ ሐንድ አውት ጠግርራ ተመርቃ በአንድ ሽህ ስምንት መቶ ብር ትቀጠርና አንድ ሺ ሦስት መቶ ብሩን ኩሽና መሰል ቤት ትከራይበትና 
ቀሪውን አምስት መቶ ብር “ተመስገን ጽሐዩ መንግስታችን!” እያለች መኖሩን ለምዳዋለች፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቱ ተውሳክ ከወንበረኞቹ ወደ ህዝቡ በሰፊው ተዛምቷል፤ የደመወዝ ማሻሻያ ፕሮግራም ገና ይፋ ከመደረጉ 
ቤት ኪራይ፣ አስሰቤዛው፣ አልባሳቱና አገልግሎቱ ሁሉም በአንድ ጊዜ ዋጋቸው ጣሪያ ይነካል፡፡ አግባብ ያልሆነ ዋጋ ጨምረው ከፍተኛ 
ፕሮፊት ማርጅንን ከመሻት የተጨመረችዋን ደመወዝ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የነበረውንም አብረው ይወስዱታል፡፡ሕዝብ ራስ
 ወዳድ መሆን ሲጀምር የፓለቲካውም ቁማር ይሰምራል፡፡ ነጋዴው በአንድ ቀን አዳር ቢሊየነር መሆንን ሲመኝ፣ ቤት አከራዮች ቤተ 
ተርፏቸው ቤት ለሌላቸው እያከራዩ ቤት የሌላቸውን ደፍቀው ሌላ ጎጆ መቀለስ ካማራቸው ኢትዮጵያችን በቁሟ መፍረሷን አያበሰሩህ 


ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ መፍትሔ ነበረው፤ ችግሩ በደመወዝተኛው ሞት ላይ የፓለቲካው ቁማር መግዘፉ ነው እንጅ! የደመወዝ ማሻሻያ
 ተቀዳሚ አላማ ተቀጣሪውን የሕዝብ ክፍል ኑሮ ለማሻሻል ታስቦ መሆን ነበረበት፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው!! ሁለት መቶ ብር ለመጨመር 
የሁለት መቶ ሺህ ብር ጭማሪ ፕሮፓጋንዳ በመገናኛ ብዙሐን የሚለፍፉ የደመወዝ ማሻሻያ ስግብግብ ፓለቲከኞች የፓለቲካ ትርፍ
 ለማጋበስ ሽተው ያደረጉት ሴራ ነውና-“ሺ ቢታለብ ያው በገሌን” እንድታዜም ትገደዳለህ፡፡

የኢትዮጵያ ፓለቲከኛ ኢኮኖሚስቶች ባለ ባንክ ኪሶቹን የዘነጋ ተቀጣሪ ምንዱባንን መሰረት ያደረገ የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ
 ፓሊሲ ይቀምሩልሃል፤ ልክ የእኔና የእርሰዎን መኖር እየተፈታተነ ያለው የኑሮ ውድነት ምክንያቶቹ በርካቶች ናቸው፡፡
ከነዚህ አንዱ በርካታ ገንዘቦች በህብረተሰቡ እጅ ሲገቡ ብዙ ብሮች ትቂት ምርቶችን የማሳደድ አደጋ ይገጥማቸዋል፤
በዚህ ጊዜ መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በህዝቡ እጅ የሚገኙትን ገንዘቦች መጠን ለመቀነስ በርካታ መንገዶችን ቀይሶ 
መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ወደ ህዝቡ እየጎረፈ ያለውን የገንዘብ ጅረትም ቆጣሪ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ 
ይህ የኢኮኖሚክስ መርህ ነው፤ በርካታ ሐገሮች የሚተገብሩት! እንዳመታደል ሆኖ በአገራችን ግን ያለው ከዚህ የተለየ ነው፡፡
 በህዝቦች እጅ የሚገኝን በርካታ ገንዘብ መቀነስ አለብን ብለው ሲነሱ የኛዎቹ ፓለቲከኛ ኢኮኖሚስቶችና መሪዎች ትዝ የሚሏቸው 
በስሮቻቸው ያሉ ተቀጣሪ ምንዱባን ናቸው፡፡ከተቀጣሪው ደመወዝ ላይ የአባይ፣የምንትስ የምንትስ በሚል በመሸቃቀብ የዘጠና ሚሊዬን
 ሕዝብን በር በአስር ሚሊዬኖች መስከኮት ሊከርችሙ ይጥራሉ፡፡ለልማት የሚውለውን እንኳን ትተነው በአሻጥር ወደ ጥገኞቻቸውና
 የትርፍ አጋሮቻቸው የሚጎርፈውን የገንዘበ ፍሰት አጠናክረው የተቀጣሪን ደመወዝ በመሻቀብ የሞኒታሪ ፓሊሲን ገቢራዊ እያደረግን
 ነው ሲሉ ያላግጡብናል፡፡

የደመወዝ ማሻሻያ በኢትቪ ካልተለፈፈ ማሻሻያ ፕሮግራም አይሰራም የሚል የኢኮኖሚክስ ህግ አልተከተበም፡፡የደመወዝ ጭማሪው 
የተቀጣሪውን ኑሮ ለማሻሻል ታስቦ ቢሆን ኖሮ ውስጥ ለውሥጥ ለዚያውም የተለያዩ የሐገሪቱ ዘርፎችን በክላስተሮች ከፋፍሎ በሒደትና 
በወራት ከፋፍሎ የደመወዝ ማሻሻያውን ገቢራዊ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ግና የኛዎቹ የፈለጉት የሎሌዎቻቸውን ኑሮ በማድቀቅ 
ፍጹም ተገዢ ይሆኑላቸው የሰሩት ሴራ ነው፡፡ የደመወዝ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ሳይጠናቀቅ፤የእድገት ስኬሉ ሳይሰላ የረከሰ በፓለቲካን 
ትርፍ ከመሻት ገና በውጥን ላይ ትቂት ፓለቲከኞች በቤቶቻቸው ያወሩትን ለሚዲያ በማቅረብ ምርጫ 2007ን ከማሰብ የተሰራ 
ደባ ነው፡፡አገር በተጻፈ ስርዓትና ህግ ካልተመራች ፍጻሜው ይሔው ነው፡፡ በሚመለከታቸው አካላት ያልጸደቀን አሉባልታ 
ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በማዋል ምንደኞችን ለመርገጥ የተሰራ ሴራ ነው፡፡

እንግዲህ የኑሮ ውድነት መንስኤዎቹ ብዙ ቢሆኑም ዋናወናዎቹ ከምርት እጥረት ወይም (Supply shock)፣ከፍላጎት ማደግ
 እና ከስነ-ልቦና (Expectation) እንደሚመጣ ኢኮኖሚስቶቹ ይስማማሉ፡፡ ከሥነ-ልቦና ጫና ማለትም ኑሮ እንደሚወደድና እየተወደደ 
መሔዱን ተፈጥሯዊ የኢኮኖሚ ባህሪ አድርጎ ያመነ ህዝብ የተጠየቀውን ከመክፈል ውጭ ማቅማማት አይችልም፤ አቅራቢውም ይህችን 
እንደ ሽፋን እየተጠቀመ ሸማቹን እንደ አልቀት ከመምጠጥ አይታቀብም፡፡ የሸማቹን ልብ ለማረጋጋትና የመደራደር አቅሙን ለመጨመር
 መገናኛ ብዙሐን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኢኮኖሚስቶች ክትባቱ ሚዲያ ነው ይላሉ፡፡ ያለመታደል ሆኖ የኛ አገር ሚዲያዎች 
የተረትና የውሸት አባት በመሆናቸው አበሻ ገልብጦ ነው የሚሰማቸው፡፡ ገባያ ላይ ሁለት ሺህ ብር የሚሸጥን ጤፍ በመቶዎች 
ይነግሩህና “አይ ኢቲቪ-ቱልቱላ ሁላ!” እያልክ ወደ ሸመታህ ትቃናለህ፡፡መንገድ ላይ ተሰልፈው በልመና የሚያስቸግሩህ ገበሬዎች ዞረው
 በኢቲቪ ልማታዊ ባለሀብት ሆነው ቁጭ ሲሉ ኢቲቪ ያስኮመኩመናል፡፡እናም ወንድሞቼ ኢኮኖምክስ በሐበሻ ምድር ላይ ከሽፏል፡፡ 
ምንደኛ የእለት ጉሮሮውን ከማራስ ባሻገር ያሉ አጀንዳዎችን እንዳያስብ በማድረግ ሚሊዬን ምንደኞችን ደጋፊ የማድረግ ኢህአዴጋዊው 
ፓሊሲም ያለ አንዳች እንቅፋት ግስጋሴውን ቀጥሏል፡፡ባካችሁ በቃኝ!...

No comments:

Post a Comment