Monday, August 11, 2014

ለአንቺ ነው ኢትዮጵያ !

 ከእንግዳ ታደሰ


ከውሻ ተሻምቶ ለሚያድረው ህዝብሽ ነው ፣
ህዝብሽ እንዲጠግብ ሽቅብ ቁልቁል ያለው ፣ራሱን ረስቶ ህይወቱን የቸረው ፣
እድል እጣው ሆኖ በግፍ የታገተው፣
ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ! ልጅሽ የታፈነው ፡፡
በማድያት የኳሉሽ – ፊትሽን ያጠለሹሽ፣
ዉብ መልክ ገጽሽን አመድ ያለበሱሽ ፣
በብተና ሴራ ከምድር ሊያጠፉሽ ፣
ታጥቀው ለተነሱት ቅጥረኛ ልጆችሽ ፣
በነው እንዲጠፉ ከመላዋ ምድርሽ ፣
ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ! የባዘነው ልጅሽ ፡፡
ክራሞታችን እንዲህ ከሆነ – የወደዱትን አሳልፎ ፣
ምን ጠቀመ መማማሉ – አንገት ላንገት ተቃቅፎ ፡፡


የተረታን ከመሰለን በጉጅሌ ሽብር ታምሰን፣
በቀላሉ ሸብረክ ካልን ከመሰለን የተሸነፍን ፣
ያኔ’ ነው ጠላታችን የበለጠ እሚጀግን ፣
ጨካኝ ሆኖ የሚበላን አንድ ሳንቀር የሚውጠን ፡፡
በእንቶፍ እንቶፍ መሸታ ቤት – ወሬ ብቻ ከጠረቅን ፣
በኮማሪት ጡት ስር ታቅፈን ቤዛችንን ካወገዝን ፣
ኮዳ ሳንይዝ በመለኪያ ፣ የጦር መስመር ካሰመርን ፣
አማራጩን ሳናቀርብ ትችት ብቻ ካዘነብን ፣
ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ከበዛብን ፣
ያኔ’ ነው አንዳርጋቸው የሚያዝንብን ፡፡
ትከሻችንን አስፍተን ሸክማቸውን ከተሸከምን፣
እንዳጋሰስ ወደል ጌኛ መጫኛቸውን ያጥብቁብን
ሸክማችንን እናመቻች ጭቆናቸው ይርበብብን፣
አርማ አንስቶ መጓዝ ሳለ ፣ እጅ መስጠት ከመረጥን
ያኔ’ ነው አንዳርጋቸው የሚያፍርብን ፡፡

ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት ሽቅብ ቁልቁል ሲል መላ እድሜውን ለመስዋዕትነት ለሰጠው አርበኛ አንዳርጋቸው ፅጌ መታሰቢያ ትሁንልኝ 
ተጻፈች በ7-8-2014 ማድሪድ/ ስፔን በእረፍት ላይ ፡፡

No comments:

Post a Comment