Tuesday, August 12, 2014

የጸጋየ አየለ ገዳይ አሜሪካ ይገኛል

ደስታው አንዳርጌ (ዶ/ር)

ጸጋየ አየለ ይግዛው ይባላል። የ፴፬ ዐመት ባለትዳርና የልጆች አባት ነበር። ጎንደር ሆስፒታል ውስጥ በራዲዮሎጂስትነት ሲሰራ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር አባል ነህ በሚል ፖሊስ የሚያደርስበትን ወከባ ለመሸሽ ወደ ደብረማርቆስ ሄዶ በአንድ የግል ክሊኒክ ተቀጥሮ መስራት ይጀምራል። ነገር ግን የፈራው አላጣውም ታህሳስ ፱ ቀን ፩፱፻፺፱ (1999) ዓ.ም ከጠዋቱ ፪ ሰዐት ከ ፵፭ አካባቢ ወደስራ ሲሄድ ፖሊስ ያለፍርድቤት ማዘዣ ይይዘዋል። ደብረማርቆስና ባህርዳር እያመላለሱ ለጥቂት ሳምንታት ካንገላቱት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተዛውሮ ታሰረ። ማዕከላዊ እንደደረሰ ለበርካታ ቀናት ከፍተኛ ድብደባና ማሰቃዬት ደርሶበታል። በደረሰበት ድብድባ እጅግ ሲደክም ራስ ደስታ ሆስፒታል ተወስዶ እንዲታከም ተደረገና ሲያገግም እንደገና ወደ ማዕከለዊ ተወስዶ ዘግናኝ ግፍ ተፈጸመበት። ጥፍሮቹ ተነቀሉ፤ የግራ ጆሮው፣ ሁለቱም እጆቹ፣ ብልቱ፣ አይኖቹ ሁሉ ከጥቅም ውጭ እስኪሆኑ ድረስ አሰቃዩት። እንዲህ አርገው ካሰቃዩት በኋላ በድብደባ ሽባ የሆኑትን እጆቹን በካቴታ ታስሮ ያድራል። ሲደክም እያሳከሙ ይደበድቡት ነበር። እንዲህያል ግፍም ይፈጸማል። ይህ ሁሉ አብረው ከሚሰቃዩት ታሳሪወችና ከቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን ከጸጋየ ከራሱ ማረጋገጥ ተችሏል።


ፖሊስ በጸጋየ ላይ ያው የተለመደው አይነት ክስ አቅርቦ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ለ፯ ጊዜ ያህል የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ተፈቅዶለት ነበር። በመጨረሻ ግን ለስሙ የሚሆን እንኳን ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻለና ጸጋየም ፍርድቤት መቅረብ የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ ሲቀርብም በድብደባ አካሉ ሁሉ በልዞ ስለሚሆን ፍርድቤት መዝገቡን ዘጋው። የሚገርመው ግን ፍርድቤቱ መዝገቡን ሲዘጋ ከህግ ውጭ ታስሮ የሚሰቃየውን ታሳሪ እንዲፈታ ትእዛዝ አልሰጠም። ስለሆነው ጸጋየ ሳይፈታ በእስር እንዳለ በደረሰበት ድብደባ የካቲት ፳፮ ቀን ፩፱፻፺፱ (1999) ዓ. ም ህይወቱ አለፈ። የጸጋዬ አስከሬን ወደ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ የተደረገለት ቢሆንም በወቅቱ ቤተሰቦች የምርምራ ውጤቱ ምን እንደሆነ አልተነገራቸውም።

ይህ ሁሉ ግፍ የተፈጸመው በስም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በተግባር ግን ዋና አዛዥ በነበረው ተስፋዬ ምሬሳ በሚባለው አረመኔ ትእዛዝ ነው። ተስፋዬ ምሬሳ አሁን አሜሪካ ውስጥ እንደሚኖር ይታወቃል። ተስፋዬ ምሬሳ በጸጋየ ላይ የፈጸመው ግፍ ይህ ብቻ አይደለም። በጸጋየ ላይ ይደርስ የነበረውን ሰቆቃ ሲከታተል የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)የደረሰውን ግፍ አስመልክቶ መግለጫ ሲያወጣ ተስፋዬ የኢሰመጉ ሃላፊዎችን ከማስፈራራት አልፎ ጸጋየ የሞተው በድብደባ ሳይሆን በኤድስ ነው የሚል ‘የማስተባበያ’ መግለጫ ማውጣቱን አውቃለሁ። በነተስፋዬ ምሬሳ ቤት አንድን ሰው አሰቃይቶ ከመግደል በላይም ግፍ አለ።

የዚህን ጉዳይ ዝርዝር ከቀድሞው ኢሰመጉ ፺፱ ነኛ ልዩ መግለጫ ማግኘት ይችላሉ።

ምንጭ /EthiopianReview.com/

No comments:

Post a Comment