ጌታቸው አበራ
ይድረስ ለወንድሜ “ለማላውቅህ”፣ ባረመኔ ገራፊዎች እጅ ለወደቅኸው፣
በኮረንቲ ሽቦ ገመድ – መላው አካላትህ ለሚላጠው፤
ከጭለማው የግፍ “ቻምበር” – ከሰቆቃ መፈጸሚያው፣
የስቃይህ ጣር ዋይታ – ላለም ጆሮ ለተሰማው።
ከህመምህ ስታገግም – ላንዲት ቅጽበት ብጠይቅህ፣
ምንስ ይሆን “ሃጢያትህ”? በነሱ ዐይን “ጥፋትህ”?
እኔማ ምን አውቄ?
ስቃይህን ሰምቼ እንጂ መጨነቄ፤
ግን፣ ግን…፣
ከሚያቃትተው ድምጽህ ዋይታ፣
እስኪ ልገምት …”መላ-ልምታ”፣
(በመዝገበ-ማሕደር ተከትቦ- ዓለም የሚያውቀውን እውነታ)፤
…ቆዳህን ባኮርባች ሲልጡ – ስጋህን በብረት ሲያቃጥሉ፣
አጥንትህን ፍቀው ሲግጡ – በስ ብልት ጠርሙስ ሲያንጠለጥሉ፣
አደንዛዥ መርፌ እየወጉ – መርዛቸውን በህዋሳትህ ሲረጩ፣
በቀዝቃዛ ውሃ እየደፈቁ – ከደረቅ ግድግዳ ጋር ሲያጋጩ፣
ጥፍርህን እየነቀሉ – ጸጉር-ጺምህን ሲነጩ…፣
በፈላ ዘይት እየጠበሱ፣
ዘቅዝቀው በመስቀል እንቅልፍ እየነሱ፣
የጸያፍ ስድብ ውርጂብኝ – የጭለማ ክፍል ደባ፣
የአእምሮ ስቃይ በትር – የስነ-ልቦና ሰለባ…፤
ለምኑ ይሆን የተጨነቁ? – አሰቃይቶ “ቃል” ለመቀበል?
“መረጃ” ለማሰባሰብ? – “ፍርድ ቤት” የሚቀርብ ለይምሰል?
እንደዚያማ እንዳልገምት – ፍርድ ቤቱ በጃቸው፣
በቀጭን ትዕዛዝ የሚወስኑ – ፍርደ-ገምድል ዳኞቻቸው፤
እና ታዲያ ለምን ይሆን? በሰው ልጅ ገላ እንዲህ መጨከኑ፣
ያገር-ልጅ በወንድሙ ላይ – ጭራቅ፣ አውሬ መሆኑ?!
… ቀውስ ነው ቂም-በቀል – ያገር-ወዳድ ቅስም ለመስበር፣
በዘረኝነት ጎዳና – ዝንተ-ዓለም ለመዘወር፤
እኩይ መንፈስ ጥላቻ ነው – የበታቸኝነት ስሜት ሕመም፣
ባለም መድሃኒት እማይድን – ነቀርሳ እማይታከም፤
ይድረስ ለወንድሜ “ለማላውቅህ” – ለእምዬ ልጅ የአንዷ፣
ለጋራ እናታችን፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ስትል እምትቀበል ፍዳ፣
እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጥህ – ከበላዔ-ሰብ መንጋጋ አላቆ፣
ለመልካሙ መጪ ጊዜ ያብቃህ – የተሰቃየህላትን ሀገር ጠብቆ!
No comments:
Post a Comment