Monday, July 14, 2014

መለስ ሰርቶ ያልጨረሰው አሻንጉሊ




ለኃይለማርያም ደሳለኝ የተጻፈ ሽሙጥ

ይህን ለሕዝብ ጆሮ ብሎ መጻፉ በራሱ ሰቅጣጭ ቢሆንም አንዳንዴ ስቆ ለማለፍም መጋራት ይበጃል እናም ለሳቸው እንዲህ ብዬ ብነግራቸው ጥሩ ነበር ያልኩትን ለናንተም አካፍላለሁ።

አቶ ሐይለማርያም ሆይ ስለ እርስዎ ማፈራችን እስከመቼ ይቀጥላል? ገና መናገር ሲጀምሩ ስቅቅ ይለኛል። ተናግረው ሲያበቁ ሙሉ ሰው መሆንዎንም ማመን ያቅተኛል። እንዲያውም አሁን አሁንማ መለስ ጀምሮ በወጉ ያልጨረሰው አሻንጉሊት ይመስሉኛል። መለስ ኮርጀን ገልብጠን ቢል ያምርበታል መገልበጥም መኮረጅም ማስመሰልም ማድበስበስም የክብር የዶክትሬት ዲግሪ የሚያሰጠው ብልጥ ሰው ነው በቃ ሞላጫ አራዳ የሚሉት አይነት ነው።

እርስዎ እግዜር ሲፈጥርዎ የሞኛ ሞኝ ገጽታ የየዋህ ሰው ቆዳ ይዘው የመገለባበጥ ችሎታው ሳይኖርዎት እንደልብ የሚዘግኑት የቃላት ቀረጢት ሳይዙ ጋዜጠኛ ፊት ቀርበው በማትረባ ጥያቄ ላብ ላብ ሲሎት ማየት እንዴት አሳዛኝ እንደሆነ ቢያውቁ ደግ ነበር።

በሚናገሯቸው ቃላት የእውቀትዎ ልክ ብቻ ሳይሆን የማስተዋል ብቃትዎ የብልጠትዎ መጠን ፍንትው ብሎ ይታያል እናም ያሳፍራል። እውነቴን ነው የምሎት በጣም ያሳፍራሉ። እኚህ ሰው እንኳን የተማሩ በትምህርት ቤት በኩል ያለፉ አይመስልም እያሉ ሰዎች ቢያወሩስ እንዴት ይፈረዳል። አረ ጥሩ አይደለም ለመሆኑ መልሰው ቃለመጠይቅዎን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? ምናልባት እኮ የቢቢሲን ጋዜጠኛ ልክ ልኩን ነገርኩት ይሉ ይሆናል ቂ ቂ የቂል ነገር።

እውነቴን ነው የምሎት እርስዎ ድንገተኛ መገጣጠም ካልሆነ በቀር ፖለቲካ በደረሰበት ሊደርሱ አይገባም ነበር። “አህያም ቢሆን በኔ ያመነ ኢሕአድግ ይሆናል” እንዳለው ጌታ መለስ እርስዎም ጠቅላይ ሆኑና የውርደት ቀንዎ መሽቶ ይነጋበታል እንጂ። ታድያ ከመለስ መማር ሲገባዎ የብልጦች ብልጥ የመሰሪዎች መሰሪ ከሆነ ሰው ልኮርጅ ብለው እማይሆን ገደል ላይ ተንጠለጠሉብንና ተሳቅቀን አለቅን።

አንዳርጋቸው በኤርትራ መሬት ሊገደል ሲል የርስዎን ይሁንታ የጠየቀ የለም። ተይዞ አዲስ አበባ ሲመጣ እርስዎ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የአንድ ጊቢ የጥበቃ ሰራተኛ ወጪና ገቢውን የማየት እድል አለው የቤት ሰራተኛ ደግሞ ጓዳ ጎድጓዳውን የማወቅ እድል አላት እርስዎ ከነዚህ ከአንዳቸው እንኳ ያነሱ ሰው መሆንዎን ለመገንዘብ ያለመቻልዎ ለምን? ለነገሩ ስሜትዎን ገድለው ሰብዕናዎን ሽጠው የሚያድሩ ስለሆነ ግድ የሎትም። እኔ ግን ስለ እርስዎ ግድ ይለኛል። መዋረድ ይብቃዎ! መጫወቻስ መሆን ምን በወጣዎት ለየትኛው ዓለም? ከንግዲህ ይህ አለም ፍጹም ቤቴ አይደለም ብለው የዘመሩ ሰው አይደሉም እንዴ? ነው ወይስ እሱም ከፈረንጆች የተኮረጀ መዝሙር ስለሆነ ነው የዘመሩት። በኢየሱስ ስጋና ደም እንጂ በድሃ ደም ታጥበው ዘለዓለማዊ ህይወት እንደሁ አያገኙ።

እኔ እንደሰማሁት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሕንድ ድረስ ዘልቀው ተምረዋል ኮሌጅ ውስጥም ሰርተዋልና ኩረጃ የሚያፍሩበት እንጂ የሚመጻደቁበት ነገር አይደለም። አሁንማ ሳስበው እነ ካራቱሪን ከሕንድ ያመጡትና ባለመሬት ያደረጉት የኮረጁበትን ውለታ ለመክፍል ይሆን እንዴ? ማለት ጀምሬአለሁ። ቃል በቃል ገልብጠን ወሰድን ብሎ መለስ ሲናገር ቦታ ይመርጣል። ፓርላማ እነዚያ እሱ ፈገግ ሲል በሳቅ የሚፈርሱ ሲቆጣ የሚያለቅሱ የፓርላማ አባላት ፊት ስለተናገረው ትክክል የሆነ ይመስል ተመሳሳይ ነገር ይዘው ቢቢሲ ላይ አንተንም ቢሆን ዋጋህን እሰጥሃለሁ ብለው ሲናገሩ ከፊትዎ የሚያዩት ጋዜጠኛ አባንግ ነው ብለው የጠረጠሩ ይመስላል።                                                               

እንደ ማነጻጸርያ ሃሳቡን ከእንግሊዝ ተውሰን ከሀገራችን ሀኔታ ጋር አገናዝበን ይህንን አደረግን ቢባል አንድ ነገር ነው። እንዴት ሆኖ ነው የእንግሊዙን ስለገለበጡ ትክክል ነን ሊሉ የሚችሉት። የእንግሊዝ ስለገለበጡ አፈፃጸሙ አተረጓጎሙ አተገባበሩ ሁሉ ትክክል ይሆናል ያለውስ ማን ነው? ይህ እኮ እርስዎን ያለውድድር ከቂልነት ወደ ጅልነት የሚወስድ የአገላለጽ ስልት ነው። መለስ ይህን ሰምቶ ሊተርቦት ቢፈልግ ሊል የሚችለውን ሳስብ ሳቄ ይመጣል። ከአማርኛ ተረት ኮርጆ ሲሉ ሰምታ ዶሮ በገመድ ታንቃ ሞተች ይሎት ነበር። እኔ ግን በኩረጃ ስለማላምን አዲስ ተረትና ምሳሌ ፈጥሬ “እንደ መለስ በሞከረ ምላሱ ተሳሰረ” እላለሁ፡

ሕገመንግስቱ እንዳለ ከካናዳ ተኮርጆ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ እንዳለ ቃል በቃል ተገልብጦ እርስዎ ራስዎ ከመለስ ተኮርጀው እንዴት ይዘልቁታል? በእርስዎ የቂል መልስ ብቻ የፈጣሪዎን የመለስን አጭበርባሪነት እያጋለጡ ነውና የወያኔ ሰይፍ እንዳይከትፍዎ በጣም እፈራለሁ። ጌታ (የርስዎን ጌታ ባላውቅም) ብቻ ጌታ ይጠብቅዎ። አራት ነጥብ ብዬ ምክሬን እጨርስ ነበር። 

No comments:

Post a Comment