Thursday, July 17, 2014

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታላቅ እህት በ24 ሰአታት አገር ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ


ሐምሌ ፲(አስር)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለሰአታት በቁም እስር ላይ የነበሩት የታዋቂው ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ታጋይ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታላቅ እህት ወ/ሮ ብዙአየሁ ጽጌ
የወንድማቸውን ጉዳይ ለመከታተል በሚል ከ10 ቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ቢያመሩም፣ ከትናንት በስቲያ ደህንነት ጽ/ቤት  ከተጠሩ በሁዋላ አገሪቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።
በታዘዙበት ሰአት ለመመለስ እንደሚቸገሩ የተናገሩት ወ/ሮ ብዙአየሁ፣ የ 24 ሰአት ጊዜ የጊዜ ገደብ ከተሰጣቸው በሁዋላ ዛሬ ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል።  ወ/ሮ ብዙአየሁ የአቶ አንዳርጋቸውን
ቤተሰቦች በመወከል ጉዳዩን ለመከታተል በሚል መሄዳቸውን ከቤተሰቦች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢህአዴግ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ የእግር እሳት እንደሆነበት የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። አቶ አንዳርጋቸው የህዝቡ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆናቸውና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግንቦት7 ዝናም
ከምንጊዘውም በላይ በመጨመሩ የገዢውን ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን እያበሳጨ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ በአገር ውስጥም በውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን  አሁንም በተከታታይ ስልኮችን እየደወሉ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።
በፐርዝ አውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ከእንግሊዝ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለቆንስላው ላቀረቡት ጥያቄ የፐርዝ የእንግሊዝ የቆንስላ ሃላፊ፣
አገራቸው የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየተከታተለችው ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል።
በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በላኩት ደብዳቤ የአቶ አንዳርጋቸው መታፈን ” ወያኔ  ፍጹም አወሪነቱን ያሳየበት እና ዘላአለም የነጻነት ታጋዮችን ለማስፈራራት እና ከትግሎ ሜዳ ለማስውጣት
የተጠቀመበት የትእቤት ስራ ነው። ” መሆኑን ያሳያል ካሉ በሁዋላ፣ የተወሰደው እርምጃ ህዝቡን ለትግል እንደሚያነሳሰው ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው ማእከላዊ እስር ቤት እንዲታሰሩ የተደረጉት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የድርጅቱ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሃላፊ

አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤት ሰብሳቤ አቶ የሽዋስ አሰፋ እንዲሁም አረና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚና ታዋቂ ጸሃፊ መምህር አብርሃ ደስታ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣
ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። አንድነት ፓርቲ የተያዙት ሰዎች በ48 ሰአታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን በመግለጽ ክስ መስርቶ ነበር። ይሁን እንጅ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

No comments:

Post a Comment