Thursday, July 17, 2014

“ጎንደር ቤተ መንግስት ውስጥ ኦሮሚኛ ቋንቋ ይነገር ነበር”


"ኢትዮጵያዊነት ፍፁም የተደባለቀና የተቀላቀለ ነው"                 ፕ/ር ማሞ ሙጬ

በተለያዩ ድረ-ገፆች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚያንሸራሽሩት ሃሳብ ይታወቃሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያኒዝም፣ ስለ ፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ምልከታዎችና ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተሰሚነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ምሁራን አንዱ ናቸው ፕ/ር ማሞ ሙጬ፡፡ ሰሞኑን ጐንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 60ኛ አመት በዓል ሲያከብር “Towards Innovative A frica: The Significance of Science, T echnology, Engineering and Innovation for Sustainable Development” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በአሁን ሰአት በደቡብ አፍሪካ ሊዋኔ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ባለፈው ሳምንት በጐንደር ሳለ ከፕ/ር ማሞ ሙጬ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ምንድን ነው?

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተጀመረው በአሜሪካ ነው፡፡ ከዚያ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ቅኝ ወደተያዙ የአፍሪካ ሃገሮች ተዛመተ፡፡ እነ ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ናይጄሪያ... ወደ መሳሰሉት ሃገሮች ነው የተስፋፋው። የመስፋፋት ማዕከላት የነበሩት ደግሞ ቤተ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ቤተ-ክርስቲያኖች የሃይማኖት አስተምህሮ ዘረኝነት ይደርስባቸው ነበር፡፡ ያንን እንዴት እንቃወመው ብለው ሲያስቡ ነው የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ የመነጨው፡፡ ነጮች ሲሰብኩ ጥቁሮችን የሠይጣን ምሳሌ፣ ነጮቹን የመላእክት አምሳል አድርገው ነበር። ነገር ግን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅስ ስታይ ነጮቹን የሚወክል ስም የለም፡፡ 
ኢትዮጵያ የጥቁሮች ሃገርን ብቻ ነው የሚጠቅሰው፡፡ እናም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲል እግዚአብሔር ጥቁሮችን ይሰማል ማለት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች ለተጨቆኑ የጥቁር ህዝቦች “ኢትዮጵያን ማኒፌስቶ” የሚል እ.ኤ.አ በ1820 አወጡ። እነ አሜሪካና ሌሎች የበለፀጉት ሃገራት የስጋ ምግብ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ግን የመንፈስ ምግብ ሰጠች ማለት ነው፡፡ በዚህ ከሁሉም ትበልጣለች፡፡ በአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴ የተቋቋመው በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መነሻነት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የእንቅስቃሴ አራማጆች በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የወደቁ ነበሩ፤ በዚህም ታስረዋል ተገድለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት በዘርና በቋንቋ የሚለካ አይደለም፡፡ ሰዎች የመጣባቸውን ችግር ለመቋቋም ባደረጉት ትግል፣ ባገኙት ውጤትና ስኬት ውስጥ ያለፈ ፍልስፍና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የብሄር ትርጉም ያለው አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነትን ከዘር ጋር :- ከአማራ፣ ከትግሬ ከጉራጌ ጋር ወዘተ ያያይዛሉ፤ ነገር ግን ይሄ የተሳሳተ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከትግል፣ ከስኬትና ከተገኙ የትግል ድሎች ጋር የተያያዘ ፍልስፍና ያለው ነው፡፡

ጥናትዎን ሲያቀርቡ፣ “ወደ ምዕራባውያኑ የሄደው ሁሉ የኛ ነገር ነው፤ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም” ብለው ነበር፡፡ ምን ለማለት ነው?
እኛ ሁሉም ነገር አለን፡፡ ቋንቋው፣ የስነ ህንፃ ጥበቡ፣ ስነፅሁፉ... ሁሉም አለን፡፡ ግን የራሳችንን ትተን ሌላውን ወደ መኮረጁ ገባን፣ ኩረጃ ጥሩ አይደለም፡፡ አወዛግቦናል። ሁሉንም ሚስጥራችንን የጥንት ኢትዮጵያውያን ተንትነው አስቀምጠውልናል፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ሚስጥር፣ የቀንና ሌሊት ሚስጥር የመሳሰሉት፡፡ በአቡሻከር እስከ 15 እና 22 ፕላኔቶ አሉ የሚል ተፅፏል፡፡ እኛ 9 ፕላኔቶች አሉ ተብለን ነው የተማርነው፡፡ አሁን ፈረንጆቹ 13 አድርሰዋቸዋል፡፡ እንግዲህ እኛ በመደበኛ ትምህርት ባንማረውም የቀደሙት ግን 22 ፕላኔቶች አሉ ብለው በአቡሻከር አስቀምጠዋል፡፡ አሁን እኔ ፕሮፌሰር ተብዬ በድጋሚ 13 ፕላኔቶች አሉ እየተባልኩ ልማር ነው ማለት ነው፡፡
ማንዴላ ከእስር ቤት ሲወጣ ነው ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው፡፡ ማንዴላ በወቅቱ ምን አለ አሉ? ለአቶ መለስ እና ለአቶ ኢሳያስ ስልክ ደውሎ “እንዴት አንድ ህዝብ ትከፋፍላላችሁ እኛ ከአውሮፓ የመጡ አፍሪካኖችንና ከአፍሪካ የተፈጠሩ አፍሪካኖችን አንድ እያደረግን፣ ለእናንተ አንድ የሆነውን ህዝብ እንዴት ትለያያላችሁ”? ብሏል ይባላል፡፡ በወቅቱም አቶ መለስ እና አቶ ኢሳያስ አንደኛቸው ፕሬዚዳንት አንደኛቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምክር ለግሷል፡፡ አገሪቱ ሳትገነጠል ማለት ነው፡፡ ግን አልተቀበሉትም፤ መከፋፈሉ መጣ፡፡
እኔ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስሄድ፣ አንድ ደስ ያለኝ ነገር ምርጫ ሲያደርጉ ማንም ይመረጥ ዋናው የምርጫው ሂደት ውጤታማ መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ወገን ተጠቃሁ አይልም፡፡ ለምሳሌ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መሪ ብዙዎቹ አይወዱትም ግን ምርጫው ከወገናዊነት የፀዳ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሂደት አምስት ጊዜ ሰላማዊ ምርጫ አድርገዋል፡፡ እኔ በዚህ በጣም እኮራባቸዋለሁ፡፡ ነጮች ጥቁርን ሰይጣን ነው እንጂ ሰው አይደለም ይሉ


ነበር፡፡ እነ ማንዴላ ያንን ችግር በግጭት ሳይሆን በእርቅና በሰላማዊ መንገድ ነው የፈቱት፡፡ አሁን ከአፍሪካ ሃገራት መካከል እነ ቻድ፣ ማሊ፣ ሊቢያ ሌሎችም በግጭት ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህ ሃገሮች የደቡብ አፍሪካን ፈለግ ተከትለው ችግራቸውን ቢፈቱ ህዝባቸው ምንኛ በታደለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ለግጭቶች መላ ሲፈለግ በመገዳደል ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ በመናናቅ፣ በመዘላለፍ፣ ባለመተማመንና በውይይት ቢሆን ሃገርን በማስበለጥ፣ በመረዳዳት፣ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና በመወያየት መሆን አለበት፡፡ እኛ የፈለግነው ወገን ሥልጣን ካልያዘ ሞተን እንገኛለን የሚለው አስተሳሰብ መለወጥ ይኖርበታል፡፡

በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ይካሄዳል? ከምርጫው ምን ይጠብቃል?
ምርጫው እግዚአብሄር ታክሎበትም ቢሆን ንፁህ መሆን አለበት፡፡ ንፁህ ከሆነና ያ ባህል ከተፈጠረ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካዎች ይሄን ማድረግ ችለዋል፡፡ በእነሱ እየቀናሁባቸው ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ዙማን ብዙዎች አይወዱትም፡፡ ኢኮኖሚያው ላይ ጥያቄ አለበት፤ ነገር ግን መርጠውታል፡፡ ዋናው ማን ተመረጠ የሚለው ሳይሆን ሂደቱን ሰው ማመን አለበት፡፡ ንፁህና እንከን የለሽ ነው ብሎ ከልቡ ሊቀበለው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ምርጫ አያስፈልገንም፡፡
የዳያስፖራው ፖለቲካ ለዚህች ሃገር ባለው ፋይዳ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?
ከቅንጅት በፊት እዚህ ሃገር መጥቼ ነበር፡፡ ገጠር ድረስ በበቅሎ ሄጄ አይቸዋለሁ፡፡ በወቅቱ የገጠሩ ሰው ሁሉ ስለምርጫ በሚገባ እንዳወቀ የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በጣም ደስ ይላል ብዬ ተስፋ አድርጌ ወደ መጣሁበት ተመለስኩ፡፡ ከምርጫው በኋላ ግን የሆነው አሳዛኝ ነው፡፡ በወቅቱም በፃፍኩት ፅሁፍ፤ እንዲህ ያለ እድል ተገኝቶ እንዴት እናበላሸዋለን ብዬ ተቆጭቻለሁ። ኢትዮጵያ አንዳች ነገር እንዳጣች ተናግሬያለሁ፡፡ በውጪ ሃገር የተለያዩ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ግን በጣም የተበጣጠሱ፣ በአንድነት ተቀናጅተው ሃይል መሆን ያልቻሉ ናቸው፡፡ በሃገራችን ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ማምጣት አለብን የሚለው አስተሳሰብ ቢዳብር ጥሩ ነው። እኔ ለኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ነው የምመኘው፡፡

በዳያስፖራው አካባቢ የከፋ ዘረኝነት ይራመዳል ይባላል፡፡ እርስዎም በፅሁፍዎ ይሄን ነገር በተደጋጋሚ ይገልፁታል፡፡ የዚህ የዘረኝነት አንድምታው ምንድን ነው?
አንድ ጓደኛ አለኝ፡፡ ከሱ ጋር ሆነን አንድ ጊዜ የብሄራዊ መግባባት መድረክ ፈጠርን፡፡ ሁሉንም ብሄሮች የብሄር ፖለቲከኞች ጠራን፤ ኦነግን ጨምሮ፡፡ ግን ለመወያየት ከባድ ነበር፤ ዘረኝነት አይሎ አስቸገረን። ዘረኝነታቸው የእውነት ይሁን የይስሙላ አላውቅም፡፡ እኔን “የግራዚያኒን ሃውልት ለምን ትቃወማላችሁ? የአፄ ምኒልክ እያለ” ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ ተናድጄ “እንዴት አፄ ምኒልክን እንደዚህ ትላላችሁ” ብዬአቸዋለሁ። አፄ ምኒልክ ለአፍሪካ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ለአፍሪካውያን ድል የአፄ ምኒልክ እጅ አለበት፤ እሳቸውን ማጥቃት ማለት ጠቅላላ ኢትዮጵያን ማጥቃት ነው ብዬ ተቃውሜያለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ፅንፍ የያዙ አለመግባባቶች ይታያሉ፡፡ ግን ሰው ከዚህ ወጥቶ በውይይት መግባባትን ቢለምድ ጥሩ ነው፡፡ በአንድ የሆነ መላ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የዘር ፖለቲካ ብትወጣ ጥሩ ነው፡፡

ይሄ በቅርቡ እውን የሚሆን ይመስልዎታል?
አሁን እንግዲህ እዚህ የምትኖሩት ናችሁ ይሄን የምታውቁት፡፡ እኔ ውጭ ነው የምኖረው፡፡ ነገር ግን የዘር ፖለቲካ አይጠቅምም የሚለው አቋሜ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነት ብቻ ይበቃል፡፡ ወደ ታች ወርዶ በቋንቋ ምናምን መከፋፈሉ አያዋጣም፡፡ ዋናው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶቹ መጠበቃቸው ነው። ቋንቋ የሰውን ልጅ ሊከፋፍል አይገባውም፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ 11 ያህል ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት ይውላሉ፡፡ በእነሱ ዘንድ ቋንቋዎቹ ከመግባቢያነት ያለፈ ትርጉም የላቸውም፡፡ እኔ አሁን ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛ፣ አማርኛ... የሌሎች ቋንቋዎችን ሙዚቃዎችም ስሰማ ደስ ይለኛል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አማራ ብዬ ራሴን የምነጥለው፡፡ በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ማለት ምን ማለት ነው? እኔ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ መብቶች በሙሉ በህግ ጥበቃ ከተደረገላቸው በቂ ነው፡፡ እኔ አሁን ማሞ ሙጬ ነው ስሜ፡፡ አላውቅም አባቴ ኦሮሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ጎንደርን ለረጅም አመታት አስተዳድረዋል፡፡ ጎንደር ቤተ መንግስት ውስጥ ኦሮሚኛ ቋንቋ ይነገር ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍፁም የተደባለቀና የተቀላቀለ ነው፡፡
የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምን ያህል አፍሪካን ያስተሳስራል ይላሉ?
በዚህ አመት በፓን አፍሪካኒዝም ላይ መፅሃፍ ላወጣ እያዘጋጀሁ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነትም ባለፈ አፍሪካዊነት ላይ አስቀድመን ብንንቀሳቀስ ለእኛም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልድ ድል ነው፡፡ ህዝቡ የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሃሳብ ቢረዳ፣ ሌሎች አፍሪካውያን በፊት ከሚሰጡን ፍቅር የላቀ ፍቅር ይሰጡን ነበር፡፡ አሁን ያሉት

ፖለቲከኞች በዚህ መንፈስ እንዲራመዱ እግዚሃር ይርዳቸው፡፡ ከዘረኝነት ወጥተው በኢትዮጵያዊነት እና
በአፍሪካዊነት እንዲያስቡ እንፀልይላቸዋለን፡፡
በመንግስት በኩል ኢኮኖሚው እያደገ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ግን ዕድገቱ ህዝቡን ከድህነት አላወጣውም የሚል ትችት ይሰነዘራል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
በኢኮኖሚ እድገት ብሄራዊ ገቢን ማብዛት ብቻውን ጥቅም የለውም፡፡ ሰዎችን በማፈናቀል መሬት ለባዕድ በመስጠት የሚመጣ እድገት ጥሩ አይደለም፡፡ እድገት ማለት የህዝቡን ህይወት መቀየር ሲችል ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ካልተፈጠረ እድገት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ የህዝቡን ህይወት መቀየር መቻል አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ጥሩ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ማህበራዊ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች ይሄ ይጎድላቸዋል፡፡

ብዙውን ጊዜ በውጭ እርዳታ ላይ ስለሚንጠለጠሉ ያመኑበትን ፖሊሲያቸውን ትተው በለጋሾች ለመመራት ይገደዳሉ፡፡ ሌላው መኮረጅም ጥሩ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከቻይና መማር ያለብን እንዴት ጎበዝ እንደሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የራስን የቤት ስራ መስራት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ስንመለከት፣ አንድም ዜጋዋ መራብ አልነበረበትም፡፡(ርእሱ የተቀየረ) 

No comments:

Post a Comment