የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ይሻሻል ብለዋል
ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት የተፈረደባቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል
41 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፕሬስ ነጻነት አቀንቃኞች፣ አለማቀፍና ክልላዊ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና የሙያ ማህበራት መንግስት በቅርቡ የሽብርተኝነት ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞችና የዞን 9 ጦማርያን በአፋጣኝ እንዲፈታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከትናንት በስቲያ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ብሉምበርግ ኒውስ ዘገበ፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19 ምስራቅ አፍሪካ፣ ሲቪል ራይትስ ዲፌንደርስ፣ ወርልድ አሊያንስ ፎር ሲቲዝን ፓርቲሲፔሽን፣ ፔን አሜሪካና የመሳሰሉት አለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ መንግስት ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን በሽብርተኝነት እየከሰሰ ለእስር መዳረጉን መቀጠሉ ያሳስበናል፣ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ መገታት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሶስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማርያን ሶስት ወራት ለሚሆን ጊዜ ይህ ነው የሚባል ክስ ሳይመሰረትባቸው ያለአግባብ በእስር ላይ መቆየታቸውንና አንዳንዶቹም በምርመራ ወቅት እንግልት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን የጠቀሰው ደብዳቤው፣ ይህም አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡