Wednesday, February 20, 2013

የዳውሮ ሕዝብ ያካሄደው መራር ትግልና ውጤቱ፤



Yenesew Gebre from Dawro-Waka Ethiopiaበደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የዳውሮ ዞን ሕዝብ ለሕወሀት መራሹ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበርና ሕዝቡ ላቀረበው ጥያቄ ተመጣጣኝ ምላሽ በመነፈጉ በመንግሥት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ማመጹን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሲዘገብ ሰንብቷል ። የሕዝቡ የልማትና የወረዳ ጥያቄ ከአስር ዓመት በላይ ዕድሜ አለው። ሕዝቡ ከዛሬ ነገ ምላሽ አገኛለሁ ብሎ ሲጠብቅ አልተሳካለትም። በመሆኑም ተስፋ በመቁረጥ ይመስላል ወደ ሰላማዊ ተቃውሞ አመራ።
ሕዝቡ ያቀረበው ጥያቄ የማያሻማና ግልጽ ነበር። የዞኑን ሕብረተሰብ ብዛትና አሰፋፈርን እንዲሁም የወረዳዎችን ጂኦግራፊያዊ አቀማማጥ ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ተጨማሪ ወረዳ ይፈቀድልን ፤ የአንዳንድ ወረዳዎች የወረዳ ማዕከላት ቀደም ሲል የወረዳውን ሕዝብ አማክሎ ከሚገኝበት ቦታ አንስተዉት አብዛኛውን የወረዳውን ነዋሪና ቀበሌያትን ወደ ማያማክል፤ የመጠጥ ውሃ እንኳን ለማግኘት ወደሚቸገርበት ሥፍራ እንዲዛወር ተደረገብን፤ የወረዳው ማዕከል ራቀብን፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ምንም የሕዝብ አስተያየት ሳይጠየቅና የብዙኀን ይሁንታ ሳይኖረው በጊዜው የነበሩ የወረዳና የዞን ካድሬዎች እንዳሻቸው በፈቃዳቸው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ወደ ማያማክለን ሥፍራ አዛውረውብናል በድለውናል። ደጋግመን በየደረጃው ብናመለክት ብናለቅስ ሰሚ አጣን። በዚህ የተነሳ ተቸገርን። ፍትሕ በአግባቡ ማግኘት ተሳነን። ማሕበራዊ ተቋማትንና ልማትን ማግኘት አልቻልንም።  መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲኖረን እንሻለን። ወረዳም የልማት አካል መሆኑ ታውቆ መፍትሄ ይሰጠን የሚል ነው።

መንግሥት ሕዝቡ ላቀረበው ዴሞክራሲያዊና የመብት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አልቻለም። በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልክ ተደራጅቶ ጥያቄውን በየደረጃው ለመንግሥት ለማቅረብ ወሰነ። ሽማግሌዎችን መርጦ ጥያቄውን ለዞን አስተዳደር ለክልልና ለማዕከላዊ መንግሥትም አቀረበ። ምንም መልስ አጣ። እንዲያውም ዘግይቶ ምላሹ በሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ ውክልና ተሰጥቷቸው በየደረጃው ተንቀሳቅሰው የሕብረተሰቡን አቤቱታ ለመንግሥት ያቀረቡትን ሽማግሌዎች ለይቶ ሕዝብን የምታሳምጹና የወረዳ ጥያቄ የምትቀሰቅሱ እናንተ ናችሁ በሚል የዋካ ከተማ አባቶችን ማሰር ተጀመረ። ሽማግሌዎቹን ፖሊስ በያዛቸው ቀን በቁጣ ገንፍሎ የወጣው የዋካ ከተማ ሕዝብ የፖሊስ ጣቢያውን ያለምንም መሳሪያ ባዳ እጁን ተቆጣጠረው። በዚህ ሁኔታ ነበር አመጹ የፈነዳው።  
በዚህ ኃላፊነት በጎደለው የዞንና የክልል የፖለቲካው አመራር አካላት ድርጊት የተቆጣው የዳውሮ ዋካ ሕዝብ የምትሰጡን ምላሽ የወከውልናቸውን ሽማግሌ አባቶችን ማሰር ሊሆን አይችልም በፍጹም አታስሯቸውም ልቀቋቸው ሲል በቁጣ ተንቀሳቀሰ አመፀ አደባባይ ወጣ። የዋካ ከተማ አካባቢ ቀበሌዎች ሕዝብም በድርጊቱ በጣም ተበሳጨ ከዋካ ከተማ ሕዝብ ጎንም ተሰለፈ። በዚህ የተነሳ አመጹ ከማረቃ ወረዳና ከዳውሮ ዞን ፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ሆነ። ሕዝቡ በቀጥታ ወደ ትግል ገባ። ከፌዴራል ከተላከው ፖሊስ ጭምር በከፍተኛ ወኔ ወደ ጠንካራ ትግል ውስጥ ገባ።። በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት በርካታ ወጣቶች ረዘም ላሉ ወራት ታስረዋል ተንገላተዋል። እንዲፈረድባቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ግፊትና ጫና ተደርጎባቸው አልፏል።
የማይረሳው ሰማዕት የመምህር የኔሰው ገብሬ ትግል ትውስታ
ሰማዕቱ መምህር የኔሰው ገብሬም ይህንኑ የሕዝብ ጥያቄ አንግበው ከተነሱት የዋካ ከተማ ወጣቶች መካከል አንዱ ነበር። ከዋካ ከተማ ሕዝብ ጎን በመሰለፍ ቆመ። ሕመምህር የኔሰው ገብሬ የዳውሮ ተወላጅ አይደለም። የአካባቢው ተወላጅ አይደለሁምና ሕዝቡ ጥያቄው ቢመለስ ባይመለስ ምን ያገባኛል? አላለም። ያደግሁበት የተማርኩበት ለሥራ የበቃሁበት ቦታ ነው። ሕዝቡም ለዚህ ያበቃኝ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነው በሚል ነው የሕዝቡን ጥያቄ አብሮ አንስቶ የነበረው። ፖሊስ አመጹን ለማክሸፍ ሲል ከሰልፉ መካከል ለይቶ ካሰራቸው በርካታ ወጣቶች መካከልም አንዱ ሆነ። ከሌሎች ወጣት ጓደኞቹ ጋር ተርጫ ፖሊስ ጣቢያና ማረሚያ ቤት ታስሮ ተንገላቷል። ከተወሰነ የእስራት ጊዜ በኋላ ከእስር በዋስና በማስጠንቀቂያ ከወጡት ጋር አብሮ ወጣ።አብሮ በአንክሮ አስተጋባ። የሕዝብ ድምጽ ይሰማ! ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሽማግሌዎቻችን ይፈቱ! የወረዳ ጥያቄ የልማት ጥያቄ ነው! ጥያቄያችን የብዙኀን ሕዝብ እንጂ የጥቂቶች አይደለም! የዋካን ከተማ ከልማት ለማራቅና ብሎም ከተማዋን ለማዳከምና ብሎም ለማክሰም የሚደረገውን የጥቂት ካድሬዎችን ሴራ እናወግዛለን! እንታገላለን! ሕዝብን የሚበድሉ አመራሮች ይወገዱ! ሙሰኞችና ጉበኞች የሆኑ ባለሥልጣናት ለህግ ይቅረቡ! ዝምድናና አድሏዊ አሰራር ከሀገር ይወገድ! በዘመድ በአቻና በጋብቻ የሚደረግ ሹመት ይቁም! ወዘተ የሚሉ ነበሩ።
ሽማግሌዎቹ በወቅቱ የታሰሩበት ዋናው ምክንያት የዋካ ሕዝብ ተወካዮች ከእኛ አልፈው ወደ ላይ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ድረስ ለምን ሄደው አቤቱታ አቀረቡብን? ለምን ከሰሱን? የሚል ስሜት ያደረባቸው ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት መመሪያ ነበር።ሌሎች ጓደኞቹ ከእስር ባለመለቀቃቸው የተነሳ የፍትህ መጓደል ሰማዕቱ የኔሰው ገብሬን ሲያበሳጨው ሰነበተ። ሌሎች በእስር የቆዩ ጓደኞቹና በርካታ ታሳሪዎች ህዳር 29 ቀን 2004 ዓ.ም ከተርጫ ወህኒ ቤት በአጃቢ ፖሊስ ወደ ማረቃ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀረቡ። ከወህኒ ቤት በዕለቱ ቢያንስ በዋስ ሊወጡ ይችላሉ የሚል የሕዝብ እምነት የነበረ ቢሆንም የዞኑ አመራሮች በፍትህ ሂደቱ ጣልቃ የገቡ በመሆናቸው ሌላ የጊዜ ቀጠሮ ፖሊስ ጠይቋል በሚል ታሳሪዎቹ በሙሉ ወደ ወህኒ ቤት እንዲመለሱ ዳኛው ያዛሉ።
በዚህ የፍትህ ቧልት የተበሳጨው መምህር የኔሰው ገብሬ ፍርድ ቤት ዳኛው የሰሩትን ሥራ እሱ በችሎቱ ላይ ስለነበር ምንም ሳይፈራ በድፍረት አውግዞ ከችሎቱ ወጣ። ከዚያም በቀጥታ ቤንዝን ወደሚያገኝበት አምርቶ ያሰበውን ያህል ይገዛና በፈሳሽ መያዣ በኪሱ ይዞ ጉዞውን ወደ ዳውሮ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት አቀና።
በአቶ አለማየሁ አሰፋ የደቡብ ክልል ምክትል አስተዳዳሪና የክልሉ የፖለቲካ ኃላፊ ሰብሳቢነት ይካሄድ የነበረ የዳውሮ ዞን የሁሉም ወረዳና የኮንታ ልዩ ወረዳ አመራሮች በጋራ ወደ ተሰበሰቡበት የስብሰባ አዳራሽ ዘልቆ ገባ። አመራሩ የዋካ ከተማ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል ተገቢ ያለመሆኑን፤ የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር በዳውሮ ውስጥ ያለመኖሩን፤ ሕዝቡ ፍትህ አጥቶ መቸገሩን በማረጋገጡና የሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ምላሽ እስር መሆኑ እንዳሳዘነው አብራርቶ ለዚሁ የሕዝብ በደል ራሱን ለመስዋዕትነት ማዘጋጀቱን ለተሰብሳቢው አስረድቶ ከስብሰባው አዳራሽ ወጣ። ከአዳራሹ በር ብዙም ሳይርቅ ራሱ ላይ የያዘውን ቤንዚን አርከፍክፎ በድፍረት ራሱን በማቃጠል ለህግ የበላይነት እጦት፤ ለፍትህና ዴሞክራሲ መጓደል ሲል ራሱን መስዋዕት አደረገ። በአመራሩ ፀረ ሕዝብነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ተማርሮ ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል የትግል ወኔ ለመቀስቀስና የሥርዓቱንና የአመራሩን ፀረዴሞክራሲያዊ አሰራር በማውገዝ ለትግል አርዓያነት ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ።
የሕዝቡ ተቃውሞ እጅግ መጠናከር
የዚያን ጊዜ የተቀጣጠለው የተጨማሪ ወረዳ የወረዳ ማዕከልና የልማት ጥያቄ እሳት በመንግሥት  ተጽዕኖና የእስር እርምጃ እንቅስቃሴ  የተገታ ቢመስልም ሊቆምና ሊጠፋ የሚችል ግን አልሆነም። ጉዳዩ የዳውሮ ማረቃ ዋካን የቶጫን የሎማ ዲሳን ወረዳ ሕዝብንና መንግሥትን ሆድና ጀርባ አድርገው። በዚህ የተነሳ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ወደ ሕዝቡ ዘልቀው ገብተው ለፖለቲካ ሥራ መንቀሳቀስ ተሳናቸው። ሕዝቡ በካድሬውና በየደረጃው ያለውን አመራር እየጠላው ተቃውሞውንም በግልጽ ማቅረቡን ቀጠለ።
በዚህ የተነሳ ይህን የወረዳና የልማት ጥያቄ ዳግም ከሕዝብ እንዳይነሳ በማድረግ ከሕብረተሰቡ አዕምሮ ፈጽሞ ለመፋቅ ያስችላል የተባለለት ዘዴ ተቀይሶ ለዝቅተኛ ካድሬዎች ስልጠና ተሰጥቶ በአዲስ መልክ ወደ ሕዝቡ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ከክልሉ የፖለቲካ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ አለማየሁ አሰፋ የታዘዘው ዝቅተኛ ካድሬ ለመኖር ሲል የማያምንበትን አጀንዳ አንግቦ ህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ ቅስቀሳ ጀመረ።
ቅስቀሳውም የወረዳ ጥያቄ የጥገኞች ጥያቄ ነው፤ የአሸባሪዎችና የነፍጠኞች ጥያቄ ነው፤ እኛ ልማት እንጂ ወረዳ አንፈልግም፤ የወረዳ ጥያቄ የሚያነሱ እርምጃ ይወሰድባቸው ወዘተ የሚሉ ነበሩ። የተፈለገው ሕዝቡ ቅስቀሳውን ተቀብሎ ጥያቄውን እንዲያቆም ነው የታቀደው። ካድሬውም ጥያቄው ዳግም እንዳይነሳ እንዲረሳ ለማድረግ እንዲችል ነው የሚቀሰቅሰው። ሕዝቡ አልቀበልም ወሬኞች ዞር በሉ አላቸው። በዚህ የቅስቀሳ ሥራ ካድሬው በገዛ እጁ የተዳፈነውን የወረዳ ጥያቄ እሳት ቆስቁሶ ጋዝ አርከፈከፈበትና አቀጣጠለው።
ዳግም ሕዝቡ በቁጣ ተነሳ። ወረዳ ከልማት አንዱና ዋነኛው ነው አለ። የወረዳ ማዕከልነት ለዋካ ከተማ ይገባል። የሚለውን አቋም አጠንክሮ እንደያዘ ጸንቶ ቆመ። ዝቅተኛ ካድሬዎችም እንደታዘዙት ህብረተሰቡ መካከል በየመንደሩ ተደራጅተው ገብተው የዋካን ከተማ የወረዳ ማዕከልነትን ጥያቄ ሊያሟሟና ሊያስቀለብስ የሚያስችል ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሰንብተው አቃታቸው። በሕብረተሰቡ መካከል መጠነኛ ያለመግባባትን ለማንሳት ቢሞክሩም ሕዝቡ አብሮ የኖረና አብሮነትን የሚፈልግ በመሆኑ የካድሬዎችን ሴራ ራሳቸውን የሚያሳፍር ሆኖ ተገኘ። ሕዝቡ እኛ አንድ ነን።፡እናንተ ናችሁ ካድሬዎቹ የበጠበጣችሁን እንጂ እኛ ሕዝቡ መች ተጣላን? ለምንስ እንጣላለን?  በሚል በካድሬ ወሬ የማይለያይ የማይጣላ መሆኑን በተግባር አስመሰከረ። ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ገብቶ የፖለቲካ ሥራ መሥራት ለካድሬዎች ዳግም የሚያስጨንቃቸው ሆኖ ተገኘ። ሕዝቡም ካድሬ የሚባል ነገር አትላኩብን አንፈልግም አይምጡብን ብሎ በአደባባይ ተናገረ። ከዚህ በላይ መሄድ እንደማይችሉ ሕዝቡ እንዳሸነፋቸው አውቀው ተስፋ ቆረጡ። በዚህ የተነሳ የዋካን የወረዳ ማዕከልነትን ጥያቄና የቶጫ ወረዳን የማዕከል ዝውውርን ጥያቄ መቀበል ለአቶ አለማየሁ አሰፋ የግድ ሆኖ መጣ። እየመረራቸው የሚጠጡትና እያነቃቸው የሚውጡት ነገር ሆነባቸው አደረጉትም።
በወቅቱ በነበሩት ጥቂት መንደርተኛና ግለኛ የነበሩት ባለሥልጣናት ሕዝቡ እያነባ ነጥቀውት ወስደውበት የነበረውን የወረዳ ማዕከል ጥያቄ በመራራ ትግሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ምላሽ ሊያገኝ በቅቷል። ታስሯል ተወንጅሏል በወራዳ ቃላት በካድሬዎች ተሰድቧል። ጸረ መንግሥት የሆነ ሕዝብ ነው ተቃዋሚ የበዛበት ሕዝብ ነው አሸባሪዎች ይበዙበታል ነውጠኛ ሕዝብ ነው ወዘተ በሚል የስጋት ፍረጃ ሕዝቡን አሰቃይተውታል።
በተመሳሳይ የቶጫ ወረዳ ህዝብም በዘመኑ ባለሥልጣናት ተፅዕኖ የተነጠቀውን የቶጫን ወረዳ ዋና ከተማ ቀድሞ ወደነበረው ሥፍራ እንዲመለስ ሕዝቡ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። ወደ ከጪ ከተሰደደበትና ከተወሰደበት እንደገና ወረዳው ወደ ቶጫ እንዲመለስ ተወስኗል።
የሚያሳዝነው ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ተገቢና አግባብ ነው ብለው በተለያዩ ጊዜያት ያነሱ በርካታ አመራሮች ከተለያዩ ወረዳዎች ተገምግመው ከሥልጣናቸው ተባርረዋል። በአካባቢው ህዝቡን ወደ አመጽ ሊመሩና ሊያስተባብሩት ይችላሉ በሚል በዝውውር ወደ ሌላ ወረዳና ወደ ዞን እንዲገቡ የተደረጉም አሉ። የቶጫ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረውን አቶ ፍቃዱ ወ/ሩፋኤልን መጥቀስ ይበቃል። ከወረዳው ውጭ እንዲነሱ ተገደዋል።
እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ የማረቃ ዋካና የቶጫ ወረዳዎች የሕዝብ ጥያቄ በህዝቡ ከፍተኛ ብቃት ድፍረትና መስዋዕትነት  ምላሽ አግኝቷል። ሕዝብ አሸንፏል። ምላሹ ቢዘገይና መስዋዕትነትን ቢጠይቅም ዋጋ ከፍሎበት ድልን ተቀዳጅቷል። ክብር የሚገባውን ታላቅ ሥራ የማረቃ ዋካና የቶጫ ወረዳ ሕዝብ ሰርቷል። የሎማ ዲሳ ሕዝብም አጠናክሮ ትግሉን ሊቀጥል ይገባል።
ከዳውሮ ሕዝብ የትግል ተሞክሮ
የዳውሮ ሕዝብ ካደረገው ጠንካራ ትግል ሌላው ኢትዮጵያዊው ሕዝብ መማር ያለበት ነገር አለ። የዳውሮ ሕዝብ ባመነበት ጉዳይ በጋራ መቆምን አብሮ መታገልን በተግባር አሳይቷል። የተለያየ የካድሬው የመከፋፈል ሐሳብና ሴራ አልተቀበለም አክሽፎታል። በደረሰበት ዛቻ ስድብ ማስፈራሪያና እስራት አልተበገረም። የመረጣቸውን ሽማግሌዎች /ተወካዮች/ ካድሬዎች ከፖሊስ ጋር ተባብረው አስረውበት በድፍረት ተጋፍጦና ታግሎ አስፈትቷቸዋል።  ጥቂቶችን በጥቅም ከፋፍለው ለመያዝ ያደረጉትን ሴራ በጋራ ታግሎ አክሽፏል። ሕዝቡ ለታሰሩት ታጋዮች እስከሚፈቱ ድረስ ስንቅ በማቀበልና ቤተሰቦቻቸውን በጋራ በመንከባከብ  አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን በተለያየ መንገድ የመርዳትና የመንከባከብ ሥራ አከናውኗል። ከካድሬዎች ጎን ለጥቅማቸው ሊሰለፉ የቃጡትን በማሕበራዊ ሕይወት ከሕዝቡ ጋር ሊቀጥሉ እንደማይችሉ በመግለጽ ባንዳነት እንዳይንሰራፋ በሚገባ ተቆጣጥሮታል።
በኢትዮጵያ ሰላም ዴሞክራሲ ነፃነት እኩልነት ፍትህ የህግ የበላይነት እንዲኖር የምንታገል ሁላችንም ለውጥ ለማምጣት የምንችለው በመተባበር በመተማመን በድፍረት በመታገልና በቀጥታ በመጋፈጥ ብቻ መሆኑን ያስተምረናል። በጋራ ሕዝብ ሲቆም የሚቋቋመውና የሚያሸንፈው አንዳችም ኃይል የለም።
በየደረጃው የሚገኙት ካድሬዎችም የተማሩት ነገርም አለ። የሕዝብን እውነተኛ ጥያቄ በሚገባ ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ከሕዝብ ጎን መቆም አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯቸዋል። በተለይ ዝቅተኛ ደረጃ ካድሬዎች ከበላይ አካል የሚተላለፍ እንጨትን ብረት ነው የሚል ዓይነት አስቸጋሪና አሳፋሪ መመሪያ በቀጥታ ተቀብሎ የሕዝብን ፍላጎት የማይጠብቅ ነገር ይዞ ለተግባራዊነቱ መግባት የሚያስከትለው አደጋ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ መሰሪ የሆነ ፕሮፓጋንዳ እንዲሰሩ የታዘዙት ካድሬዎች እንደገና የመጀመሪያውን ቅስቀሳ የሚያፈርስ ተቃራኒ የቅስቀሳ ሥራ እንዲሰሩ መመሪያ መሰጠቱ በካድሬውና በህዝብ መካከል ፍጥጫ ማስከተሉ በተግባር ታይቷል። የሕዝብን ፍላጎትና ውሳኔ መከተል እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ተምረዋል።
ጥያቄው እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄ እንጂ የጥቂቶች ባለመሆኑ እነሆ ሰማዕቱ የኔሰው አንግቦት የተነሳው የዋካ ከተማ የወረዳ ማዕከልነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። ዋካ ከተማ የወረዳ ማዕከልነት እንዲያገኝ የዳውሮ ዋካ ሕዝብ በከፈለው መስዋዕትነት የትግሉን ውጤት አግኝቷል። ባላንጣው የነበረውን የፖለቲካ አመራር አንገት አስደፍቷል። የቶጫ ወረዳ ሕዝብም በተመሳሳይ የወረዳ ማዕከሉን በመራራ ትግሉ አስቀይሮ ቀደም ሲል ወደነበረበት ሥፍራ ወደ ቶጫ እንዲመለስ አስደርጓል። የዳውሮ ሕዝብ ታግሎ በብቃት አሸንፏል። የሎማ ዲሳ ወረዳ ሕዝብ ጥያቄም ምላሽ ይቀጥላል። ምላሽ ማግኘቱ የግድ ነው። የዲሳን ሕዝብ ጥያቄ ፍትሃዊነት አምነን እያንዳንዳችን እንደዳውሮ ሕዝብ አካል የህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እንዲያገኝ በሞራልና በማቴሪያል መደገፍ ይጠበቅብናል።
የሚከተሉትን ነጥቦች እስቲ እናንሳ! የዳውሮ ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ ልክ ነበር ወይስ አልነበረም? የማረቃ ሕዝብ የወረዳው ማዕከል ዋካ ይሁንልኝ ማለቱና የቶጫ ሕዝብ ደግሞ ቶጫ ላይ ይሁንልኝ ብሎ መጠየቁ ስህተት ነበር ወይ? ሕዝብ የዋካንና የቶጫን የወረዳ ማዕከልነት የጠየቀው ጥያቄ ተገቢ መሆኑ ከተረጋገጠና ጥያቄው የሕዝብ መሆኑ ከታመነበት ዘንድ ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለማፈን ሲሉ ሕዝቡ በወከላቸው ያገር ታላላቅ ሽማግሌዎችና በወጣቶች ላይ ለደረሰው የሞራልና የማቴሪያል ኪሳራ እስራትና ግርፋት ለደረሰበት በደል ሁሉ ተጠያቂው ማነው? ይህንን ያህል ጊዜ ሕዝቡን ያለፋው የቀጣው ጠላቱ ማነው? ማንነቱን ለይቶ ለሕግ የማቅረቡ ሥራስ? ለሰማዕቱ የየኔሰው ገብሬ ህይወትስ ተጠያቂው ማነው? ነፍሱ ተጠያቂ ሰው አይኖራት ይሆን? ከዚህ ቀደም የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ማለት በዳውሮ ደረጃ የሕዝብ ጥያቄ ነው በሚል አቋም ይዘውና በመድረክ አንስተው ከሥልጣናቸው ከካድሬነታቸው ጭምር የተወገዱ የህዝብ ልጆችስ ካሳ አይገባቸውም? እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ።
እንደሚታወቀው ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለውጤት ለማብቃት ከፍተኛ ድካምና ዋጋ ተከፍሎበታል። የማረቃ ወረዳ በተለይም የዋካ ከተማ ወጣቶችና አባቶች ዋጋ ከፍለውበታል። የሕዝቡ ጥያቄው መመለሱ ሕዝቡን ያስደስተው እንጂ አይገባህም እያሉ ሲያፍኑት የነበሩትን ባለጊዜዎች የሚያበሳጫቸው ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል። ከዚህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ያላግባብ በተጽእኖ በእስር ሆነው አሁንም ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖቻችን እንዳሉ ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም።
የዳውሮ ዋካ ሕዝብ ትግል ከክልልና ከአገር አቀፍ ትግልነት በዘለለ መልኩ ዓለም ዓቀፋዊ ይዘትና ትኩረት ሊያገኝ የበቃ ትግል ነበር። ለህዝቡ ጥያቄ ሲል ራሱን መስዋዕት አድርጎ ትግሉን የበለጠ አጠናክሮት ያለፈው ሰማዕቱ መምህር የኔሰው ገብሬ ነው። የሕዝብ ልጅ የነበረና ራሱን ለትግሉና ለጥያቄው የሰዋው ወንድማችን የኔሰው ገብሬ በዋካ ከተማ ሕዝብ የትግል ታሪክ ጉልህ ሥፍራ አግኝቶ ለዘለዓለም ሲዘከር ይኖራል። ለዚህ ሰማዕት መምህር የኔሰው ገብሬ ዝክር ለሚደረገው ዓለም ዓቀፍ እንቅስቃሴ እያንዳንዱ የሕዝብ ወገን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል  እላለሁ።
በቀጣይ በዳውሮ ውስጥ እየተንሰራፋ የመጣውን ግፍ በደልና እስራት በዝርዝር የሚያብራሩ ጽሁፎችን አቀርባለሁ። አለማየሁ አሰፋና ግንቦት 7 በዳውሮ፤ የሚገዛን ግለሰብ ነው ወይስ ፓርቲ? እንዲሁም የሰማዕቱ መምህር የኔሰው ገብሬ የዝክረ ታሪክ የሥራ ዕቅድ በቀጣይዋ ዳውሮ ዋካ  በሚሉ ርዕሶች ይሆናል። በቸር ያሰንብተን።

No comments:

Post a Comment