Wednesday, February 6, 2013

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ሳስበው!



«ልጆቼን ከተወለዱ ጀምሮ ለ20 ቀናት ያህል ስለያቸው ይህ የመጀመሪያዬ ነው። ለዚህ ብርታት እና ፅናት እንዲሆነኝ ግን ዘወትር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አስበዋለሁ። የእስክንድር
Eskinder Nega and his Son Nafkot
እስክንድር ነጋ እና ልጁ ናፍቆት
ልጅ የተወለደው አሁን እርሱ የሚገኝበት እስር ቤት ውስጥ ነው። የሕወሃት ደጋፊዎች ይህንን ሕዝብ ከደርግ ገላገለው እያሉ የሚያደንቁት ስርዓት እርጉዝ ሴት እስር ቤት ውስጥ እንድትወልድ ያደረገ ግፈኛ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል። ይህም ሳይበቃቸው ልጁ አምስት ዓመት ሞልቶት እስክንድር ከትምህርት ቤት ሲመልሰው ነበር ድንገት ይዘውት የሚወደው አንድ ልጁ ፊት እጁን ወደኋላ የፊጥኝ አስረው በቪድዮ እየቀረጹ የወሰዱት፣ አሁን የርሱን ልጅና የኔን ልጆች ሳወዳድር የኔ ልጆች በምንም መለኪያ ከ20 ቀናት በኋላ እንደሚያዩኝ እርግጠኞች ናቸው። የእስክንድር ልጅ ግን አይችልም።»
(አርቲስት ታማኝ በየነ አድላይድ/ደቡብ አውስትራሊያ እ.ኤ.አ ጁላይ 2012 )
እውቁ ኢትዮጵያዊ የነፃ ፕሬስ ጀግና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ “አሸባሪ” ተብሎ ለዘጠነኛ ጊዜ የወያኔ እስር ቤት ውስጥ ከተዘጋበት እነሆ ድፍን 16 ወራት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብርቅዬው የኢትዮጵያ ልጅ በፈጠራ ወንጀል ያለአግባብ መታሰሩን በመቃወም በአገር ውስጥ የወያኔን የአፈና ድር በጣጥሶ የተደረገ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባይኖርም፣ በውጭ አገር የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ድምፃቸውን በልዩ ልዩ መልክ በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ።

ከኛ ከኢትዮጵያውያኑ ይበልጥ ግን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ መንግስታትና ታዋቂ ግለሰቦች የተመሰረተበትን የፈጠራ ክስ በማጣጣል፣ አምባ-ገነኑ የሕወሃት አገዛዝ ያለምንም ቅድመ-ሁናቴ ከእስር እንዲፈታው ደጋግመው ከመጠየቅ የተቆጠቡበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል። እንዲያውም እርሱንም ሆነ ሌሎቹን በአሸባሪነት ተወንጅለው እስር ቤት የተጣሉትን የተወነጀሉትን በእስር ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ለታላቅ ማዕረግ፣ ክብርና ሽልማት አጭተው በመሸለም የወያኔ የፍትሕ ስርዓት ምን ያህል የተዛባና የተወላገደ መሆኑን ለዓለም ህዝብ በግልጽ አሳይተዋል።
ብዙዎች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚከትባቸውን በሳል መጣጥፎቹን በማንበብ ብቻ፣ ታላቅ የነፃ ፕሬስ ጀግና አድርገው ይስሉታል። በርግጥም እስክንድር የተላበሰው የዓላማ ፅናትና የሞራል ጥንካሬ፣ የሕወሃት መንግስት በተደጋጋሚ እያደረሰበት በሚገኘው እንግልት፣ ማስፈራሪያ፣ ድብደባና የግፍ እስራት ከቶም ሊሰበር ያልቻለ ብርቱ ሰው ነውና ይህ ክብር የሚበዛበት አይደለም። “ምነው ችሎታውና መራቀቁ፤ ብቃቱና የቅኔው ችሎታ በኖረኝና ለእስክንድር ነጋ በውስጤ ታምቆ ያለውን አክብሮት መግለጽ በቻልኩ?” የሚሉት እውቁ የህግ ምሁርና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም “እስክንድር ፍጹም የሆነ ተስፋና ጥንካሬ ያለው፤የእያንዳንዱን ሰብአዊ ፍጡር ውስጣዊ የነጻነት ስሜት የሚወክል ተስፋ የሰነቀ ታላቅ ሰው ነው።” ሲሉ ይገልፁታል።
“እንደ እስክንድር ያለ አለም አቀፍ እዉቅና ያለዉ ጀግና በመካከላችን ማግኘታችን እድለኞች ነን።” የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ናቸው። ዶ/ር ፍስሃ በቅርቡ ባስነበቡን መጣጥፋቸው “በዘመናችን ከጀግናዉ እስክንድር ነጋ የተሻለ ተበታትኖ ያለዉን የትግል ጎራ አሰባሳቢ ሊሆን የሚችል የራሳችን ማንዴላ ይኖራል ብዬ አላምንም።” በማለት ጋዜጠኛ እስክንድር የጥንካሬ፣ የነፃነት፣ የአንድነት፣ የፅናት ተምሳሌታቸው መሆኑን በመግለጽ እርሱን ለዚህ ያጩበትን 11 ጉልህ ነጥቦች በዚህ መልኩ ይዘረዝራሉ፦
1.በትግሉ ከሃያ አመታት በላይ ተፈትኖ እስካሁን ያለማመንታት በፅናት እየታገለ ያለ፤
2. ለኛ ነፃነት፤ ለፍትህ፤ ለመናገር መብት ለእኩልነት በመቆሙ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ በፋሽሽቱ ስርዓት ለእስር የተዳረገና አሁንም ለበርካታ አመታት ተፈርዶበት ወህኒ እየማቀቀ ያለ፤
3. ሀብትና ንብረቱን ለሀገሩና ለወገኑ ክብር አሳልፎ የሰጠ፤
4. ለሀገሩና ለወገኑ ነፃነት እስከ መሞት ለመታገል በቃልኪዳኑ የፀና፤
5. እንደሌላዉ ከሀገር ተሰዶ መኖር ሲችል ባርነትንና ጭቆናን ለመታገል ሀገር ቤት በመቅረት እየታገለ ያለ፤
6. በበሳል አንደበቱና በሰላ ፅሁፎቹ ስርዓቱን በፍፁም ጀግንነት ያንገዳገደ፤
7. በፀባዩ፤ በበሳልነቱ፤ ባጠቃላይ በስብእናዉና ለሰዉ ልጆች ባለዉ አመለካከት ፈፅሞ የተከበረ፤
8. የተከበረ የቤተሰብ አስተዳዳሪ፤
9. የሀገሩን ፍቅር ከልጁ ያስበለጠ፤
10. እኛ የሚገባዉን ድጋፍና እዉቅና ባንሰጠዉም በአለም አቀፍ ደረጃ እዉቅናና በርካታ ሽልማቶችን ያገኘ፤
11. በርካታ ፅሁፎችን የፃፈና ለኛ የታገለ እንዲሁም ትምህርቶችን ያስተማረ ሲሆን ሌሎችም እጅግ በርካታ ነጥቦች ማስቀመጥ ቢቻልም በኔ እምነት እንደወርቅ አንድ የሰዉ ልጅ ሊቀበለዉ የሚችለዉን ፈተና በእሳት የተፈተነና አሁንም ድረስ እየተፈተነ ያለ ነዉ።…
ድንቅ አገላለጽ!! …. ከወራት በፊት ቃሊቲ እስር ቤት ደርሶ የተመለሰውና አሁንም በፍርድ ቤት በተመሰረተበት ክስ እየተከራከረ የሚገኘው የታፈነችው የፍትህ ጋዜጣ (አዲስ ታይምስ) ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ስለ እስክንድር ጽፎ የሚታክተው ሰው አይደለም። እንዲያውም የእስክንድርን ታላቅነት ሳያወሳ ያለፈባቸው መጣጥፎቹ በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል። በርግጥም ተመስገን ያልታሰረው የእስክንድር መንፈስ የሰፈፈበት ብርቱ፣ ፅኑና ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። በዚህም የተነሳ በየምክኒያቱ ስደትን ምርጫቸው አድርገው በሰው አገር ከሚንገዋለሉ የነፃ ፕሬስ ባልደረቦች አንዱ እንደመሆኔ መጠን እርሱ በአገር ውስጥ የሚመጣበትን ነገር ሁሉ ተቋቁሞ ለማሳለፍ ባለው ቁርጠኝነትና ጽናት፣ በእጅጉ እማረካለሁ። የተመስገንን አነሳሁ እንጂ በአሸባሪነት ተወንጅላ እስር ቤት የተጣለችው እሕታችን ወጣት ርዕዮት ዓለሙን ጨምሮ ሌሎቹም የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች፣ በጥንካሬያቸው ብቻ ሳይሆን በችሎታቸውም አብዝቼ የማደንቃቸውና የምኮራባቸው የዘመኑ ድንቅ የነፃ የፕሬስ አርበኞች ናቸው። የፍኖተ-ነፃነቶቹም እንዲሁ!!
ምትክ የማላገኝለት ወዳጄ፣ የስራና የሙያ ባልደረባዬ፣ እንዲሁም የቀድሞ አለቃዬ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለኔ በዝች አለም ላይ አቻ የሌለው አንድ እውነተኛ ሰው ሊኖረው የሚገባውን መልካም ባህርይ የተላበሰ ምርጥ ሰው ነው። እስክንድር በጋዜጠኝነት ሕይወቱ ብቻ ሳይሆን ቀርቦ ለሚያውቀውም ሰው ብዙ የሚወደድ ባህርይ ያለው ታላቅና መልካም ሰው ነውና እንዲህ በዋዛ የሚዘነጋና በቀላሉ ከልብ የሚወጣ ሰው አይደለም። በዚህም የተነሳ እስክንድርን ሳላስበው የዋልኩበት ቀን ብቻ ሳይሆን፣ በእስር ቤት እየገፋው ያለውን የመከራና የስቃይ ህይወት እያብሰለሰልኩ ከአይኔ ሽፋፍሽፍቶች ድንገት ኮለል! ብለው በሚወርዱ ትኩስ የእንባ ዘለላዎች ፊቴ ያልተጨማለቀባቸው ቀናት እምብዛም ናቸው ማለት እችላለሁ። ለማንኛውም የእስክንድርን የግል ሰብዕናና መልካም ሰውነት በተመለከተ ማንም ካሁን ቀደም አስተያየቱን ሲሰነዝር አላየሁምና ዛሬ የትውስታ ማህደሬን እየፈተሽኩ ስለርሱ ጥቂት ላጫውታችሁ ተነስቻለሁና እነሆ!
ጠንካራ ሰራተኛው እስክንድር
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፈጽሞ እረፍት የሌለው ሰው ነው። “ከኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውጭ የትም መሆን አልፈልግም፣ ከድሉ ጋር አብሬ እልልታዬን እያቀለጥኩ፣ ከሞቱም ጋር መሞት እፈልጋለሁ።” በማለት ቃል የገባው እስክንድር፣ ከ17 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ የነፃው ፕሬስ ባልደረባ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ለመዝናናት አይደለም ለእንቅልፍ እንኳን የሚተርፍ በቂ ጊዜ ያልነበረው ሰው ነበር። ቀድሞ ከሕዝብ ጋር ይገናኝባቸው የነበሩትን የህትመት ውጤቶች (ኢትኦጲስ፣ ሃበሻ፣ ወንጭፍ መጽሄት፣ …ወዘተ) እንተዋቸውና መጨረሻ ላይ በርሱ የበላይነት የሚተዳደረው የሰርካለም አሳታሚ ድርጅት በሃይል ተዘግቶ ንብረቱ በገዥው ፓርቲ ከመወረሱ በፊት፣ በወር አንድ መጽሄት፣(ምኒልክ) እንዲሁም ከሳምንት ሶስት ጋዜጦች ተዘጋጅተው ለአንባብያን ይቀርቡ ነበር። ምንም እንኳን የነዚህን ስራ ሁሉ ብቻውን የሚያከናውነው ባይሆንም፣ የእስክንድር የስራ ድርሻ ግን እረፍትና ፋታ የሚሰጥ አልነበረም። በዚህም የተነሳ ከሰኞ እስከ እሁድ ድረስ ከቢሮ የተለየበት ጊዜ መኖሩን አላስታውስም። በተለይም የከተብናቸው ፅሁፎች ባግባቡ ተሰናድተው ወደ ማተሚያ ቤት በሚያመሩበት ዕለት፣ አብዝቶ በስራ ከመወጠሩ የተነሳ ለምግብ እንኳን የሚተርፍ ደቂቃ በማጣት አብዛኛውን ጊዜ ጾሙን ነበር የሚያሳልፈው ማለት ይቻላል።
እንዲያውም ጊዜውን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ለመስጠት ወስኖ የገባበትን ክቡር ዓላማ ከግብ ለማድረስ ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ፣ ከጋዜጣና መፅሔት ዝግጅቱ አልፎ ሌሎች ጥልቅ የህትመት ስራዎችን ለማዘጋጀት መድከሙን አያቋርጥም። ርዕሳቸውን ባሁኑ ወቅት ለመጥቀስ ባልፈልግም በርካታ ሰነዶችና ጥናቶች የተካተቱበት በርሱ የተዘጋጁ እጅግ ድንቅ መጽሃፍትም በብዕር ስም ታትመው በተለያዩ ጊዜያት ለአንባብያን ቀርበዋል። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በቀናት ውስጥ ተሸጠው በማለቅ ወዲያውኑ ከገበያ የጠፉ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ከመታሰሩ በፊት ያሳተመው “ምርጫ 97፣ መረጃና ትንታኔ” የሚለው መጽሃፉ፣ እንዲሁም ከቃሊቲ መልስ አዘጋጅቶት የነበረውና የማተሚያ ቤት ቀብድ ሁሉ ተከፍሎበት በገዥው ፓርቲ አፈና እንዳይታተም የተደረገው ጥራዙም ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ብቻ ሳይሆኑ፣ የርሱ ብቃትና ጥንካሬ መገለጫዎች ናቸው።
ቸሩ እስክንድር
እውቁ ሽሙጥ ፀሃፊና ጋዜጠኛ አቤ ቶኪቻው “ጠብሽ” በመታው የመንደር ጉልቤ የመሰለው ግፈኛው የሕወሃት አገዛዝ፣ እስክንድር ነጋ ከወላጅ እናቱ የወረሰውንና በስሙ እንኳን ያላዘዋወረውን ቤትና ንብረቱን ለመውረስ መንደርደሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያሳዘነ ጉዳይ ነው። ሆኖም ይህን ነገር ከቁብ ያልቆጠረው የንብረቱ ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ብቻ ነው። እርሱም ሆነ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ጉዳዩን እያየ ካለው የይምሰል ችሎት ቆመው በዚህ ጉዳይ መከራከር እንደማይፈልጉ በግልጽ አሳውቀዋል።
የ18 ዓመታት እስራት ከ5 ዓመታት የመብት እግድ ጋር የፈረደበት የወያኔው ፍርድ ቤት፣ ይህም አልበቃ ብሎት ከቤተሰቡ በውርስ ያገኘውን የቤተሰቦቹን ቤት፣ እንዲሁም በባለቤቱ ስም የተመዘገበውን መኪና ለመውረስ መነሳቱ ጤነኛ አዕምሮ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ መሆኑ አይካድም። ይሄ ሁሉ እንግዲህ በተደጋጋሚ በደረሰበት እስራት፣ ድብደባና ማስፈራሪያ አልበገር ያለውን የእስክንድርን ሞራል ለመስበር ከሚደረገው ጥረት አንዱ መሆኑ ነው። ነገር ግን እስክንድር ሲፈጥረውም ለሃብትና ለንብረት ግድ የሚሰጠው ሰው አይደለምና ውሳኔው በተቃራኒው የስርዓቱን አምባ-ገነንነት፣ ብሎም በፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚያደርገውን ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት ለሌላው የሚያሳብቅ ሆኖ ነው የተገኘው።
በርግጥም እስክንድር ነጋ እና አብዝቼ የማከብራት እንስቷ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ ወያኔ ለሚልካቸው ሽማግሌ ተብዬ የስርዓቱ አዳማቂዎች ባለመንበርከከ የ“ይቅርታ” ድራማው ላይ ለመተወን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከዚህም ያለፈ በደልና ጫና ሊደርስባቸው እንደሚችል እሙን ነው። በቅርቡ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበችውን ይግባኝ ሲያይ የነበረው ዳኛ ተነስቶ፣ በምትኩ የስርዓቱ ቀኝ እጅ የሆነ አዲስ ዳኛ በመሰየም ይግባኟ ውድቅ የተደረገበት ምክኒያትም ከዚህ የዘለለ አይደለም።
ድንገት አፈር የለበሱት አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ከውጭ አገር የሚደረግባቸውን ጫናና ጉትጎታ ተከትሎ ቃሊቲ ዘግተውባቸው የነበሩትን ስዊድናውያን ጋዜጠኞችን ይፈቱ እንደሆነ ሲጠየቁ “የነጭም የሆነ የጥቁር ደም አንድ አይነት ነው” በማለት ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተነጥለው እንደማይፈቱ በግልጽ ነግረውን ነበር። ሆኖም የጦር መሳሪያ አንግቦ ከሚፋለመውና በወያኔ መንግስት ዘንድ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ኦብነግ ሰራዊት መሃል የተያዙት ስዊድናውያን ጋዜጠኞች አቶ መለስ ተስካራቸው ሳይወጣ በ”ሬሳ አምላኪው” አዲሱ አገዛዝ በምሕረት (በይቅርታ) ስም ሲፈቱ፣ አብረዋቸው ይቅርታ የጠየቁትና ያቀረቡት ይቅርታም ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ እንዲሁም ሒሩት ክፍሌ እስካሁን ድረስ ከቃሊቲ እስር ቤት አልወጡም። በርግጥ የስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ይቅርታ የጸደቀው፤ የነጭና የጥቁር ደም ቀይ እንደሆነ ነግረውን የነበሩት የአቶ መለስ “ራዕይ” ታይቶ እንደሆነ በወቅቱ ተነግሯል። ይህ ከሆነ ደግሞ ጋዜጠኛ ውብሸትና ሂሩት እስካሁን ያልተፈቱበት ለምንድነው? …. የነውብሸት ደም ከነጮቹ የተለየ ቀለም ያለው ሆኖ ተገኝቶ ይሆን?
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በአንድ ወቅት እስክንድር እጅግ ባለፀጋ ከሆነ ቤተሰብ የተወለደ መሆኑን ለመግለጽ “የወርቅ ዋንጫ ይዞ ነው የተወለደው” ብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። እኔ ደግሞ እስክንድር ከብዙ የአገራችን የሃብታም ልጆች በተለየ መልኩ ከችግረኛ ወገኑ ጋር ወዳጅነት መስርቶ ያለውን ተካፍሎ ለመኖር የሚደክም ብቻ ሳይሆን ለዚህም ሲል ጥሪቱን የጨረሰ ሰው እንደሆነ ልነግራችሁ እሻለሁ። ስማቸውን አሁን መጥቀስ ባልሻም በግሉ ከወደቁበት አንስቶ በማቋቋም ዛሬ ለትልቅ ደረጃና ማዕረግ ያበቃቸው በርካታ ሰዎች እንዳሉም አውቃለሁ። እስክንድር ያማረ መኪና በመንዳት፣ ወይንም በውድ ዋጋ የተገዙ አልባሳትን በመልበስ ልታይ ልታይ ማለትና ማሸብረቅ የማይወድ፣ ፈጽሞ ድሎትንና ምቾትን የማይፈልግ፣ በጣም ደግ፣ ሩህሩህ፣ ለወገኑ አዛኝና የችግርም ተካፋይ የሆነ ልዩ ሰው ነው።
እንደሚመቸኝና ቀድሞ እንደለመድኩት አቆላምጬ ልጥራውና፤ “እዝቄ!” የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባው ሳንፎርድ (እንግሊዝ) ት/ቤት መማሩ፤ ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት በኢኮኖሚክስ የማስትሬት ዲግሪውን መስራቱ፣ አልፎ ተርፎም እንደዛሬው የአሜሪካ ኑሮ ሳይከብድና አበሻም ሳይረክስ፣ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ለ17 ዓመታት የተደላደለ ሕይወት ማሳለፉ፣ ይቺን በፍፁም ድሕነት የምትኖርና በያመቱ በረሃብ አለንጋ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆቿ የሚረግፉባት ምስኪን አገሩንና ወገኑን እንዲዘነጋና እንዲተው አላደረገውም።
እስክንድር ለስራም ሆነ ለሌላ ነገር ወደ ጎዳና ወጣ ብሎ ሲመለስ ኪሱ ውስጥ ገንዘብ ይገኛል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ያለውን በየመንገዱ ላገኘው ምጽዋት ጠያቂ ሁሉ አድሎ ባዶ እጁን ነው የሚመለሰው። ይህንን ስል እንደብዙዎቻችን አምስትና አስር ሳንቲም ጥሎላቸው የሚያልፍ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። አንዳንዴ እንዲያውም ይዞት የወጣው ገንዘብ አልቆ የሚያደርገው ሲያጣ የቢሮአችንን አድራሻ በመስጠት ነዳያኖቹ ቢሮአችን ድረስ ሰተት ብለው እንዲመጡ አመላክቷቸው ሁሉ ነው የሚመለሰው። በዚህም የተነሳ በየዕለቱ ከጠዋት እስከ ማታ ቢሮአችን የሚንጋጉት የምጽዋት ጠያቂዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። እንዲያውም ይህ ነገር ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመምጣቱ በአንድ ወቅት ባለቤቱ ሰርካለም ገንዘብ የሚባል ነገር እንዳይዝ እስከመከልከል የደረሰችበት ጊዜም እንደነበር አስታውሳለሁ። እስክንድር ግን ይህ ሁሉ እግድ ቢጣልበትም የሚመለስ ሰው አልነበረም። በተለይም ለህክምናም ሆነ ሌላ ሰበብ እየደረደሩ “ወደ አገሬ መመለሻ ገንዘብ አጣሁ” የሚሉ አዳፋ የለበሱ የተለያዩ ሰዎች አዘውትረው እየመጡ የጠየቁትን ያህል ገንዘብ አግኝተው መመለሳቸውን አይቻለሁ። እኔ እንዲያውም በመገረም ሰዎቹን አዘጋጅቶ የሚልካቸው ሰው እንዳለ ከመጠርጠር አልፌ እስከመጨረሻው አልገፋሁበትም እንጂ መከታተልም ጀምሬ ነበር። እርሱ ግን እንዲህ አይነት ነገር ለማሰብ ጊዜ የለውም፤ ካለው ከኪሱ አውጥቶ፣ ከሌለውም ከሌሎቻችን ኪስ ተበድሮም ቢሆን የልባቸውን አድርሶ ይሸኛቸዋል።
በወቅቱ የሚገርመኝና የማይዘነጋኝ ሌላው ነገር ሰዎቹ የርሱን ልብ ለማራራት የሚዘበዝቡትን ብሶትና ችግር እህ! ብሎ ለማድመጥ ያለው ትዕግስት ነው። እስክንድር ስራውን ሁሉ ትቶ ሁሉንም በቀና ልቦናና በሙሉ ትኩረት ነበር የሚያደምጣቸው ማለት ይቻላል። በአንድ አጋጣሚ ታዲያ አባዱላ ገመዳ (ምናሴ ተ/ማርያም) መጀመሪያ የቀድሞ ጦር ሰራዊት ወታደር፣ በኋላም የሻዕቢያ ምርኮኛ በነበረበት ወቅት አብሮት ያሳለፈና ሁለመናውን ጠንቅቆ የሚያውቀው የቀድሞ የቅርብ ጓደኛው ምፅዋት ጥየቃ በራችን ድረስ መጥቶ ብዙ አስገራሚ ነገር አውግቶን ይህንኑ በምስል አስደግፈን በጋዜጦቻችን ላይ ለአንባቢ ማካፈላችንን አስታውሳለሁ። በዚህ መልኩ ለሕትመት የበቁ ሌሎችም እውነተኛ ታሪኮች አሉ።
ዘወትር ስለ እስክንድር ሳስብ የልቡን ንፅህና አይቶ ሰርካለምን የመሰለ ለሁላችን መኩሪያ የሆነች ጠንካራ እህታችንን ከጎኑ ስለሰጠው ፈጣሪ አምላኬን ሁልጊዜም አመሰግነዋለሁ። ለነገሩ ቅዱሱ መጽሓፍስ “ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት።” አይደል የሚለው? (መጽሃፈ ምሳሌ 19፡14) የዚህ ፅሁፍ አላማ አይደለም እንጂ ሁለቱ የተገናኙበት አጋጣሚ፣ የፍቅራቸው አጀማመርና አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸው ፍቅርና መተሳሰብ እፁብ ድንቅ የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ብዙ ትምሕርት የሚሰጥና በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነ ልነግራችሁ እሻለሁ። ከስራ ባልደረባነት አልፎ አያሌ ዓመታት ባስቆጠረው ቤተሰባዊ ወዳጅነታችን እንደተገነዘብኩት ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የርሷ መንፈስ በርሱ፣ የርሱ ደግሞ በርሷ ውስጥ እየሰረፀ ፍፁም አንድ አይነት ሰዎች እየሆኑ መምጣታቸውን አስተውያለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ለዘላለሙ ከነርሱና ከቤተሰባቸው ጋር ይሁንልን!
ፈጣሪን ፈሪና ሰውን አክባሪው እስክንድር
እስክንድር ነጋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነው። ለረጅም ዓመታት እስክንድርን በቅርበት ሳውቀው ከአንደበቱ ሰውን የሚያስቀይም መጥፎ ቃል ሲወጣ ሰምቼ አላውቅም። ሰዎች ቢሰድቡትና ቢያንጓጥጡት እንኳን ምላሹ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ!” የምትል መልካም ቃል ብቻ ናት። እስክንድር በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ያነጋገረውን ሰው በፈጣሪ ስም ሳያመሰግነው አያሰናበተውም።
ይቺን ባህርይውን በጣም እወድለት ስለነበር እኔም ሳላውቀው ቀስ በቀስ ተዋህዳኛለች ማለት እችላለሁ። በርግጥ ስሜቴን የሚነካ ቃል ለተናገረኝ ሁሉ እንደርሱ መልካም ቃል ለመመለስ ትዕግስቱን ባልታደልም፣ በስልክም ሆነ በአካል ከሰዎች ጋር አውግቼ ስጨርስ የምደመድመው ከርሱ በተዋስኳት “እግዜር ይስጥልኝ” በምትለው ታላቅ ቃል ነው። ይህንንም መገንዘብ የቻልኩት ብዙ ሰዎች መልሰው “ለምኑ ነው እግዜር ይስጥልኝ የምትለኝ?” ስለሚሉኝ ነው።
እንዲህ ስል እስክንድር እንደዘመናችን ሃይማኖተኞች ፈጣሪውን በአንደበቱ ብቻ የሚያከብር ሰው ሊመስሎት ይችል ይሆናል። እስክንድር በስራ ውጥረት አዘውትሮ ቤተክርስቲያን መሄድ ባያዘወትርም፣ አርብና ረቡዕን ጨምሮ ሌሎቹን የቤተክርስቲያንችንን አጽዋማት ሳያፋልስ የሚጾምና የሚፀልይ ሰው ነው። ጾም ሲባል ደግሞ ከስጋና ከወተት መቆጠብ ብቻ ሊመስሎት ይችላል። እስክንድር በፆም ወቅት እስከቀኑ 9 ሰዓት ድረስ ውሃ እንኳን የማይጎነጭ ጽኑ ሰው ነው። ይህንኑ ጾምና ፀሎቱን አሁንም ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ቀጥሎበት እንደሚገኝ ባለቤቱ ሰርካለምም አጫውታኛለች ። ከዚህም በተጨማሪ ጫትም ሆነ ሲጃራ ምን አይነት ጣዕም እንዳላቸው ፈጽሞ የማያውቅ፣ ከሰው ጋራ ለመጫወት አንድ ብርጭቆ ድራፍት አስቀርቦ፣ እርሱንም ግማሽ ሳያደርሰው ትቶት የሚወጣና ከማንኛውም ሱስ የፀዳ ንፁህ ሰው ነው።
ማጠቃለያ
እስክንድር ነጋ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለየካቲት 10 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል። በርግጥ በርዕዪት ዓለሙ ይግባኝ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ያየ ሰው ከፍርድ ቤቱ ብዙም አዲስ ነገር አይጠብቅ ይሆናል። ነገር ግን አምባ-ገነኑ ስርዓት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ያሰራቸውን ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይፈታ ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተደረገበት ያለውን ከፍተኛ ጫና ለማለዘብ ሲል ቢያንስ ቢያንስ የ18 ዓመታቱን ፅኑ እስራት በማሳነስ ሌላ ጨዋታ ለመጫወት መሞከሩ የሚጠበቅ ነው።
ታዲያ በዚህ ወቅት ከምንም በላይ ዘረኛው ስርዓት ያለአግባብ እስር ቤት የዘጋባቸውን የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁናቴ ይፈታ ዘንድ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ተቀናጅተን፣ ሰፊና ቀጣይነት ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርብናል። እስክንድር ብቻ ሳይሆን፣ አንዷለም አራጌ.፣ ርዕዪት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ … ወዘተ ሌሎቹም የሕሊና እስረኞች መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የሚገኙት ለሕዝባችንና ለአገራችን ዘላቂ ጥቅም፣ ብልፅግና፣ ነፃነትና ሰላም ሲሉ መሆኑን ተገንዝበን ከጎናቸው በመቆም አለንላችሁ! ልንላቸው ይገባል።
እነዚህ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው እስር ቤት ውስጥ የቅማልና የቱሃን እራት እየሆኑ ያሉት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲፈቱ በማንኛውም መልኩ መታገል፣ እንዲሁም አብዛኞቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸውና በየእስር ቤቱ እያዩት ካለው ስቃይ በላይ “ልጆቼ እንዴት ሆነው ይሆን?” በማለት በሃሳብና በሞራል እንዳይጎዱ ቤተሰቦቻቸውን በተቻለን አቅም በሞራልም ሆነ በኢኮኖሚ ችግራቸው መደገፍ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ግዴታችን ነው። ለዚህ ደግሞ በተለይም በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን በያለንበት ከተማ ተደራጅተን በየወሩ በጣት የሚቆጠሩ ዶላሮችን ብቻ በማዋጣት ብዙ ውጤት ያለው ስራ መስራት እንችላለን ብዬ እገምታለሁ። ቋሚ የሆነ ስርዓት ሳናበጅለት በመቅረቱ በጅምር ቀረ እንጂ በስደት የምንገኝ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ይህንን መንገድ ባለፈው ዓመት ይህንን መንገድ ሞክረነው አጥጋቢ ውጤት አግኝተንበት እንደነበር አይዘነጋኝም። ለዚህም እኔ በምኖርባት አገር ላይ ያሉትን ጨምሮ በወቅቱ ቀና ትብብራቸውን ላሳዩ በዓለም ጫፍ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ እያመሰገንኩ፣ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደምና፣ እነዚህ ፍትሕ የተነፈጉ ወገኖቻችን ነፃነታቸው እስኪታወጅ ድረስ በስርዓቱ ላይ አስፈላጊውን ጫና በማድረግም ሆነ በማንኛውም መልኩ ከጎናቸው ለመቆም ሁላችንም በያለንበት በአንድነት ተደራጅተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል እላለሁ።
ቅዱስ-ሃብት በላቸው
ከደቡብ አውስትራሊያ
ለግል አስተያየት

No comments:

Post a Comment