Monday, February 11, 2013

አቶ ስብሓት ነጋ ፍርዳቸውን ሲጨርሱ…



ሐራ ዘተዋሕዶ
  • ‹‹ዕርቅ ለመፈጸም በማለት ሰዎችን ሲልኩ የነበሩ ቄሶች መሰቀል አለባቸው፡፡››
  • ‹‹ታምራት ቤተ ክርስቲያኒቱን ይቅርታ ሊጠይቅ አይችልም፡፡››
  • ‹‹[ሲኖዶስ ማቋቋም] በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከግራኝ ከጉዲት የባሰ ትልቅ  ወንጀል ነው፡፡››
  • <‹ኣቦይ ስብሃት አረጋዊ ናቸው፤ ይሄ የመነጣጠል አባዜ ቢቀርባቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የተጣላ ቢያስታርቁይሻላቸዋል፡፡. . .አርባ ዓመት ሙሉ ቀውስ አታቀጣጥሉ በሉልኝ፡፡›› /አቶ ኣስገደ ገብረ ስላስ ለኢትዮ ምኅዳርጋዜጣ/
ላይፍ፡- አንድ ጉዳይ እናንሣ፡፡ በአሜሪካን አገር የሚገኘው የኦርቶዶክስ ሲኖዶስም ኾነ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ አገር መምጣት የለባቸውም በማለት ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይኾንም?
Tigray People Liberation Front Split
(አቶ ስብሓት ዛሬ ለንባብ ከበቃው ላይፍ መጽሔት ጋራ ካደረጉት ቃለ ምልልስ)
አቶ ስብሓት፡- የተናገርኹት እንደ አማኝ እና እንደ ዜጋ የግል አመለካከቴን ነው፡፡ መጀመሪያ ፓትርያሪኩን ከኢትዮጵያ የሚያወጣቸው ምክንያት አልነበረም፡፡ ፓትርያሪኩ ኢሕአዴግ ይነካኛል የሚል እምነት አልነበራቸውም፤ ምክንያቱም እንደማንነካቸው ያውቃሉ፡፡ ብንነካቸው እንኳን መሰየፍ ነበረባቸው ወይም ገዳም ገብተው መመነን ነበረባቸው ወይም ኢየሩሳሌም መሄድ ነበረባቸው፡፡
ይህንን ሁሉ ትተው በመጨረሻ ግን ወደ አሜሪካ ወሰዷቸው፡፡ ይህም ሳያንስ በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ ትልቅ ወንጀል በመፈጸም ሲኖዶስ አቋቋሙ፤ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴን ደገፉ፡፡ እነዚህን ነገሮች ስሰማ ሐሳቤን ገለጽኹ፡፡

ይህ አድራጎት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከግራኝ ከጉዲት የባሰ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡
ላይፍ፡- በአቡኑ ስደት ግን የመንግሥት እጅ እንደነበረበት የቐድሞው ጠቅላይ ሚኒትር አቶ ታምራት ላይኔ በመናገር ቤተ ክርስቲያኒቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ስብሓት፡- /ሣቅ/ ታምራት ቤተ ክርስቲያኒቱን ይቅርታ ሊጠይቅ አይችልም፡፡ ታምራት እንኳን ይህንን ሌላ ለመከታተል ጊዜ የነበረው አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት ግን ኢሕአዴግ አቡኑን የሚነካበት ምክንያት አልነበረውም፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የዕርቅ ምክክር አልነበረበትም፡፡ የአሜሪካውን ሲኖዶስ አውግዞ ሲያበቃ ዕርቅ ለመፈጸም ወደ አሜሪካ መሄዱ ስሕተት ነው፡፡ ዕርቅ ለመፈጸም በማለት ሰዎችን ሲልኩ የነበሩ ቄሶች መሰቀል አለባቸው፡፡ ዕርቅ ከነዚህ ጋራ መደረግ የለበትም፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትገኝበትን ኹኔታ ለፖሊቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚጥሩ ብዙ ናቸው፡፡
ላይፍ፡- እናንተ ሥልጣን እንደያዛችኹ በጳጳስ ላይ ጳጳስ መሾማችኁስ ወንጀል አልነበረም?
አቶ ስብሓት፡- (በሣቅ አለፉት)
ሐራዊ ማስታወሻ – ስለ ‹‹ቀውስ አቀጣጣዩ›› ስብሓት ነጋ፡-
ቀድሞ የህወሓት መሥራችና አሁን የኣረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ አባል አቶ ኣስገደ ገብረ ሥላሴ የዛሬውን አዛውንት የያኔውን የ47 ዓመት ጎልማሳ ኣቦይ ስብሓት ነጋን ሚያዝያ 21 ቀን 1967 ዓ.ም ከሽሬ እንዳሥላሴ ተቀብለው ወደ በረሓ ያወጧቸውና ወደ ጓዶች የቀላቀሏቸው፣ በደፈጣና በፀረ ደፈጣ ውጊያ ያሠለጠኗቸው ‹የትግል አባታቸው› ናቸው፡፡
አቶ ኣስገደ በዚህ ሳምንት በወጣው ኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ÷ አዛውንቱን አቦይ ስብሓትን በአሽሙረኝነት፣ በሤረኛነት እና በተንኰለኛነት ወቅሰዋቸዋል፡፡ አቶ ኣስገደ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ኣቦይ ስብሓት በእርሳቸው አማካነይነት ሠልጥነው ወደ ህወሓት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ቀውሶች (የደደቢት ሕንፍሽፍሽ አንድና ሁለት) ሁሉ ተጠያቂ ያደርጓቸዋል፡፡ ‹‹አሁን ታሪክ የሚያበላሸው ኣቦይ ስብሓት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡. . .የአውራጃ፣ የወረዳ፣ የጎጥ ምንጭ አቶ ስብሓት ነጋ ናቸው፤›› ይላሉ አቶ ኣስገደ፡፡
‹‹አቦይ ስብሓት አሁን ሳያቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን የተመለሱ ይመስለኝ ነበር›› የሚሉት አቶ ኣስገደ÷ ዛሬም ይኹን በትግሉ ወቅት ህወሓት ለሚከተለው ‹‹ፕሪንስፕል›› ኣቦይ ስብሓት አስቀድመው በአሽሙር፣ በተንኰል ንግግር ፍንጭ የሚሰጡ ቀውስ አቀጣጣይ እንደነበሩ ይመሰክሩባቸዋል፡፡ እንዲህም ስለኾነ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙትን አባቶች በፖሊቲከኝነትና በ‹‹አክራሪ እስልምና›› ደጋፊነት የሚወነጅለው የአዛውንቱ ኣቦይ ክሥ እና የስቅላት ፍርድ÷ መንግሥት በውጭ በስደት ባሉ አባቶች ላይ ለወሰዳቸውና ለሚወስዳቸው አቋሞች (የኢቲቪን የዝግጅት ዕቅድ ያስታውሷል) መሠረቱ ይኾን? ብለን እንጠይቃለን፡፡
የኾነው ኾኖ አቶ ኣስገደ ስለ ኣቦይ ስብሃት ነጋ ሰብእና በሰፊው ባስረዱበት የኢትዮ ምኅዳር ጽሑፍ ለአዛውንቱ የለገሡትን ምክር በመጥቀስ ማስታወሻችንን እንቋጭ፡፡ የአቶ አስገደ የምክር ቃል እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹እኔ የምለው፣ ኣቦይ ስብሃት አረጋዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄ ቢቀርባቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢሄዱ፣ ቢቆርቡ፣ የተጣላ ቢያስታርቁ ይሻላቸዋል፡፡ ይሄን አሥምርልኝ፡፡ ርግጥ ኮሚኒስት የምፅዓት ቀን ስትደርስ ነው የሚናዘዘው፤ ቄስ አምጡልኝ የሚለው፡፡ ስለዚህ ኣቦይ ስብሃት ሤራውን ትተው ቢያስታርቁ ይሻላል፡፡
አሁን እኮ እኔ እንኳን ዕድሜዬን 63 አድርጌያለኹ፤ እርሳቸው ደግሞ 84 እና 85 ዓመታቸው ነው፡፡ ስለዚህ እነኚህ ሰዎች ትንሽ ከማንዴላ ለምን አይማሩም? እግዚሃር ያሳያችኹ፡፡ ለኣቦይ ስብሃት ወደ ቤተ ክርስቲያን ግቡ፣ 40 ዓመት ሙሉ ቀውስ አታቀጣጥሉ በሉልኝ፡፡››

No comments:

Post a Comment