ድምፃችን ይሰማ
አቶ ሽመልስ ኡስታዝ አቡበከርን ‹‹አጥፍቶ ጠፊ›› ብለው መዝለፋቸውን ሰምተዋል?
‹‹መንግስት መፅሐፍ ቅዱስንና ቁርአንን ጠቅሶ ክርክር ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡››
የአመቱ ምርጥ ቀልድ
የአመቱ ምርጥ ቀልድ
አቶ ሽመልስ ኢቲቪ ከዶኩመንታሪው በኋላ በስህተት ባስተላለፈው የቪዲዮ ፊልም ውስጥ የኮሚቴያችን ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ በካቴና ተጠፍሮ መታየቱን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ደግሞ ክፋት የተመላበት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ራሴን አጥፍቼ እጠፋለሁ፣ ወደ ጥፋትና ወደ ሽብር ሥራ እገባለው ያለ ሰው ለጥንቃቄ ተግባር ሲባል በካቴና እጁን እንዲታሰር ማድረግ የየትኛውንም ህግ የሚጥስ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ይሄ ወንጀል ነው! አንድን ነጽህና የሚልዮኖች ውክልና ያለው ዜጋ ‹‹አጥፍቶ ጠፊ›› ሲሉ መሳደብ ለአንድ ባለስልጣን አሳፋሪ ነው፡፡ ኡስታዛችን አንድም ቀን እንኳን እንዲህ ያለ ንግግር ተናግሮ አያውቅም፡፡ እጅግ ሰላማዊና ሰላምን ሲሰብክ የቆየ ሰው ነው፡፡ ሁልጊዜም ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው አስተዋይ መሪያችን ነው፡፡ መንግስት መሪዎቻችንን ለማሰር ባሰበበት ወቅት እንኳ እኛ ብንታሰር ከስሜታዊነት ራቁ! ሲል ነው ህዝበ ሙስሊሙን ቃል ያስገባው፡፡ ይህን ለሚሊዮኖች ተምሳሌት የሆነ ሰው ‹‹አጥፍቶ ጠፊ›› ሲሉ መሳደብ ወንጀል ነው – ምን ያደርጋል! ይህን እንኳ የሚያርም የአስተዳደርም ሆነ የፍትህ ስርአት የለም እንጂ፡፡
አቶ ሽመልስ በቃለ መጠይቃቸው ሌላ ቦታ ላይ የተናገሩት ንግግር ደግሞ መንግስት እስልምናን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይመስላል፡፡ ‹‹በየሲዲው ፀብ ቆስቋሽ ፕሮፓጋንዳዎችን የሚያስፈፅሙት፣ በቲቪ አፍሪካ የተለያዩ ቻናሎችን በመጠቀም የሚያሰራጩት እነዚሁ አክራሪዎችና ሽብርተኞች ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸው ውስጥ እንደምናየው ሁሉንም ነገር በባዶ ከመወንጀል ያለፈ ያቀረቡት ማስረጃም የላቸውም፡፡ ሰላማዊ የእስልምና ትምህርት እየሰጠ የሚገኘው ቲቪ አፍሪካ ለምን ኢላማቸው ሆነ? ህገ መንግስታችን የሃይማኖቶችን ሰበካ የማድረግ መብት አስጠብቆ የለም እንዴ? ይህን መብት በመጠቀም ሁሉም ሀይማኖት ሰበካ እያደረገ አማኞቹን ያስተምራል፡፡ ቲቪ አፍሪካም ያደረገው ይህንኑ ሆኖ ሳለ ጸብ ቀስቃሽ እየተባለ ነው፡፡ ጣቢያው ምንድነው ጥፋቱ? ኢትዮጵያ ምድር ላይ እስልምናን መስበክ ክልክል የሚያደርግ አዲስ ህገ መንግስት ሳናውቀው ወጥቶ ይሆን?
ከአቶ ሽመልስ ከማል ቃለ መጠይቅ ውስጥ እስቲ የሚቀጥለውን ንግግር እንመልከት፡፡ ‹‹መንግስት መፅሐፍ ቅዱስንና ቁርአንን ጠቅሶ ክርክር ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ይሄ ምድራዊ መንግስት ነው፡፡ የትኛውንም ሃይማኖት አይደግፍም፡፡ የትኛውንም ሃይማኖት የማይቃወም መንግስት ነው፡፡ አለማዊና ምድራዊ መንግስት ነው፡፡››
እውን ይሄ ሹፈት አይመስልም? የመንግስት ባለስልጣናት በድምጽና በምስል በተቀዱ የስብሰባ ንግግሮቻቸው ውስጥ ‹‹ትክክለኛው የእስልምና አይነት›› አህባሽ ስለመሆኑ ሲተነትኑ አልነበረምን? የእስልምና አስተምህሮቶችን ብፌ ላይ እንደተደረደረ ምግብ እያማረጡ ‹‹ይሄኛው መጤ ነው… ያኛው ነባር ነው!›› እያሉ ሲከፋፍሉ አልነበረምን? ንግግር ብቻ በሆነ…. በተግባርስ ‹‹እኛ የመረጥንላችሁን አይነት ‹‹እስልምና›› ካልተቀበላችሁ የመስጊድ ኢማም መሆን አትችሉም! ቁርአን ማስተማር አትችሉም!›› እያሉ በኃይል ያስባረሯቸው ኢማሞችስ ምን ይበሉ? መንግስት አህባሽ የተባለውን አንጃ ከሊባኖስ አስመጥቶ እኛ ላይ ለመጫን የሚያደርገውን ጥረት በሰላማዊ መንገድ ስለተቃወሙ ብቻ የተደበደቡ፣ የታሰሩ፣ የተገረፉ፣ የተዘረፉ፣ የተገደሉ ስንት ናቸው? ይህን ሁሉ በአይናችን እያየን አቶ ሽመልስ ‹‹መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም›› ሲሉ ስለምን ያሾፉብናል? አመቱን ሙሉ መንግስት ‹‹መስጊድ ገብቶ አልወጣ›› ማለቱን አልሰሙ ይሆን? እንደ ድርጅት ሁሉ አንድ ሰው ‹‹ሙስሊም ነኝ›› ሲል ‹‹የግል ሙስሊም ነህ ወይስ የመንግስት ሙስሊም?›› የሚል የብሶት ቀልድ መጀመሩን አልሰሙ ይሆን?
አቶ ሽመልስ ‹‹ለዘብተኛ ኢማሞችን ካድሬዎች እያሉ እያሳቀቁ የህብረተሰብ ድጋፍ እንዳያገኙ ያደርጋሉ›› ሲሉ ያማረሯቸው ‹‹ጥቂት አክራሪዎች›› ጉዳይም አስገራሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት በመጅሊሱ ላይ ካድሬዎችን እንደሚያስቀምጥ ካወቀ አስርት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይኸው ጉዳይ የኢቲቪ ህገ ወጥ ዶኩመንታሪ ላይ እንኳ ሳይጠቀስ አላለፈም! አቶ ሽመልስ ይህንን ሁሉ አመታት የት ነው ሳይሰሙት የቆዩት?
ሌላም እንጨምር፡፡ አቶ ሽመልስ ህዝበ ሙስሊሙ የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ ‹‹መስሚያ ጆሮ የለኝም›› በማለቱ ምሬታቸውን ሲገልጹ እንዲህ ነበር ያሉት፡- ‹‹የአሁኖቹ አክራሪዎችና የፕሮፓጋንዳ ኔትወርካቸው የኢቲቪን ማስታወቂያ ከመጀመሪያው አይተው ስለሚያውቁት ከተጋለጠ መረጃው እንዴት እርቃናቸውን እንደሚያስቀራቸው ስለሚያውቁት ሙስሊሙ ህብረተሰብ እንዳይሰማው፣ እንዳይከታተለው ‹‹አትዩ›› የሚል ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ምን ያህል ፀረ-ዴሞክራሲ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ህብረተሰቡ የራሱን መረጃ ወስዶ ነፃ በሆነ መንገድ የራሱን ብያኔ እንዲሰጥ ሳይሆን ከመረጃ ዓይኑን፣ ጆሮውን ሸፍነው ራሳቸው በሚግቱበት መንገድ ግተው ሊጋልቡት የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡››
ይገርማል! በአገሪቱ ውስጥ የመንግስትን አደገኛ የሃይማኖት ፖሊሲ የሚወቅስ እና የሚዘግብ አንድ እንኳ ኢስላማዊ ጋዜጣ እና መጽሄት እንዳይታተም ያገደ መንግስት በድፍረት ዞሮ ሌሎችን ‹‹በጸረ-ዴሞክራሲያዊነት›› ሲወቅስ በእርግጥም ይገርማል! ሙስሊም ጋዜጠኞችን እና አርቲስቶችን ከተቃውሞው መሪዎች ጋር በእስር ቤት አጉረው ‹‹ሽብርተኞች ናቸው›› የሚሉን ራሳቸው ሆነው ሳለ ‹‹የመንግስት ድምጽ እንዳይሰማ አደረጋችሁ›› ሲሉ ይወቅሱናል፡፡ በቃ ብሄራዊ ሹፈቱ ማብቂያ የለውም ማለት ነው?
በጥቅሉ ቃለ መጠይቁ እስካሁን ያነሳናቸውን በመሰሉ ሀሰቦች የተሞላ ነበር፡፡ ሁሉንም መልስ መስጠት ጊዜ ስለሚወስድ ቀሪውን በፕሮፓጋንዳ ለማይሸወደው አንባቢ ትተነዋል፡፡ ችላ የማንለው ግን ግለሰቡ ከኮሚቴዎቻችን ጠበቆች አንዱ በሆኑት አቶ ተማም አባ ቡልጉ ላይ የሰነዘሩት ዛቻ እና ማስፈራሪያ ነው፡፡ ‹‹ህግ የበላይ ነው›› በሚባልበት ማንኛውም ስርአት ውስጥ ከሳሽ እንዳለ ሁሉ ጠበቃ መኖር አለበት፡፡ ተከሳሹ ጠበቃ የማቆም አቅም ባይኖረው እንኳን መንግስት በራሱ ወጪ ጠበቃ ሊያቆምለት ይገደዳል፡፡ ህጉ ይህ ሆኖ ሳለ መሪዎቻችን በሐሰት ‹‹ሽብርተኛ›› ተብለው መበደላቸው ሳያንስ ጠበቆቻቸው ላይ ማስፈራሪያ መሰንዘር ለከት ያለፈ ተግባር ነው፡፡ ባንድ ፊቱ ‹‹ህግ የሚባል ነገር አያስፈልግም፤ የፈለግነውን በፈለግነው መልኩ ወንጅለን በእስር እናበሰብሳለን›› የሚሉን ከሆነ መልካም ነው፡፡ አሊያ ግን እየፈጸሙ ካሉት ጠበቆችን የማስፈራራት ህገ ወጥ ተግባር በአስቸኳይ ይቆጠቡ!
የትኛውም አይነት ፊልም ቢሰራ፣ ድርሰት ቢደረስ ትግላችን በርካሽ ፕሮፓጋንዳ አይፈታም! ድምጻችን አንድ እና ተመሳሳይ ነው… ንጹህ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎቻችን ይመለሱ! መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን! መሪዎቻችን ይፈቱ! ይህንን በትክክል ሰምቶ መረዳት ይህን ያህል ይከብዳልን?
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!
አላሁ አክበር
No comments:
Post a Comment