ትዕግስቱ አወሉ እንደ አየለ ጫሚሶ
የዛሬ አስር ዓመት “የሕዝብ ሱናሚ” እያለ ሲምል ሲገዘት የነበረው ህወሃት ሱናሚው ወደ እርሱ እየጎረፈ ሲመጣ በረገገ፡፡ መፍትሔ በጠብመንጃ አፈሙዝና በብረት ብቻ እንደሆነ የሚያምነው ህወሃት በረሃ የለመደውን በትሩን አነሳ፤ ንጹሃንን ጨፈጨፈ፤ ደም አፈሰሰ፤ ኢትዮጵያን ወደ እስርቤትነት ቀየራት፡፡ ትዕዛዙን በቀጥታ የሰጡት “ባለራዕዩ” ለፍርድ ሳይቀርቡ “እንደጀመርን እንጨርሰዋለን” ያሉትን ሰፊውን ሕዝብ ሳይጨርሱት እንደ ክዳን ቆርኪ ተስፈነጠሩት፤ ላይመለሱ ሄዱ፡፡
የዛሬ አስር ዓመት የቅንጅት አካሄድ ያስፈራው ህወሃት ጉዳዩን ለራሱ ለፓርቲውና ለሕዝብ ከመስጠት ይልቅ ደም መቃባት ውስጥ ገባ፡፡ ፓርቲው የነበረበት የውስጥ ችግር እንዳለ ሆኖ የፈሪ በትር የዘረጋው ህወሃት የገደለውን ገድሎ ከጨረሰ እና የኢትዮጵያን መሬት በደምና በእናቶች እምባ እንደገና ካጨቀየ በኋላ ቅንጅትን የማፍረስ ተግባሩን በዕቅድ ይዞ በይፋ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ግምባር ቀደም ተሰላፊው የተቋም ባንዳ “ምርጫ ቦርድን”፤ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ በተለይ ሁለት ግለሰቦችን አሰለፈ፡፡ ዘመቻ “ቅንጅትን መግደል” ተጀመረ፡፡
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ምንም በማያሻማ ሁኔታ በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ያማሞቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) ለሚገኙት አለቆቻቸው “THE ETHIOPIAN GOVERNMENT CHEWS THE CUD” (የኢትዮጵያ መንግሥት ቅንጅትን አኘከው) በሚል ርዕስ የጻፉት እንዲህ ይነበባል፤