Thursday, January 29, 2015

መልእክት አለኝ ለአንድነት አመራሮች እና አባላት

ግርማ ካሳ


የሕወሃት የደህንነት ሃላፊዎች፣ አንድነት መወዳደር የለበትም የሚል ዉሳኔ ካሳለፉ ቆይተዋል። ከዚህ በፊት፣ ፓርቲ እንደ ኢንጂነር ግዛቸው ባሉ ደካማ አመራር ሥር ስለነበረ ፣ የትም ገፍቶ እንደማይሄድ ተረድተው ነበር። ኢንጂነሩ በአባላት ግፊት ከሃላፊነታቸው ተነሱ። አዲስ ፣ ለዉጥ ፈላጊ አመራር መጣ። ችግሩ የአመራር ችግር ስለነበረ፣ አዲሱ አመራር ሃላፊነቱን በያዘ በሶስት ወር ጊዜ ዉስጥ ብቻ፣ የአገሪቷን ፖለቲካ አነቃነቀ። ፓርቲው ተቀባይነቱ ከመቼዉም ጊዜ በላይ አደገ። ይህን ጊዜ አይን ባወጣ መልኩ፣ አይኖቻቸዉን በጨው አጥበው፣ አንድነት ፓርቲ አገዱት። እኔ የምሬ ለነርሱ አዘንኩላቸው !!!! አቤት፣ አቤት፣ አቤት ፣ ……



ነጥብ አንድ። የዛሬው የሕወሃት ዉሳኔ የአንድነቶች የሥራ ዉጤት መሆኑን መረሳት የለበትም። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገዛዙ እንዲዋረድና መሳቂያ እንዲሆን አድርገዉታል። ሕወሃት ጭንቅላት ባላቸው ሰዎች ሳይሆን፣ ፉዞ በሆኑ ሰዎች እየተመራ እንደሆን አለም አውቆታል። የሚቀበሩበትን መቃብር ቆፍረዋል።


ነጥብ ሁለት። አንድነቶች ከዚህ በፍትም በቅንጅት ሥር ሲታገሉ ነበር። ቁም ነገሩ ስሙ አይደለም። የትግልና የጥንካሬ ዉጤት የሕወሃት ምርጫ ቦርድ በሚሰጠው ወረቀት ወይንም እውቅና አይወሰነም። ወደ ዘጠና ምናምን የሚሆኑ ምናምንቴ ፓርቲ ተብዬዎች አሉ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ። ከዚያ ዉስጥ ከአራት፣ አምስቱ በስተቀር ሌሎችን የሚያውቅ አለ ? የለም። አያችሁ የምርጫ ቦርድ ወረቀቶች ዘጠና ምናምን ፓርቲዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ የሚረቡ አይደሉም።

አንድ ፓርቲ ጥንካሬው በሕዝብ ያለው ድጋፍ ነው። የአንድነት ፓርቲ ስሙን ቢወስዱም፣ ደጋፊዉንና አባላቱን ሊወስዱ አይችሉም። ለዉጥ የሚያመጣው ደግሞ ሕዝቡና ደጋፊው ነው። በመሆኑም ዛሬ የሆነውን ነገር እንደ ድል በመቁጠር የሚቀጥለውን ጉዟችንን በጥንቃቄና በማስተዋል፣ በበለጠ ቁርጠኝነት ለማድረግ መነሳት አለብን። ከም፤እራፍ አንድ ወደ ምእራፍ ሁለት ተሸጋግረናል።

እነርሱ ያለፈው እሁድ አስከፊ ድብደባ ፈጸመው ሽፎቶችና ወንበዴዎች መሆናቸውን ሲያሳዩን፣ እነሱ ዛሬ ስማችንን ወስደው የለየላቸው ዘርፊዎች መሆናቸዉን ሲያሳዩን ፣ አላማቸው አንድ ብቻ ነው። እኛ ፈርተን እንድንቀመጥና እነርሱ አገራችንን እንደፈለጉት እንዲያደረጉ። አላማቸው ከዚህ በኋላ ለ25 እና 50 አመት መግዛት ነው። አላማቸው ሱልጣን ኢብራሂም አሰብን ለጣሊያኖች እንደሸጠው፣ ገንዘብ ተቀብለው ኢትዮጵያን ለቻይናና ለአረቦች መሸጥ ነው። አንድ ያለተገነዘቡት ነገር ቢኖር ዘመኑ 2007 እንጂ 1997 አለመሆኑን ነው። የአሁኑ ትዉል የነርሱን አገዛዝ ለመሸከም አቅምና ትግስት እንደሌለው ነው። ከመቼዉም ጊዜ በላይ ሕዝቡ የነርሱ ነገር እንዳስጠላው ነው። በርግጥ ይሄ እያደረጉት ያለው ነገር የነርሱ መጨረሻ ጅማሬ ነው። አንዳንዶች አርቆ ካለማየት ሁሉ ነገር አበቃ ሊሉ ይችላሉ። አይደለም። ገና አሁን ጀመረ።

እንግዲህ ላደረጋችሁትና ለከፈላችሁት መስዋእትነት ያለኝ ትልቅ አድናቆት እየገለጽኩ፣ ድርጅታዊ መዋቅራችሁን፣ አባላቶቻችሁን እና ደጋፊዎችሁን ይዛቹህ፣ ሌሎች በፖለቲክ ፕሮግራም ከሚስሟሟችሁ ድርጅቶች ጋር በመሆን ትግሉ እንድታጧጥፉ በአብሮት እጠይቃለሁ። መኢአድ አለ። ሰማያዊም አለ።

በድጋሚ እላለሁ። እንደ አንድ ኢትዮዮጵያ ትልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ኮርቼባቹሃለሁ። ባላችሁበት ቦታ እግዚአብሄር ያክብርልኝ!!!

No comments:

Post a Comment