Tuesday, April 15, 2014

ያገር ጉዳይ ሲነሳ

                        ያገር ጉዳይ ሲነሳ        ከምናሴ መስፍን
                                                                                       almazmina@yahoo.com

«  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝነሽ ተላላ          
የሞተልሽ ቀርቶ  የገደለሽ በላ »
ቀኝ ጌታ  ዮፍታሄ ንጉሴ
(1887 1939)

የምድሪቷ ብእረኞች ቀድሞ የማየት አቅም ያላቸው ከአጥብያ  ኮኮብ ብርሃን የበለጠ ተወረውረው፣ ነገን አይተዋል ከሚባሉት ቀደምት ፈርጦች መካከል ተጠቃሹ ዮፍታሄ ንጉሤ አንዱ ነበሩ፡፡   ታሪክ ራሱን   ሲደግም ማየት አለመታደል በመሆኑ፣ እኒህን ጎምቱ ደራሲ የነገራችን መነሻ አደረኳቸው ።

ከሀገራችን የታሪክ ውቅያኖስ በማንኪያ ስንጨልፍለት ብዙ ያለፉ ዘመናት ክፉና በጎ ትዝታዎች ከፊታችን ድቅን ያላሉ፡፡ በኢትዮጵያና በፋሽስት ኢጣሊያ ጦርነት ወቅት የነበረውም እውነታ ላብነት ያህል የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሄ ዘመን ከአገር ፍቅርና ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምና እራስ ወዳድነት ይቅደም የሚለው አስተሳሰብ በጉልህ ተንጸባርቆ የታየበት ክፉ ወቅት ስለነበረ ሁሌም ይታወሰናል፡፡ ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ እንዲሉ  በማይጨውና በተንቤን ኢትዮጵያውያን ተዋጊዎች ከመሶሎኒ  ታንክ ጋር በጎራዴ ተፋልመው በመርዝ ጋዝ  


የመፈታታቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ እጣ ፈንታ የተዳረጉት በዘመናዊ የጦር መሣሪያ በመበለጣቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከጠላት ጋር ባበሩ ሆድ አደሮች ሴራ ጭምር መሆኑን ታሪክ ዘግቦታል፡፡ ዛሬም ታሪክ ራሱን ይደግም ዘንድ እንዲሉ ሆነና የወገን ጠላቶች ከጠላት ጎር ውስጥ ሰልፋቸውን አሳምረው፤ እናት አገራቸውን ለመውጋትና ለመበደል በቅተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጭንብል “Mask”  ያጠለቁ ላልረባ ጥቅም ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን የሸጡ ሆድ አዳሪ ግለሰቦች፣ የሕዝብን የዲሞክራሲና የነፃነት ትግል ለማዳከም ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይገቡበት ቀዳዳ አልነበራቸውም።  አገር መውደድን በአፍ ጉቦነት እየከፈሉ በተግባር ግን አገርን የሚያዋርድና የሚገል አሳፋሪ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ለአገርና ለሕዝብ አሳቢ መስለው “በእንብላው ለጊዜው” እስታይል ሆዳቸውን እየሞሉ ሰፊውን ምስኪን ሕዝብ ያንገላቱታለ፣ ይበድሉታልም፡፡  ደግሞም የወያኔን እድሜ ዘመን እያራዘሙ 

 በወንድሞች መካከል ጠብን እየዘሩ ትግሉን ለማዳከም ሌት ተቀን ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ለነዚህ ሆድ አደሮች ሴራ ሳይንበረከክ፣ በዘር፥ በጉሳና፥ በሀይማኖት ሳይከፋፈል እነሆ ትግሉን ቀጥሏል፡፡
ወያኔ ከአባቶቹ የወረሰውን የባንዳነት መሰሪ ተግባር እያከናወነ፣ በተባባሪዎቹ ሆድ አዳሪዎች እየታገዘ የአገርን ንብረትና ሀብት ይዘርፋል፡፡ ያዘርፋልም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያቆም፣ ለምዕራባውያን ካፒታሊስቶች በሩን ከፍቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት እያዘረፈ ይገኛል፡፡ ከነሱም የተራረፈውን ፍርፋሪ ለሆድ አዳሪዎች ይበትናል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ባለማሰብ ነገ ለሚያልፈው ከንቱ ሕይወታቸው የማያልፍ አስነዋሪ ስምና ተግባር ትተው ያልፉሉ።  

አገር ወዳዱ ዜጋ በረሀብ ፥ በኑሮ ውድነትና በስደት በያገሩ በየቀዬው ይረግፋል። ሀገሬን ባዩ ለስደት ለወህኒ ሲዳረግ፤ አደርባዩ ደግሞ በአንፃሩ ለሹመት ሲቋምጥ የዘመናችን አስደንጋጭ ክስተት ሆኖ ይስተዋላል። እናም ይህንን ዘረኛና አስከፊ ወያኔ ስርዓት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታግሎ መጣልና አገርን ነጻ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ደሞ አንድ የቆየ  አባባልን ሁሌም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
እንዲህ ይላል…
             “ጠላትማ መቼም ምንጊዜም ጠላት ነው
              አስቀድሞ መግደል አሾክዋኪውን ነው”
                                             ኢትዮጵያን ለዘላለም ትኑር !!!
                                              

             


    



          

1 comment: