Monday, May 13, 2013

የኢህአፓ (ዴሞክራሲያዊ) ድጋፍ መግለጫ ለተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ


 

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP ዴሞክራሲያዊ/Democratic)
ግንቦት ፫ ቀን ፪ ሺህ ፭ ዓ. ም
የኢትዮጵያ ሕዝብ የተነጠቀውን መብቱን በትግሉ ይቀዳጀው!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገብጋቢ የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ጥያቄዎቹን ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ. ም አዲስ አበባ ውስጥ በሰላማዊ ሰልፍ በአንድ ድምፅ ለማሰማት መነሳሳቱን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ዴሞክራሲያዊ) ከልብ ይደግፋል።Ethiopian People's Revolutionary Party (EPRP Democratic)
በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራውን ሰልፍ የምንደግፈው አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች የችግሮቹ ሰለባ በሆነው ሕዝብ በራሱ በአደባባይ በግልጽና በአንድነት በሰላማዊ መንገድና በይፋም ስለሚገለጹ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥው አምባገነናዊ ቡድን መብቱንና ሰላሙን አጥቷል። ሕዝቡ ሰላም የሚያገኘው፣ ክብሩንና መብቱን ሊያስመልስ የሚችለው፣ በተባበረ ትግሉ ብቻ ነውና የተደራጁ ኃይሎች በሙሉ ከጎኑ ሊቆሙ ይገባል እንላለን። ሕዝቡ አምባገነኑን ገዥ ኃይል “የተቃውሞ ሰልፍ እንድናደርግ ፍቀድልን!” ብሎ ሲጠይቅ የሚጠበቀው የእምቢታ ምላሽ ሲመጣ ሳይደናገጥ የተነጠቀውን መብቱን፣ በሰልፍ ጭምር ሃሳቡን በነፃ የመግለጽ መብቱ የራሱ ነውና ዛሬም ሊጠቀምበት ይገባል እንላለን።

ሰልፍ ከአንድ አማካይ ሥፍራ ሊጀመር ይችላል። መፈክሮቹ ሊበዙም ሊያንሱም ይችላሉ። ጉልህ የሆኑትን የሕዝብ ጥያቄዎች ማንሳት ግን የግድ ነው። ከግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ. ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ሀገሮችና ከተወሰኑ ዓለም አቀፍ ተቋሞችና ድርጅቶችም እንግዶች ስለሚኖሩ፣ የሕዝቡ ድምፅ ጎልቶ ሊሰማ የሚችልበት ምቹ አጋጣሚ ነው።
የሕዝቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊገደቡ አይገባም። ሃሳብን በነፃ የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ በነፃነት የመዘዋወር፣ ማንኛውም ዜጋ በመረጠው ሥፍራ የመኖር፣ የፈለገውን ዕምነት የመከተልና እምነቱን በነፃነት የማስፋፋት፣ ማንኛውም ዜጋ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመያዝና መኖሪያ ቤቱ ያለመፈተሽ፣ ሠርቶ የመኖር፣ የንብረት ባለቤት የመሆን፣
እንዲሁም የሥልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ የመምረጥና የመመረጥ መብትና ነፃነቶችን ተቀምቷልና በትግሉ ሊጎናጸፋቸው ይገባል። ዛሬ ሀገራችን ሕግና ፍትኅ የጠፉባት ሀገር ሆናለች። የሕግ የበላይነት እንዲሁም እኩልነትና ፍትኅ የሰፈነባት፣ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የምንፈልግ ሁሉ ያለመወላወል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመን የትግሉና የመስዋዕትነቱም ተካፋዮች ልንሆን ይገባል።
በፀረ-ሽብርተኝነት ስያሜ የወጣው ሕዝብን እያሸበረ ያለው ዓዋጅ በአስቸኳይ ይነሳ!
የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዚጠኞችና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች በሙሉ አሁኑኑ ይፈቱ!
“የነፃው ፕሬስ መተዳደሪያ ሕግ” በሚል ስያሜ የወጣው አፋኝ ሕግ በአስቸኳይ ይሻር!
በአማራው ብሄረሰብ ተወላጆች፣ በጋምቤላ፤ በአኝዋኮችና በሌሎችም ዜጎች ላይ እየተፈፀሙ ያሉት ሰቆቃዎች፤ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች የማፈናቀል፣ ዘር የማጽዳት፣ ዘር የማጥፋት አሰቃቂ ተግባሮች በአስቸኳይ ይቁሙ! ለተጎጂዎች ካሣ ይከፈል! ወንጀለኞቹ ለፍርድ ይቅረቡ!
በዕምነት ተቋሞች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው እመቃና ወከባ በአስቸኳይ ይቁም! የታሰሩት የምዕመናኑ ተወካዮችና መሪዎች ባፋጣኝ ይፈቱ!
ፓትሪያርክ ከመሾም ጀምሮ፣ ገዳማትን እስከ መድፈርና ማፍረስ፣ ምዕመናንን መግደልና ባህታዊያኑን መደብደብ፣ ማሠርና ማሰቃየት፣ ያብቁ! አገዛዙ በዕምነት ተቋማቱ ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ያቁም!
የገዥው ቡድን የሀገራችንን ለም መሬት ቆርሶ ለሱዳን መንግሥት ለመስጠት ያተደረገው ሚስጥራዊ ውል መሰረዝ አለበት! ለባዕዳን ከበርቴዎች በረጅም ጊዜ ኪራይ ስም የተቸበቸበው የእርሻ መሬት ለሀገራችን ኤኮኖሚ እጅግ አስፈላጊ ነውና ውሎቹ በአስቸኳይ ይሻሩ!
ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ከሕዝቡ ጎን እንቁም!
የመከላከያና የፖሊስ ኃይል በሚባሉት ተቋሞች ውስጥ ያላችሁት ሁሉ ከሕዝብ ጎን ቁሙ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ትግሉ ያለጥርጥር ያቸንፋል!

No comments:

Post a Comment