መግቢያ፦ በሜዳ የሚደረገው ትግል እየጠነከረ ሲሄድና ዳሩ መሃል እየሆነ ሲመጣ ነገሮች ሁሉ አዳጋች ሲሆኑ ገዥዎች በሥልጣን ለመሰንበት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ደርግ ይወስድ ከነበረው ርምጃ በቂ ትምህርት አግኝተናል። በጭፍን አስተሳሰብ ዐይኑ ያልወደደውን ሁሉ ወደ እስር ማጋዝና ነጻ ርምጃ በሚል ፈሊጥ በጅምላ ሕዝብ ጨፍጭፏል። «የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት»ሳይባል የተገደሉትን ብርቅየ የኢትዮጵያ ልጆችማ ቤት ይቁጠራቸው።
ህወሃት አሁን የሚገኘበት ደረጃ የሚያሳየውም ያነውኑ ነው። በሰላማዊ መንገድ መታገል በራሱ በህወሃት ሕግ የተፈቀደ ነበር። ነገር ግን አንዲት ጠጠር ሳይወረውሩና ቅጠል ሳይበጥሱ ሕጉ በሚፈቅድላቸው መንገድ በመሄድ እየታገሉ ባሉ የተቃዋሚ ኃይሎች ላይ ህወሃት ያደረሰባቸውን እንግልት እስራትና ንብረት ዘረፋ ተመልክተናል። በአብዛኛው እኔ በመጣሁበት መንገድ ካልመጣችሁ በማለት ገፊ ሁኔታዎችን እየተነኮሰም ነው። የሰላማዊ ትግሉን እንዳይቻል አድርጐታል እንጅ ቢቻል በሰላማዊ መንገድ ታግሎ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን መረከብ ወይም ማስረከብ የ21ኛው መቶ ዓመት ሥልጡን ህዝብ ጨዋ ሥነ-ምግባር ነበር። እነዚህ የኛ ድናቁርቶች ግን በሕገ-አራዊት እየተመሩ ነገር የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም።