ሰሞኑን ከአገር ቤት አንዲት እናት ልጃቸውን ሊጠይቁ መተው ነበር። ልጃቸው የባለቤቴ ጓደኛ ነች።..የኔም ጓደኛ!…እኒህ አናት አንደበተ ርቱእና ተደምጠው የማይጠገቡ ጨዋታ አዋቂ ቀልደኛም ናቸው። ሑሉም ነገር የገባቸው ፍጹም ፖለቲካ አዋቂ ብሩህ እናት ናቸው። ጨዋታቸው ንግግራቸው ሁሉ ይማርካል። ሰማንያ አመት አይሞሉም። ጥንክር ያሉ፤ የነቁ ፍጹም ጤናማ እናት ናቸው።
ወይን ቢጤ ገዛሁና ባለቤቴ ድፎ ዳቦ ጋግራ (እናቶች አዚህ አገር ሲመጡ ድፎ ዳቦ ሲቀርብላቸው ደስ እንደሚላቸው ታውቃለች) እንኳን ደህና መጡ ልንል ሄድን።
ለሁለት ሰአት ያህል አብሬ ስቆይ ከናታችን የገበየሁት ትምህርትና ቁም ነገር በቀላል የሚገመት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ እየጠላቸው ዛሬ ስልጣን ላይ የተጣበቁት የወያኔ ደናቁርት፤
የኢትዮጵያን ህዝብ ምንም አያውቅም ብለው፤ የሚገምቱትና የሚንቁት፤ወደ ታች ወደ ህብረተሰቡ ዝቅ ብለው፤ስለነሱ አገዛዝ፤ ስለ መልካም አስተዳደር ያለውን ግንዛቤ ቢረዱ ምን ያህል ከህብረተሰቡ ኋላ ኋላ እየሄዱ እንመራሀለን እንደሚሉ በተረዱና ባፈሩ ይበጃቸው ነበር።

እኒህ እናት ድህነትን እኩል ያካፈለን ደርግ ተሻለ ነው ነው የሚሉት፤ “እነዚህ ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቅ ሆነዋል። ደርግ አንዱን ልጅ አንዱን እንጀራ ልጅ አላደረገንም። ቢበድለንም አልለያየንም።”
ጎዳና ላይ ለፈሰሱ ለማኝ ህጻናትና ወላጆች ዘወትር ያለቅሳሉ። ኑሮአቸውን የከተማው ቆሻ ክምር ላይ የመሰረቱ ወላጆችና ልጆች ያስለቅሷቸዋል። “ይሄ ሁሉ ፎቅ ይገነባል። የእያንዳንዱን ፎቅ ባለቤት አስር አስር ልጅ ከጎዳና ወስዶ እንዲያሳድግ ቢያስገድዱት ጽድቅ ነበር። ላለው ሰው ምንም ማለት አይደለም” ይላሉ።