Monday, March 4, 2013

ከኬኒያው ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ምን እንማራለን?



East Arican Kenya election 2013
ለውጥ ፈላጊ ኬንያዊያን መራጮች ደምጽ ለመሰጠት ተራቸውን ሲጠባበቁ
ህዝባዊ  ምርጫዎች  በመጡ ቁጥር ስልጣኑን እነማን ይርከባሉ? ምርጫው ምን አዲስ  ነገር ይፈጥርልን ይሆን? ምርጫው ሰላም ወይም  አለመረጋጋት … ወዘተ ይቀሰቀስ ይሆን? የሚሉ መሰል  ጥያቄዎች በበርካታ መራጮች  አይምሮ ውስጥ መመላለሱ የተለመደ ነው፡፡
ከአምስት አመት (2007\2008 እ ኤ አ) በፊት ተካሄዶ  በነበረው  ፕሬዜዳንታዊ  ምርጫ ሳቢያ  ከ1300 በላይ ዜጎቿን ያጣች ፡ከ600ሺህ በላይ ዜጎቿ የተፈናቀሉባት  እና   በቤሊዮኖች  የአሜሪካ ዶላሮች  የሚገመቱ ንብረቶች  የወደሙባት  ጎረቤት አገር  ኬኒያ  በያዝነው  የፈረንጆቹ መጋቢት 4 2013 እኤአ ፕሬዜዳንታዊ  ምርጫ አድርጋለች፡፡ ከአንድ  ሳምንት በፊት በጋዜጠኞች አዘጋጅነት  ስምንት እጩ ፕሬዜዳንታዊ  ተመራጮች  ባደረጉት  3 ሰአት  የፈጀ የመጀመሪያው ዙር  ክርክር  በ34  ራዲዮኖች  እና  ስምንት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች  በቀጥታ ተተላልፋል፡፡ ይህ ከትምህርት  ፖሊሲ  አንስቶ  እስከ የዘር ማጥፋት  ወንጀል  ክስ  ድረስ  ያካተተው  ክርክር  ከ40ሚሊዮን  በላይ የሚገመተው  የኬኒያ  ህዝብን  ቀልብ ከመሳብ አልፎ አለማቀፋዊ  ትኩርትን  መሳቡ አልቀረም፡፡

በዚህ የጦፈ ክርክር ላይ እጩ ፕሬዜዳንታዊ ተመራጮቹ ከተሰጣቸው  ጊዜ ሲያልፉ ወይም  ለጥያቄው  ተገቢ ምላሽ ሲያጡ  ተናጋሪዎቹን በማቋረጥ  ተከታታይ ጥያቄዎችን   ያለ ፍርሃት በመደርደር (እንደ አስፈላጊነቱ ) በማድረጋቸው  አወያዮቹ  (ሞደሬተሮቹ) ከፍተኛ  ሚና  ተጫውተዋል፡፡ የወዳጆች  መገናኛ ብዙሃናት  የሆኑት  አነ ፌስ ቡክ እና ቲዊተርም ቢሆኑ  በአስተያየት ሰጬዎች ተጨናንቀው ነበር  የሰነበቱት ፡፡ የበርካታ  ኬኒያዊያን አንገት  ያስደፋው  እና ቁስሉ  እስከ ዛሬ ድረስ  ያልደረቀው  የ ድህረ 2007\2008 እኤአ ምርጫ መዘዝ በሰሞኑ የምረጡኝ ዘመቻ  ክርክር  ላይ መነሳቱ አልቀረም፡፡ በአይነ ቁራኛ  የሚተያዩት እና  በሰሞኑ  ምርጫ ላይ  የአሸናፊነቱ እድል እንዳላቸው   ሰፊ  ግምት  ተሰጥቷቸው  የነበሩት   ጠ\ሚ\ር ሪያላ ኦዲንጋ  እና   የኬኒያ መሰራች  እና የመጀመሪያው ፕሬዜዳንት የነበሩት ጆሞ ኬኔያታ  ወንድ ልጅ የሆኑት   ኡሁሩ ኬኔያታ ያለፈው ቅራኔያቸውን  እና ልዩነታቸውን  ወደጎን በማድረግ :  ከጥላቻ እና ከከፋፋይነት   አመለካከት ይልቅ  በአገር ጉዳይ አብሮ መስራት  ጠቀሜታ  እንዳለው  በተለያዩ  መድረኮች  ላይ  የተናገሩ  ሲሆን  ያለፈውን  ቁርቋሶ በተመለከተ እጃቸው አለበት  ተብልው   እስከ አሁን ድረስ ከተከሰሱት  14 ሰዎች  መካከል  አንዱ የሆኑት  እጩ ፕሬዜዳንት ኡሁሩ  ኬኔያታ “ ፕሬዜዳንት   ሆነው ቢመረጡ በሆላንዷ   ዘ- ሄግ  ከተማ  በተሰየመው   የአለማቀፉ የወንጅለኞች ችሎት
(ICC) የቀረበቦትን  የዘር ማጥፋት  ውንጀላን እንዴት ያደረጋሉ?” ለሚለው የሞደሬተሩ (አወያዩ) ጥያቄ ሲመልሱ “የኬኒያ ህዝብ እንዳገለግለው ከመረጠኝ  በ ዘ- ሄግ ላይ የቀረበብኝ ውንጀላን  በተመለከተ  ተሟግቼ እራሴን ነጻ አደርጋለሁ” ሲሉ  ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
በምረጡኝ  ክርክሩ ላይ  የተሳተፉት ጠ\ሚ\ር ኦዲንጋ  ለጥቅ አድርገው “  ዘ- ሄግ  ላይ ሆኖ  አገርን በስካይ ፔ(ኢንተርኔት አማካኝነት ) መምራት ከባድ ይመስለኛል ፡፡ተቃዋሚ ነን የሚሉ  ወገኖች  ካግበሰበሱት ሰፋፊ መሬት ጥቂቱን እንኳን  ለደሃው ህዝብ ቢያካፍሉ?  በማለት  ታዋቂው ፎርቢስ መጽሄት  በቅርቡ የኬኔያው ቁጥር አንድ  ቱጃር ሲል የሰየማቸው  ኡሁሩ ኬኔያታን  በነገር ወረፍ አድርገዋቸዋል፡፡   በነገራችን ላይ ኡሁሩ ኬኔያታ እና የጥምረት አጋራቸው  የሆኑት ዊሌየም ሩቶ  በ ዘ- ሄግ  ላይ የተረመሰረተባቸው ክስ አነርሱን ከፖለቲካው  መድረክ ለማባረረ በስልጣን ላይ ባለው  ገዤ መንግስት እና በምእራባዊያን የተወጠነባቸው  ሴራ አንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን የተሰበሰቡ  ቅድመ የህዝብ የምርጫ አስተያየቶች እንዳመለከቱት ምርጫው  ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ  ቢካሄድ  ኖሮ ኡሁሩ ኬኔያታ  ጠ\ሚ\ር ኦዲንጋን በ740 ሺህ ድምጽ አንደሚያሸንፋቸው  የምርጫ ተንታኞች ተንበየው  ነበር ፡፡ ያለፈውን  ፕሬዜዳንታዊ ምርጫን ተከትሎ  ኬኔያ በደረሰባት  የፖለቲካዊ  ፡የኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ  ቀውስ ሳቢያ  አለማቀፉ ማህበረሰብ  በተለይ ደግሞ የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሃፊ  የሆኑት  ጋናዊው ኮፌ አናን አማካኝነት  የተካሄደው  የሸምጋይነት  ጥረት  የተነሳ በጡረታ ተሰናባቹ በፕሬዜዳንት  ማዋዬ ኬባኬ  እና  በተቀናቃኛቸው የአሁኑ ጠ\ሚ\ር ኦዲንጋ መካከል  ጥምር መንግስት  ለማቋቋም የተገደደችው ጎረቤት አገር   ኬኔያ ህገመን ግስቷን   በአዲስ መልክ  በማሻሻል፡የፍትህ ስርአቷ ገለልተኛ  እንዲሆን ጥርት በማድረግ  በኩል  እና  ዜጎቿን ለብቀላ የሚጋብዙ  ቃላትን እና  ብሄርን በብሄር ላይ ለአመጻ የሚያነሳሱ አስተያየቶችን  ከመጠቀም የሚያግድ  የቁጥጥር ኮሚሽን  በማቋቋም  የሰሞኑ ምርጫ 2013 እኤአ የተሻለ  ምርጫ ለማድረግ  ውስጣዊ  ጥረቶችን  ብታደርግም  ምርጫ ይሳካ ዘንድ  ያለፈውን ደህረ ምርጫ ይመሰለ ዘግናኝ፡ የብቀላ  እና ኤ-ዲሞክራሲያዊ እርምጃ እንዳይደገም  እና  የናይሮቤ መንግስት ዜጎቹን እንዲታደግ  የአለማቀፉ ማህበረሰብ   ከማሰጠንቀቀ አልቦዘንም፡፡  በወላጅ አባታቸው በኩል ኬኔያዊ ዝርያ ያላቸው    የአሜሪካው   ፕሬዜዳንት  ባራክ ኦባማ  ሰሞኑን  ለኬኔያ ህዝብ በላኩት  የቬዲዮ  መልእክት ኬኔያዊያን  ነጻ ፡ዴሞክራሲያዊ  እና  የሰከነ  ምርጫ እንዲያካሄዱ ተማጽነዋል፡፡ የኬኔያ ቀኝ ገዢ  የነበረችው እንግሊዝም  በበኩሏ በምረጫ ስም  ስርአተ አልበኝነት  እንዲከሰት እንደማትሻ  ገልጻለች  ፡፡
ባለፈው ሳምንት (ሰኞ እለት)  ለሁለተኛ   እና የመጨረሻ ዙር  ፕሬዜዳንታዊ ክርክር  ወደ መገናኛ ብዙሃናት ብቅ ያሉት  እጩ ፕሬዜዳንቶች  ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ (እሁድ እለት)  በተካሄደ  አንድ ታላቅ መንፈሳዊ  ጉባኤ  ላይ በመገኘት ከህዝቡ  ጋር የህብረት   ጸሎት  ያደረጉ  ሲሆን  ልዩነቶቻቸውን   በማጥበብ  ኬኔያን ወደ ተሻለ  እና ዲሞክራሳዊ  ስርአት  የሚለውጧት  ኬኔያዊያን  ብቻ እንደሆኑ  በጾሎት ስርአቱ ላይ ለተገኘው በ አስር ሺዎች ለሚቆጠር መራጭ  እና ጸሎተኛ  ህዝብ በጋራ  ተናግረዋል፡፡ እንዚህ  ባለፈው በምርጫ ሳቤያ ጥርስ የተናከሱት  እጩ ፕሬዜዳንታዊ ተመራጮች  ምርጫው  ቢጭበረበር  እንኳን  ተሸናፊው ወገን ቅሬታ ካለው  አግባብነት  ወዳለው  የፍትህ አካል  ከመሄድ  ውጪ  አንዳለፈው   ድህረ  ምርጫ ውዝግብ ዜጎች  ቢላዋ ፡ሜንጫ ፡ጦር ፡ እና   ጠመንጃ  እንዲያነሱ  እንደማይገፋፉ  በተለያዩ  አጋጣሚዎች  ቃል ገብተዋል፡፡ በ 2010 እኤአ  በተካሄደው  ህዝበ ውሳኔ አማካኝነት  በተገኘው  ከፍተኛ   የህዝብ ድምጽ  የጸደቀው   አዲሱ  የኬኔያ  ህገ መንግስት  ተመራጩ ፕ\ት ከ50% በላይ  የህዝብ ድምጽ ማግኘት እንዳለበት  የሚደነግግ ሲሆን  ሰሞኑን IPSOSበተባለ የህዝብ እሰተያየት ማሰባሰቢያ ተቋም አማካኝነት  የተገኘ ቅድመ ምርጫ ግምት ለኡሁሩ ኬኔያታ 44.8% ብልጫ  የሰጠ ሲሆን  ጠ\ሚ\ር ራያላ ኦዲንጋ  በ44.4% እንደሚከተሉ  ግምት ሰጥቶ ነበር፡፡ የቁጥሮቹ ተቀራራቢነት  የመርጫውን  ምን ያህል አጓጌነት እና  በብርቱ ፉክክሮች   ይታጀበ  መሆኑን የሚያመላክት  ሲሆን  ማክሰኞ እለት የተቆጠሩ የድምጽ ካርዶች  ውጤት  አንደሚገልጹት  ከሆነ  14.3 ሚሊዮን ህዝብ ለምርጫ ተመዝግቦ 70 ከመቶው ድምጹን ለማሰማት  በአገሪቱ በሚገኙ  30 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች  የሚፈልገውን መሪ ለመምረጥ በወጣበት የኬኒያው ፕሬዜዳንታዊ  ምርጫ ኡሁሩ ኬኒያታ ተቀናቃኛቸው  ጠ\ሚ\ር ራያላ ኦዲንጋን 56%  ለ 40% በሆነ የድምጽ ብልጫ እየመሯቸው እንደሆኑ ዘገባዎች ይገልጻሉ ፡፡   ይህ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ነጻ እና  ሰላማዊ ነው ባይባልም ምርጫውን ተከተሎ   የቱሪስት  መነሃሪያዋ   የወደብ  እና  ሁለተኛ ከተማ ሞምባሳ  “ኬኔያዊ አይደለንም በሚሉ ወይም እንገነጠላለን የሚል አቋም ባላቸው”  ወገኖች እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተከሰተ ግጭት 5 ፖሊሶች እና በረካታ ሴቬሎች  መገደላቸው ታውቋል፡፡ይሁንና የተፈጠረው  ድንገተኛ ግጭት መራጮች ድምጻቸውን ከመስጠት አላገዳቸውም  ተብሏል፡፡ጋሬሳ በተባለ ሰሜናዊ አካባቢም መጠነኛ ችግሮች እንደነበሩ ከ መዲናይቱ  ናይሮቢ ተላንትና (ማክሰኞ  እለት)  የወጡ  ዝገባዎች ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን  የኬኒያው የ ፕሬዜዳንታዊ ምረጡኝ  ዘመቻ  በአመዛኙ  እንደተቀረው የ አፍሪካ አህጉር የምረጡኝ  ዘመቻዎች  በጎሳ ፖለቲካ ፡በመሬት የባለቤትነት ጥያቄ  እና  ፖለቲካዊ አመለካከቶች ዙሪያ   ያተኮረ ቢሆንም   ኬኔያዊያን  ተቀዋሚዎች  ሆኑ  ገዢው መንግስት እንደ እኛ አገሩ  ምርጫ  97  “ጨዋታው   ፈረሰ ዳቦ ተቆረስ  “አይነት  አካሄድ  ሳይከተሉ  ወይም ተቃዋሚዎች  ከምርጫው በሁዋላ   የፖለቲካው  ምህዳር ጠቧል ጫናውም በዝቶብናል…ወዘተ  ብለው  እራሳቸውን ከ እነ አካቴው ከውድድር እንዳራቁበት  እና አገዛዙም በተቃዋሚዎች ላይ የተለያዩ የማግለያ ዘዴዎችን  በመጠቀም  ፈላጭ ቆራጭነቱን  አንዳረጋገጠበት  አካሄድ ሳይሆን  ኬንያዊያን   ከምርጫው ጋር  በተያያዘ  ለተፈጸመው የሰላማዊ ዜጎች  ህይወት መጥፋት እና የንብረት ውድምት  በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ  በህግ የሚጠየቁ   ወገኖች  ተጠይቀው  ገሚሱም ለተፍጸመው ስህተት በ አደባባይ ይቅርታ ጠይቀው   በረካታ ተበዳዮችም  እንደ  አንዳንድ  አገር መራጮች በደረሰባችው  ጠባሳ ምክንያት ተሸማቀው “እናቴን ያገባ ሁሉ  አባቴ  ነው”  ባለማለት   ወይም ከምርጫ ባለመሸሽ በተቃራኒው  ቁጥራቸውን አብዝተው  ወደ ድምጽ   መስጫ ጣቢያዎች   መሰባሰባቸው  ለተቀረው የአፍሪካ  አህጉር  አምባገነኖች  ሆኑ ተቃዋሚዎች    ነን የሚሉ  ጥሩ  ትምህርት የሚሰጡ የመስላሉ፡፡ ይህ ማለት  ግን ደሀር ምርጫውን ተከትሎ በደረሰው  ችግር ሳቢያ የሁሉም  ኬኔያዊ እምባው  ታብሶለታል ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ ድረስ በመቶ ሺህዎች  የሚቆጠሩ ኬኒያዊያን ከተሰደዱበት  አካባቢ  ወደ ትውልድ ሰፈራቸው  ለመመለስ ብዙ ፈተናዎች  ከፊታቸው ተደቅነውባቸው  ይገኛሉ ፡፡ አያሌ የድህረ 2007\2008 እኤአ ምርጫ ሰልባዎች  ተመሳሳይ  የብቀላ እርምጃ  እንዳይወሰድባቸው  ቀደም ብለው  ሽሽትን የመረጡ  ቢሆኑም  በምርጫው ሳቢያ ዛሬም ድርስ የስጋቱ ደመና  በተወሰነ ደረጃ ቢኖርም  ምርጫው ከተሳካ  ኬናዊያን ምርጫቸውን  የተሳካ ምርጫ ለማድርግ  የተጓዙበት  ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከጎርቤቶቻቸው አልፎ  ለምእራባዊያን ጭምር  ትምህርት ሰጪ ነቱ ቀላል አይሆንም ፡፡

No comments:

Post a Comment