Tuesday, January 7, 2014

“የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች”

“የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች”

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” አለ ያገሬ ሰው ይህንን ማሳሌያዊ አነጋገር እዚህ ቦታ ላይ ያምክንያት አላመጣሁትም። ሰሞኑን የሰማሁት ነገር ገርሞኝ ነው። የወቅቱ የዓለም መነጋገሪያ ጉዳይ ያው እንደምታውቁት የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ነው።  በሁለት የደቡብ ሱዳን ብሄረሰቦች መካከልየተጀመረው አሰቃቂ ጦርነት፣ የወቅቱ መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነበት በቂ ምክንያት አለ።

ካንድ ጎልማሳ እድሜ ያላነሰ ፍልሚያ ከሰሜኑ ሱዳን መንግስት ጋር ሲያደርጉ ቆይተው፣ ከብዙ የደም መፋሰስ ስቃይ በኋላ በተባበሩት መንግስታት፣ ባፍሪካ አንድነትና በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያላሰለሰ ጠረት ሳቢያ ነጻነታቸውን ሊገኙ ችለዋል፡፡ ከዚያ ሁሉ እገዛ በኋላ ለዚህ ድል በመብቃታቸውና፤ ድፍን የአለም ህዝብ እሰይ አሁን የዚህ ህዝብ ስቃይ አበቃ ብሎ ትንሽ እንኳን ሳያገግም፣እንደገና ወደከፋ የደም መፋሰስ መግባታቸው እጅግ የሚዘገንን ሁኔታ ነው ።

ሌላ የውጭ ጠላት ሳይመጣባቸው እርስ በርሳቸው ብቻ በመባላት እንዲህ ያለውን አሳዛኝ እልቂት ሊፈጽሙት ችለዋል። ይህን ችግርም ማቆምም እጅግ በጣም ውስብስብ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው። ለምን ቢሉ፣ ጦርነቱ የሚካሄደው ጎሳን መሰረት አድረጎ ስለሆነ፤ በሁለቱም ብሔር ወይም ጉሣዎች ዘንድ የሚጥለው ጠባሳ ትንሽ የሚባል አይደለም።


እንግዲህ ልብ በሉ የዚህ ሁሉ ነገር ጠንሳሽና ይሄ ሁሉ ነገር እንዲመጣ ያደረገው ህዝቡ
ሳይሆን ፓለቲከኞቹ መሆናቸው ነው። ለወንበር ባለ ሽሚያ ምክንያት በሁለቱ ዝሆኖች ትግል  ሳቢያ ሚጎዳው ሳሩ  ነው እንዲሉ፣ ሕዝቡ አሰቃቂ ጉዳት እየደረሰበት ነው። የመጀመሪያ ካርዳቸው ለነፃነትህ ልንታገልልህ መጣን ነው። ነገር ግን በተግባር የሚታየው ለራሳቸው ስልጣንና ቦታ ሲታገሉ ነው። በሕዝብ ስም ትንሽ ቆሎ ይዘው ወደ አሻሮ መጠጋታቸው ነው የሚያከፋው።

ታዲያ የደቡብ ሱዳኖቹ ሁናቴ የህን ቢመስልም፣ የራስዋ እያረረባት የሰው ታማስላለች የተባለችው ገልቱ ሴት ተረት ደርሶ ማየታችን ነው። እኔን የሚያሳስበኝና ሁሌም የሚያስጨንቀኝ የራሳችን የጓዳ ጉድ ነው ።


 እንደ ደቡብ ሱዳን እንድንሆን የምትመኝልን ወያኔ (ኢህሃዴግ ) ከሷ ብሶ ሁለታችሁንም ቁጭ ብዬ
ካልዳኘሁ እያለች ነው። ይሄ ታሪክ በኛ እንዲደገም ከዛሬ መቶ ምናምን አመት በፊት ምኒልክ          ጡትና እጅ ቆርጠዋልና የመታሰቢያ ሃውልት ይቁም ብላ አኖሌ ላይ ሃውልት አሠርታለች። ህዝቡ ያንን እያየ በክፋት ልቡ እንዲሞላ አፈ ቀላጤ በሆኑ ጋዜጠኛ መሳይ ካድሬዎችዋ የተካሄደው
‘ቅዱስ ጦርነት’ ምናምን እያሉ የክፋት መርዝን እንዲረጩ እያስደረገች ነው። አሁን ሱዳን ጉዳይ ውስጥ ገብታ ካልሸመገልኩ ማለቷ “ልሸምግላችሁ” ወይስ “እኔ አልተሳካልኝም ከደቡብ እናንተ እንዴት እንደተሳካላችሁ ትምህርት ልቅሰም” ማለቱዋ ይሆን?                                 

እኔን የማይገባኝ ነገር ለኦሮሞ ሲሆን የመታሰቢያ ሃውልት ለትግራይ ሲሆን ልማት ምን ማለት ነው ጎበዝ ? አማራውንና ኦሮሞውን እያባሉ እነሱ ሃገራቸውን ያለማሉ። እድሜያቸውን ያረዝማሉ። ብቻ ሁሉንም ነገር በማስተዋል ክፉ ስራዋን ከስር ከስር እያከሸፍን ተጓዝን እንጂ፣ እንዳያያዝዋማ “ኢትዮጵያ” የምትባል አገር ገና ድሮ ጠፍታ ተቀብራ ነበር። ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ዛሬ ባልኖረችም ነበር። አሁንም እያንዳንዱን የክፋት ስራዋን እያከሸፍን በፍቅር በህብረት በመተሳሰብ አብረን እንኖራለን። ወያኔ ያልፋል ‘ኢትዮጵያ’ ግን ለዘላለም በክብር ትኖራለች! ልዑል እግዚአብሄር ለአክራሪ ብሄርተኞች ማስተዋልን ይስጥልን እንለምናለን፡፡ አሜን!

                                           ምናሴ መስፍን                   

No comments:

Post a Comment