Sunday, January 5, 2014

ብሔርተኝነትና መዘዙ

ብሔርተኝነትና መዘዙ

መቼም ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ብሔር ሊወለድ የሚችለው ከአንድ ሰው ነው የዛን
ሰው የዘር ግንድ ይዘን ስንቆጥር መድረሻችን አንድ ሰው ወይም ሁለት ጥንዶች ጋር ያደርሰናል ። አዳምና ሄዋን እንዲሉ…

ለዚህ እንደምሳሌ ሊሆነን የሚችለው ሁላችንም የምናውቀው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ነው፡፡ እሱን እንመልከት እስራኤል የሃገር ስም ሣይሆን የያዕቆብ ስም ነው፡፡ እርሱ የወለዳቸው አስራ ሁለት ልጆቹ ነገድ ወይም ብሔር ለመሆን በቁ፡፡ የኛንም ታሪክ ስንመለከት ልክ እንደዛው ነው፡፡ ለምሣሌ ስለ ኦሮሞ ብናነሳ ኦሮሞ የብሔር ስም አይደለም የሰው ስም እንጂ እርሱ የወለዳቸው እነ ሜጫና ቱለማ ሲወልዱ ሲዋለዱ በዙ ተባዙ ታላቅ ህዝብም ለመሆን በቁ፡፡ ለዚህም እንዴት እንደበቁ ለማወቅ አንድ በአንድ እንመርምር ቢባል በቂ የታሪክ ምስክርና አሻራ እናገኛለን ።  መነሻዬ ማን ማንን ወለደ የሚለውን መርምሮ ለማሳየት ሳይሆን የብሄርንና የጎሳን መዘዝ መጠቆም ነውና ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስ፡፡
   

ብዙን ጊዜ የሰዎች ትልቁ አጥፊ ጠላት እኔነት ወይም ኢጎ (Ego) የሚባለው ነው ባይ ነኝ፡፡ ለምን ቢባል ስለሰው ዘር አመጣጥም ይሁን ስለ ብሔር አፈጣጠር ብንመለከት የምናገኘው ምላሽ ሰው ሲወለድ ሲዋለድ እዚህ ደርሶ እንጂ ሌላ ወይም ከሌላ ኘላኔት የመጣ የለም የሚለው መደምደሚያ ላይ ነው ።   

ሰው በተፈጥሮው የበላይ ልሁን ሲል  እኔነቱን መቆጣጠር ሳይችል ይቀርና እኔ የበላይ ወይም ከሁሉ በላይ የመሆን ስሜቱ ሲጎለብት፤ እኔ የበላይ ነኝ  ከሚለው አመለካከቱ ጋር ጥፋትንም ይዞ ይመጣል በየዘመናቱ የተነሱ ዕብዶችን ብንመለከት እንደ ምሳሌ  እስታሊንና ሂትለር ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ባገራችንም ያጼ ቴዎድሮስን የመጨረሻ ቀኖቻቸውን የእብደት ሥራዎች ሰናጤን፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለ ማርያም በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ያደረሰውን ግፍ ስንመለከት የትምክህትና ከኔ በላይ የማንአለብኝ ስሜቶች ውጤት መጨረሻዎች እንደሆኑ እናጤናለን፡፡

ባገራችን ምስኪን ሕዝብ ላይ በመርዝ ጋዝ ያን ሁሉ ጭካኔና ግፍ የፈጸመው፣ ሞሶሎኒና ተከታዮቹ መነሻቸው እኔነታቸው የፈጠረባቸው እራስን ከሁሉ አስበልጦ የመመልከት ባህሪ ወይም አባዜ ነው ።

ብሔርተኝነት ማለት የአሁኑ ያላደጉ ሃገራት ‘ ቫይረስ’  ነው፡፡  አለም ወደ አንድ መንደር እየተሰባሰበች ባለችበት ወቅት፣ የብሔር አቀንቃኞች ጫፍ እና ጫፍ ሆነው ህዝብን መከፋፈል የነሱ ባህሪያት መገለጫ ነው፡፡ እነዚህ የብሔር አቀንቃኞች ሁልጊዜ እራሳቸውን ማንም ሳይመርጣቸው ማንም ሳይወክላቸው ላንተ የቆምን ነን፣ ላንተ ከኛ በላይ የሚቆረቆር የለም እኛን ስማን ተገፍተሃል ተበድለሃል ተጨቁነሃል የሚሉ አማላይ ቃላትን ጠዋት እና ማታ እየዘሩ የዋሆችን ያነሆልሉበታል፡፡ መወገድ ያለበት የጋራን ጠላት ትተው፣ ከመቶ አመት በፊት የተሰራ ወይ ያልተሰራ ይሁን ወይ አይሁን ለነሱ ግድ የማይሰጣቸውን ብቻ የሆነ ታሪክ እያራገቡ ዘረኝነትን ያስፋፋሉ ።

ብሔርተኞች ብዙውን ጊዜ የሌላውን ሃሣብ መስሚያ ጆሮ የላቸውም፡፡ ሁልጊዜ እነርሱ ትክክል እንደሆኑ ነው የሚያወሩት፡፡ እሩቅ ሳንሄድ ባሁኑ ጊዜ እዚህ ጉረቤታችን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ምን እየደረሰ እንዳለ በየሚዲያው የምንሰማው ነገር ነው፡፡  ህብረት እንጂ ብሔርተኝነት ለየትኛውም ሃገር ሲበጅ አላየነም አልሰማንም ።

ለምሣሌ ብንወስድ፣ በአለም ላይ በቋንቋ በእምነት በብዙ ነገር የሚመሳሰሉ ህዝቦች ያሉዋት ብቸኛ ሃገር ሱማልያ ናት፡፡  ብሔርተኝነት መጥፎ ነው ነገሩ ሲጀመር እውነት የሚመስሉ ነገሮች አሉት፡፡ ግን እውነት የለውም፡፡ ሶማሊያ ለዚህ በቂ ማሣያ ምሳሌ ናት፡፡ በመጨረሻ እኔ ላስተላልፍ የምፈልገው ነገር በተለያየ ዋልታ ሆናችሁ እንደ ክር የወጠራችሁትን የዘር ፓለቲካ አርግቡትና፤ በህብረት በፍቅር ለመኖር የየራሳችሁን አስተዋፅኦ አድርጉ የሚል ነው፡፡ ቢያንስ አለም ጥሎን እየሄደ ነው፡፡ በዘር እንከፋፈል የምትሉ ሁሉ ተሳክቶላችሁ ያች ሃገር በዘር ብትከፋፈል የሚቀጥለው ሥራችሁ  ደሞ በጎሳ እንከፋፈል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ህብረት ማለት ሀይል ነው! ህብረታችን ብዙ ነገራችን ነው!  በተለያየ ጎራ ሆናችሁ የወይኔን እድሜ አታርዝሙብን!!!!! አጭር ለሆነች እድሜ እረጅም የቤት ስራ አትስጡን!!!! የታሪክ ተወቃሽ አታርጉን!!!! ለልጆቻችን የምናስረዳው የምንነግረው ነገር አትንፈጉን!!! ሁሉ ነገር በኛ እንዲበቃ የሁላችን ስራ ይሁን!!!! አሜን!        
                         ከምናሴ መስፍን

                     alazmina@yahoo.com

No comments:

Post a Comment