Thursday, November 8, 2012

የሃሪኬን ዐውሎ ነፋሳት መነሻቸው ከኢትዮጵያ መሆኑን የናሳ ሳይንቲስት አረጋግጠዋል

በፍቅር ለይኩን

HARRICANE SANDY GOES FULL
 
የአሜሪካን በተለያዩ ጊዜያት የመቱ አውሎ ንፋሳትና ወጀቦች መነሻቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራማ ቦታዎች መሆናቸውን የናሳ ሳይንቲስቶች ጥናቶች በተለያዩ ጊዜያት ሲያመለክቱ ነበር፡፡ ኦውን ኬሊ የተባሉ የናሳ ተመራማሪ በ2006 ዓ.ም ጥናታቸው፡- A lot of hurricanes start out over the Ethiopian Mountains. Air steadily flowing over those mountains and they cause waves in the air. በማለት የሄሪኬን አውሎዎችና ወጀቦች መነሻ ኢትዮጵያ መሆኗን በጥናታቸው አመልክተዋል፡
 
ሌላኛው የናሳ ሳይንቲስትና ተመራማሪ የሆኑት ስኮት ብራውን እ
ስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሄሪኬን መነሻዎች ከባሕሮችና ከውቅያኖሶች ዳርቻዎች ነው ከሚለው በተጨማሪ ለሄሪኬን መከሰት ከምዕራብና ምስራቅ አፍሪካ የሚነሱ ንፋሳትና አውሎዎችም የብዙዎች ሳይንቲስቶችና አጥኚዎች ትኩረትን እየሳቡ መምጣታቸውን በጥናታቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
 
Wall Street Journal የናሳ ሳይንቲስቶችን ጥናት ዋቢ በማድረግ እንዳስነበበው ደግሞ አሜሪካንን የመታው ‹‹ሄሪኬን አርል›› የተባለው አውሎና ወጀብ መነሻው ከኢትዮጵያ እንደነበር በወቅቱ አስነብቦ ነበር፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም የተከሰተው ‹‹ሄሪኬን ኢሳቤላ›› የሚል መጠሪያን ያገኘችው አውሎና ወጀብም መነሻዋ ከኢትዮጵያ እንደነበር ተገልጾ ነበር፡፡
 
2008, ABC News, “The Real Home of Hurricanes: Ethiopia?” በሚል የሀሪኬን አውሎና ወጀብ ከኢትዮጵያ ከየትኛው ቦታ እንደሚነሳ በአኒሜሽን በተደገፈ ምስል ጭምር ዘግቦ ነበር፡፡ የዘንድሮው አሜሪካን ምስራቃዊ ግዛት በመምታት ወደ ሰሜናዊ አሜሪካ ግዛትና ካናዳ እየገሰገሰ ያለው ሄሪኬን ሳንዲ መነሻው በትክክል ከየት እንደሆነ ባይገለጽም ከምስራቃዊ አፍሪካ ግዛት ሊሆን እንደሚችል ግን ያለፉትን የሄሪኬን መነሻዎች ጥናቶች ዋቢ በማድረግ አንዳንድ ሳይንቲስቶች እየተናገሩ ነው፡፡
ስለ ሄሪኬን ሳይንሳዊ ጥናቱና መረጃው እንዳለ ሆኖ ነፋሳትን፣ አውሎዎችንና ወጀቦችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት አስራ ሁለት የንፋስ መስኮቶች እንዳሉና ከእነዚህ የነፋሳት መስኮቶች መካከል አራቱ ብቻ የምሕረት ሲሆኑ የተቀሩት ስምንቱ የመዓት ወይም የቁጣ የነፋሳት መስኮቶች/መዛግብቶች መሆናቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንቶች ይናገራሉ፡፡
 
የክርስትና ሃይማኖት መመሪያ የሆነው ቅዱስ መጽሐፍም በዮሐንስ ራእይ፡- ‹‹በምድር ላይ ምንም ዓይነት ንፋስ በባሕርም ሆነ በምድር ላይ እንዳይነፍስ መላእክት አራቱን የምድር ንፋሳት ያዙ፡፡›› (ራእይ ፯፣፩) በማለት አራት የነፋሳት መስኮቶች እንዳሉ ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ፍንጭ መስጠቱን የራእይ መጽሐፍ ይናገራል፡፡
 
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ከሆነ በምስራቅ ወይም በአዜብ በኩል የሚነሱ ንፋሳትና አውሎዎች የመዓትና የቁጣ መገለጫዎች እንደሆኑ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ እውነት መሠረትም በተደጋጋሚ አሜሪካን ግዛቶችና በዙሪያዋ ያሉትን ሀገራት የመቱ አውሎዎችና ነፋሳት መነሻቸው ከምስራቅ/ከአዜብ ነው የሚለው ጥናት ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ይመስላል፡፡
 
ስለ ምስራቅ ነፋሳት ጽኑነትና አደገኛነት ለአብነትም ያህል ከክርስቶስ ልደት በፊት መላውን ዓለም የመታውን ጽኑ ራብ አስቀድሞ በራእይ የተገለጸለት ዮሴፍ ስለ ድርቁና ክፉ ስለሆነው የራቡ ዘመን በግብፅ ሳለ የተመለከተውን ራእዩን ሲገልጽ፡- ‹‹በምስራቅ ንፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፡፡›› በማለት በምድር ላይ ለሰባት ዓመት ጸንቶ የቆየውን ራብ አስቀድሞ እንደተነበየ ሙሴ በዘፍጥረት መጽሐፍ ገልጾታል፡፡
 
የክርስትና ሃይማኖት መሠረት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋእለ ስብከቱ ለአይሁዳውያን ‹‹… በምስራቅ ንፋስ ሲሆን ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፣ ይሆንማል…፡፡›› (ሉቃ ፲፪፣፶፭) በማለት በምስራቅ የሚመጣው ንፋስ ለምድሪቱ ክፉ አደጋ ይዞ የሚመጣ መሆኑን ሰማያትን በማንበብ ትተነብያላችሁ፣ ግና የዘመኑን ምልክት በቅጡ ለማንበብ አለመቻላቸውን/መስነፋቸውን በመገሰጽ በቁጣ እንደተናገራቸው ወንጌላዊው ሉቃስ ጽፎልናል፡፡
 
አይሁዳዊው ሊቀ ነቢያት ሙሴም ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ያወጣባቸውን ተዓምራቶችና የኤርትራ ባሕርን ያሕዌ እንዴት እንደከፈለው በዘጸአት መጽሐፍ ሲገልጽ፡- ‹‹ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምስራቅ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፣ ባሕሩንም አደረቀው፣ ውኃውም ተከፈለ፡፡›› በማለት ስለ ምስራቅ ነፋሳት ኃያልነትና እግዚአብሔር በድንቅ ተዓምራት ሕዝቡን እንዳሻገራቸው በማስታወስና እንዲሁም ጠላቶቻቸው የሆኑትን ግብፃውያንንም እንዴት በእግዚአብሔር መዓት ቁጣ በባሕር እንደተከደኑ ሲገልጽ ደግሞ፡- ‹‹ነፋስ አነፈስህ ባሕርም ከደናቸው፣ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረረ ሰጠሙ፡፡ ይለናል፡፡ (ዘጸ ፲፭፣፲፤ ፲፬፣፳፩)
 
ንፋሳት የእግዚአብሔር የቁጣ መዓት መገለጫዎች እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ፡፡ ‹‹ወጥመድን በኃጥአን ላይ ያዘንባል፣ እሳትና ዲን አውሎ ንፋስም የጽዋቸው ዕድል ፋንታ ነው፡፡ በሌላ ስፍራም፡- ‹‹እሳትና በረዶ አመዳይም ውርጭ ቃሉን የሚያደርግ አውሎ ንፋስ፤ ተናገረ አውሎ ንፋስም ተነሣ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ…፡፡›› በማለት መዝሙረኛው ዳዊት እነዚህ የተፈጥሮ ኃይላት የእግዚአብሔር ቃል/ትዕዛዝ ተገዢዎች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ (መዝ ፶፣፫፣ ፸፯፣፲፰፣ ፻፯፣፳፭፣ ፻፵፰፣፰)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም፡- ‹‹እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል የክንዱም መውረድ በሚነድድ ቁጣ ነውና በምትበላ እሳት ነበልባል በአውሎ ነፋስም፣ በወጨፎ፣ በበረዶ ጠጠርም ይገለጻል፡፡›› ይለናል፡፡ (ኢሳ፴፣፴) ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር አውሎ ንፋስ እርሱም ቁጣው የሚያገለባብጥ አውሎ ንፋስ ወጥቶአል የዓመፀኞችን ራስ ይገለብጣል፡፡›› (ኤር ፳፫፣፲፱)
ንፋሳት ከመዓት ውጭም የእግዚአብሔር ክብር፣ ኃይል፣ ክንድና ጽናት መገለጫዎች እንደሆኑ መዝሙረኛው ዳዊት ሲናገር ‹‹እግዚአብሔር በኪሩብ ላይ ተቀምጦ በረረ፣ በነፋስ ክንፍም ሆነ እግዚአብሔር ታየ››፣ ‹‹የነጎድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበር፣ መብረቆችህ ለዓለም አበሩ፣ ምድር ተናወጠች፣ ተንቀጠቀጠችም፡፡››ይለናል፡፡ (፪ሳሙ ፳፪፣፲፩፤ መዝ ፸፮፣፲፰)፡፡
በዘንድሮ ምስራቃዊው የአሜሪካን ግዛት በመምታት ወደ ሰሜንና ወደ ካናዳ እየገሰገሰ ያለውን ‹‹ሀሪኬን ሳንዲ›› የሚል ስያሜ ያገኘቸውን አውሎና ወጀብ ያስከተለችውን ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በሰዓት ከ80 ማይልስ በላይ የሚጓዘው ይኸው አውሎ ንፋስ ኃይለኛ ወጀብና ዝናብ ጭምር የቀላቀለ መሆኑንና እስካአሁን ድረስ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን እንዲሁም በዚሁ አደጋ ከ700 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን አጥቶ በጨለማ ውስጥ መዋጣቸው እየተነገረ ነው፡፡
 
በዚሁ “super storm” በአሜሪካ ታሪክ አቻ ያልተገኘለት፣ እጅግ አስከፊና ታይቶ የማይታወቅ በተበላው በሀሪኬን ሳንዲ አውሎና ወጀብ የተነሳ ስልክ፣ መብራትና የትራንስፖርት አገልግሎት በከተማዋ መቋረጡ የመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡
በተለምዶ The October Surprisings/የጥቅምት ወር አስገራሚ ክስተቶች/ድንገቴዎች በሚል እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካውያን ጋዜጠኞች ዘንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅትን ተከትሎ የሚከሰቱትን አስገራሚና አስደንጋጭ ተፈጥሮአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ክስተቶችን ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ያልተጠበቁ ክስተቶችን ይዘግባል፡፡ ከሁለት ወር በፊት በሀሬኬን አውሎ ንፋስ አደጋ ቅድም ትንበያ የተነሣ የባራክ ኦባማ ተቀናቃኝ የሆኑት ሩሚኒ በፍሎሪዳ ሊያደርት የነበረውን ኮንቬንሽን በመሰረዛቸው በምርጫ ዘመቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አድርሶባቸው እንደነበር ተገልጾአል፡፡
ከዚሁ ከሃሪኬን ሳንዲ አውሎ ንፋስ ጋር በተያያዘ በዘንድሮ የአሜሪካ ምርጫ የሀሪኬን ሳንዲ አውሎ ንፋስ ያስከተለው ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ the October Surprising/ አስገራሚ የጥቅምት ክስተት/ድንገቴ በሚል ሊጠቀስ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
 
በዚሁ ተፈጥሮአዊ አደጋ የተነሳ ባራክ ኦባማም ሆኑ ተቀናቃኛቸው ሩሚኒ የምርጫ ዘመቻቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል፡፡ ይህ አደጋ በተለይ ለባራክ ኦባማ የምረጡኝ ዘመቻ ፈታኝ የሆነ ክስተት ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡ የፕሬዝዳንቱ የምረጡኝ ዘመቻ አማካሪ የሆኑት ዴቪድ አክስሎርድ ለሲ ኤን ኤን እንደተናገሩት የሀሬኬን ሳንዲ በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ አሁን ለመናገር አይቻልም፡፡ አሁን በእጅጉ አሳሳቢው የሆነው የሕዝባችን የመታደግና የማቋቋም ጉዳይ ነው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በማለት ነበር የገለጹት፡፡
የአሜሪካን ምስራቃዊ ግዛት ያደባየው ሃሪኬን ሳንዲ እንደ በፊቶቹ ሄሪኬኖች መነሻቸው ምስራቃዊ የአፍሪካ ግዛት ይሆንን…ወይስ…!? ለማንኛውም በዚህ ተፈጥሮአዊ ክስተት ክፉኛ ለተመታችው አሜሪካ መልካሙ ነገር ሁሉ እንዲገጥማት እንዲሁም በዚህ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን፣ ሀብትና ንብረታቸውን ላጡ ሁሉ መጽናናትን በመመኘት ልሰናበት፡፡
ሰላም! ሻሎም!
-

-

No comments:

Post a Comment