በሥራ ላይ አለ የሚባለው በ1987 ዓ.ም. የወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30ና 31 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብት ይደነግጋሉ፤ ነገር ግን ሁለቱም አንቀጾች ግን እያሉ መፍረሻውን ወይም ማርከሻውን አብረው ይገልጻሉ፤ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ነው፡ይህ ዘዴ በአጼ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የሚታይ ነበር፡፡
የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቶች የሕዝቡን ስሜትና ፈቃድ ለማወቅ ለሚፈልግ መንግሥት የእነዚህ መብቶች በተግባር መዋል በጣም ፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም መንግሥትንና ሕዝብን ያቀራርባሉ፤ የእነዚህ መብቶች መታፈን የሚያሳየው በመንግሥት ፋንታ አገዛዝ መኖሩንና ሕዝቡን ያለፈቃዱ በኃይል ብቻ የሚገዛ መሆኑን ነው፡፡
አንቀጽ 30‹‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፤›› ከአለ በኋላ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፤›› በማለት የአንቀጹን ዋና ርእስ ያደበዝዘዋል፤ ያውም ምንም ትርጉም በሌለው ማመካኛ ነው፤ እግዚአብሔር ያሳያችሁ መሠረታዊ የሆነ የዴሞክራሲ ማሙያዎች የሆኑትን የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍን የማድረግ መብት ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ›› በሚል በተምታታና ግልጽ ባልሆነ አስተሳሰብ ዋናውን መብት ለመገደብ ‹‹ሕጋዊ›› የሚመስል ማመካኛ ፈጠሩ፤ በዚህም ምክንያት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሚመስሉት አንቀጾች በተግባር ታግተዋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመሰብሰብም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መትረየስንና ክላሽን የሚጋርድና የሚከላከል ጥላ ያስፈልጋል፤ አነዚህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ከሥራ ውጭ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበርና የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ወደአለመኖር ተሸጋግረዋል፡፡
አሁን ደግሞ በፖሊቲካ ፓርቲዎች ላይ ጭቆናውና አፈናው እየበረታ በመሄዱ ፖሊቲካ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ስብሰባ የሚያደርጉበት አዳራሽ (የግልም ሆነ የመንግሥት) ማግኘት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ በሰላማዊ ሰልፍም አገዛዙ መሳቂያና መሳለቂያ ሆኖአል፤ ለግራዚያኒ በኢጣልያ የሚሠራውን ሐውልት ለመቃወም ጥቂት ዜጎች በስድስት ኪሎ ቢሰበሰቡ ፖሊሶችና የደኅንነት ነጭ ለባሾች እየደበደቡ ይዘው፣ አንድ ቀን አስረው በበነጋታው በዋስ ለቀዋቸዋል፤ በፋሺስት ኢጣልያ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ካልተፈቀደ ለምን ይፈቀዳል?በዚህ ሁሉ ላይ ጋዜጠኞችን ሽብርተኞች እያሉ ወደወህኒ ቤት በመወርወር ጋዜጠኞች ሁሉ አንድም ወደስደት አንድም ወደወህኒ እየገቡ ነጻ ጋዜጣ እየጠፋ ነው፤ ስለዚህም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለገብ አፈና ሰፍኖአል ለማለት ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝቡ ቤቱ ሲፈርስ፣ መሬቱን ሲነጠቅ፣ ከኑሮው እየተፈናቀለ ሲባረር፣ ፍትሕ ሲጠፋ፣ ክብሩንና ኩራተን ተገፎ በያገሩ ሲሰደድና ውርደት ሲደርስበት ተሰብስቦ ለመወያየት መብት የለውም፤ በተናጠል እንባውን እያፈሰሰ ወደአምላኩ ማመልከት ልማድ ሆኖአል፤ በአገዛዙ ወንበር ላይ የተቀመጡት እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ሕዝብ ግፍ የማያይ፣ ጩኸቱንም የማይሰማ ይመስላቸዋል፤ አግዚአብሔር ግን ሁሉንም ይመዘግባል፤ ለንስሐ የሰጣቸው ጊዜ ሲያበቃ ፍርዱን ለእያንዳንዱ ይሰጣል፤ ያን ጊዜ ኃይልም፣ ሀብትም፣ ሥልጣንም የሕዝብ ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment