Friday, May 3, 2013

የዘመኑ ትውልድ ሥነ-ምግባር ወዴት?





አንድ ትውልድ ትውልዳዊ ፍሰቱን ጠብቆ ዘመናትን በስኬት መጓዝ ይችል ዘንድ ከቁሳዊ ሥልጣኔ  ባሻገር በመንፈስ የሰለጠነ፤ በሥነግባር የታነፀና ባለራዕይ ሊሆን ይገባል። ከዚህ አኳያ በወያኔ ዘመን በሥነምግባር የታነፀ፤ ባለተስፋና በትክክል ማለም የሚችል ስነ አዕምሮና  ጠንካራ ስነልቦና ያለው ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ምን ላይ ነው ያለነው? የትውልዱ ሥነ-ምግባር በምን ልክ እየተቀረፀ ነው? ትውልዱ በጥሩ ሥነ-ምግባር ይታነጽ ዘንድ ከፍተኛው ድርሻ የሚጠበቅባቸው ተቋማት ድርሻቸውን እየተወጡ ነውን? ካልሆነ ምን ዓይነት ነገ ይጠብቀናል? መፍትሔውስ ምንድነው?
በእኔ እምነት የአንድ ትውልድ ሥነምግባር በቅጡ ይታነጽ ዘንድ የሚከተሉት ተቋማት ኃላፊነት አለባቸው። ይህን ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አኳያ ምን ሳንካ እየገጠማቸው ነው የሚለውን አያይዤ ለመጥቀስ እሞክራለሁ።
1.     ቤተሰብ
ቤተሰብ የአንድን ማኅብረሰብ እጣ ፈንታ ለመወሰን የሚችል የሚታይና የሚዳሰስ ተቋም ነው።ጥሩ ቤተሰብ የጥሩ ማኅበረሰብ መሠረትነው። ጥሩ ማኅበረሰብ የጥሩ ሃገር መሠረትነው። ስለዚህ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖር ግብረገባዊ መስተጋብር፡ እናት ወይም አባት (የቤሰብ ሃላፊዎች)  ልጆቻቸውን በሥነ ምግባር ለመቅረጽ የሚኖራቸው ኃላፊነት እና አደራ እጅግ ከባድ ነው። ልጆች ትምህራቸውን በደንብ እንዲከታተሉ፤ ሰው ማክበርና ሰው  መውደድን፣ ሰብዓዊነትን፣ ቅንነትን፣ “ይቻላል” ባይነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ የሌሎችን ሃሳብ ማዳመጥንና ከሌሎች መማርን፣ መረዳዳትን፣ መተጋገዝን፣ የሃገር ፍቅርን … ወዘተ ባህሪያቸውና የሕልውናቸው አካል እንዲያደርጉ፤ በአንፃሩ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ግትርነትን፣ ቂመኛነትን፣ መጠላለፍን፣ ሰው መናቅን፣ እና የመሳለሉ የመንፈስ እድፎችን እንዲጠሉና እንዲያስወግዱ በማድረግ ልጆቻቸውን የእውነት “ሰው” አድርጎ  የመቅረጽ ኃላፊነት አለባቸው። የሕፃንነት ዘመናቸው የነገ ማንነታቸው ፈጣሪና መሠረት ነውና።

ከዚህ አኳያ በወያኔ ጊዜስ? ቤተሰብ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ  ነውን?  መልሱ : “አይደለም”  ነው። በዚህ ወቅት ለልጆች የመልካም ስብዕና ባለቤት መሆን መጨነቅ በሌላ አንገብጋቢ ጭንቀት ተተክቷል። በልቶ በማደር!!! ልጆቼ ምን በልተው፣ ምን ለብሰው፣ ምን ጠጥተው ትምህርት ቤት ይሂዱ? ከቤት ወጥተው ይዋሉ እንጂ ምን  ሥነምግባር ተላበሱ የቅንጦት ጥያቄ  ሆኗል። ሆዱ ያልሞላ ቤተሰብ ስለልጅ አስተዳደግ እንደምን ሊጨነቀው ይችላል? ይህ ከሆነ “የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት” ዓይነት ቅሌት ይመስላል። የሚላስ የሚቀመስ እየጠፋ ሕፃናት በየትምህርት ቤቱ በምግብ እጥረት ምክንያት ክፍል ውስጥ በሚወድቁበት አገር ቤተሰብ ቤቱ ከእጅ ወደአፍ በሆነ ኑሮ  ሕይወቱን ማሳደር የሚችልበትን መላ  ከማሰላሰል ባለፈ የልጆች ሥነምግባርና ሃገር ተረካቢነት ጉዳይ ከቶ  እንዴት ሊታሰብ ይችላል? በፍጹም አይቻልም!!ቤተሰብ በችግር፣ በነፃነትና ተስፋ ማጣት ተወጥሯል። ስለሆነም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ውስጥ ያለ  ልጅ አናጭ እና ቀራጭ አሮበት ሲባዝን ይውላል።
2.   የሃይማኖት ተቋማት
በእኔ እምነት ሁሉም ሃይማኖቶች መልካምና በመንፈስ የበለፀገ ትውልድን ለማፍራት የሚያስችል አስተምሮት አላቸው ። ምክንያቱን ሁሉም ሃይማኖቶች ልዕለ ኃያል የሆነ  ተፈጥሮ  ያላቸው ቸር፣ ሩህሩህ፣ አዛኝ፣ ቀና፣ ሁሉንም እኩል የሚያይ፣ ተንኮልንና ክፋትን የሚጠላ፣ጠጭነትን፣ ሴሰኝነትን፣ ቦዘኔነትን የማይወዱ ወዘተ ፈጣሪ ወይም ጌታ ወይም አምላክ ወይም መሲህ አላቸውና ። አስተምሮታቸውም በእነዚህ የመንፈስ ማጽጃ ጉዳዮችና ሌሎች ቀኖናዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በየሃይማኖቱ ጌቶች ወይም አምላኮች ወይም መላዕክት ወይም መሲሆች መልካም ባህሪዎች ተከታዩን ለመቅረጽ ይሞክራሉ።
በወያኔ ጊዜስ? … ከ1983 ዓም ወዲህ የሃይማኖት ተቋማት በየሃይማኖቱ ካህናትና መሪዎች ልብስ ባጌጡና  በደመቁ፣ ቆብ በደፉ፣ መቁጠሪያ ባንጠለጠሉና ሻሽ በጠመጠሙ ካድሬዎች ተጥለቀለቁ።  እንደ ፓለቲካው መዋቅሩና ሲቪል ቢሮክራሲው ሁሉ ተቋማቱ የዘመዳሞች መፈንጫ የጎጠኞች መራገጫ ሆኑ። የሃይማኖቱን ተከታይ መስበኪያ መድረኮች ከወያኔ የፕሮፖጋንዳ መለፈፊያ አደባባዮች፣ ቢሮዎችና ሚዲያዎች አልለይ አሉ። ቤተክርስቲያንና ቤተመንግሥትን ለመለየት ከቤቶች አናት ላይ የተሰቀለ መስቀልን መፈለግ የግድ ሆነ። ቤተመስጊድንና የፕሮፖጋንዳ  ጽ/ቤቶችን ለመለየት ጨረቃንና ኮከብን ማማተር ወቅቱ የግድ አለ። ባጠቃላይ ድሎትንና ምቾትን በሚያሳድዱ የሃይማኖት መሪ ተብየዎች ተቋማቱ ተወረሩ። በመሆኑም ሌሎች ሁኔታዎች ከፈጠሩት ተስፋ  መቁረጥ ጋር ተዳምሮ ትውልዱ ከሃይማኖት ተቋማት ሸሸ። የሃይማኖት ቤቶችን ጠላ። የሃይማኖት አባቶች  ራቀ። ስለሆነም ከሥነምግባር ትምህርቶች ራቀ።
3.   ትምህርት ቤቶች
ትምህርት ቤቶች የአንድ አገር ሕልውና  ከሚወስኑ ጉዳዮች ዋነኛ የሆነውን ትምህርትና የተማረ ትውልድ መፍጠሪያ ተቋማት ናቸው። ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ከጠበቁ መምህራንና የመማር ማስተማር ሁኔታ  ጋር ሲደመሩ ትውልዱን በእውቀት ለማነጽ ዋናዎቹ ቦታዎች ናቸው። ነፃ ትምህርት ቤቶች፣ ነፃ የመማር ማስተማር ሂደት፣ነፃ መምህራን ከትክክለኛ የትምህርት ካሪኩለም ጋር ሲገናኑ በትክክልም ሰው መፍጠር ይቻላል።
በወያኔ ጊዜስ? …  ግራ የገባው የትምህርት ካሪኩለም ትውልዱን  ግራ  እያጋባው ይገኛል። ትምህርት ቤቶች ልክ እንደ ሃይማኖት ተቋማት ሁሉ በወያኔ ካድሬዎች ተሞሉ፤ በወያኔ  ካድሬዎች ተመሩ። ተማሪ ለወያኔ ስብሰባ ክፍል አቋርጦ  የሚወጣበት ጊዜ መጣ። መምህራን በዘራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በፓለቲካ አቋማቸውና በአጠቃላይ በማንነታቸእው የተነሳ  ተዋከቡ። የትምህርት ቤቶች ንጹህ አየር ተበከለ። ትምህርት  ቤቶች የእውቀት መቅሰሚያ ሳይሆኑ የጊዜ ማሳለፊያ ወይም መሸማቀቂያ ተቋማ  ሆኑ። የአንደኛ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስቲዎች የካድሬዎች የፓለቲካ ት/ቤት መሰሉ ። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መካከል ያለው ልዩነት በከተማው ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች መገኘታቸው ብቻ ሆነ። በመሆኑም ፕሮፌሰር ጌታቸውሃይሌ እንዳሉት ‘’አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ማን እንደሆኑ የማያውቅ የኮሌጅ ተማሪ ያውም የደብረብርሃን ልጅ’’ ተፈጠረ:: ዩኒቨርስቲዎች የብሔር ግጭቶች ማሳያ ትያትር ቤቶች ሆኑ። የአካዳሚ ነፃነት ጠፍቶ፤ መምህራን የሚያውቁትን ማሳወቅ ቀርቶ የሚቀጥለውን ወር ደመወዛቸውን ስለመውሰዳቸው እርግጠኛ መሆን ተስኗቸው “መምህሩን ያጣ ሃገር ጭንቅላቱን ያጣ ሃገር” እንዳለው” ሎሬቱ ትውልዱ ያለ ጭንቅላት እየቀረ ነው።
4.   ማኅበረሰቡ
በማኅበረሰቡ ውስጥ በረዥም የጊዜ ሂደት የሚፈጠሩ የጋራ እሴቶች፣ ባህሎች እና ማንነቶች ትውልድን ለማነጽ እጅግ ወሳኝ ናቸው። እነዚህ የትክክለኛነትና ስህተትነት ህጎች ከሌሎች ከተፃፉ መደበኛ ህጎች በበለጠ  ኃያል ሲሆኑ የትውልዱን ማንነት በመቅረጹ በኩልም ያላቸው ኃይል ከፍተኛ ነው።
በወያኔ ጊዜስ?… ለወገን የመቆርቆር አልፎም ለሃገር የመሞት የሕዝቡ እሴቶች በፍርሃት በጥርጣሬና በጎመን በጤና አስተሳሰብ ተተኩ።  መለያችን የነበረው ማኅበረሰባዊ ብልህነት ወደ ብልጠት ተቀየረ። ግለሰበኝነት፣ ሃሜት፣ ወሬ፣ ኢምክንያታዊነት አልፎ አልፎም ጥላቻ መልካም እሴቶቻችን እያጠፉ ይገኛሉ። ማኅበረሰቡ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ታስሮ  እናት ልጇን ማመን የማትችልበት ዘመን መጣ፤ ጎረቤት ጎረቤቱን ማመን ተሳነው፤ እድሮች፣ እቁቦች፣ ሰንበቴዎችና ሌሎች ማኅበረሰባዊ መሰባሰቢያዎች የወያኔን የስለላ ተቋማት ያህል ማስፈራት ጀመሩ። ፍርሃትና ጥርጣሬ፤ ጥሎ ማለፍና ብልጠት የኑሮ  ዘዴዎች ሆኑ።”ሃገር ማለት የእለት እንጀራ ሃይማኖት ማለት ለመሶብ መስገድ  ሆነ”::
5.   ሲቪክ ተቋማት
እነዚህ ሙያን፣ እድሜን ጾታን፣ ፍላጎትን ወይም ሌላ መስፈርትን መሠረት አድርጎ  በተለይ በወጣቱ ትውልድ የሚመሠረቱ ተቋማት ወጣቱን እርስ በእርስ በማቀራረብ የጋራ ፍላጎቱን በጋር እንዲያንፀባርቅ በማድረግ፣ በጋራ ለጋራ ዓላማ መታገልን በማለማመድ፣ የዲሞክራሲ እሴቶችን የመለማመጃና የማስረጫ እድል በመክፈት፣ አባላት እርስ በርሳቸው አባላት የተቋማትን አመራር በአጠቃላይም ድርጅቱን የማመን ባህልን በማዳበር የሚጫወቱት ሚና ጉልህ ነው።
በወያኔ ጊዜስ? … ሲጀመር እንዲህ ዓይነት ትውልዳዊ ፋይዳ ያላቸውና ትውልዱን የዘመን ተሻጋሪ የራዕይ ባለቤት የሚያደርጉ፣ የሚያቀራርቡ፣ የሚያዋድዱ፣ማኅበረሰባዊ መተማመንን የሚፈጥሩ ተቋማት እንዲኖሩ አይፈለግም። ከ1983 ዓም በፊት የተመሠረቱ ቢሆንም እንኳን ከወያኔ የዘር ፓለቲካ እና የወኔ ቢስ ትውልድ ፈጣራ መርሃ ግብር ጋር እንዲጣጣሙ ሆነው ተስተካክለዋል። አዲስ የተፈጠሩትም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ታስረው ተጥለዋል። ከቀበሌ  እስከ ሃገር አቀፍ ደረጃ  ድረስ በሥርዓቱ አባሎች እንዲመሩ ሁነው ሲቪካዊ ዓላማቸውን በመጣል የሥርዓቱ ጉዳይ አስፈፃሚዎች  ሆነዋል። ስለሆነም ከዚህ አካባቢ ይገኝ ይገባው የነበር  ትሩፋት ውሃ በልቶታል።
6.  የኢኮኖሚ ሥርዓት
በአንድ አገር ውስጥ የተዘረጋ የኢኮኖሚ ሥርዓት በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ካለው ቀጥተኛ ተጽዕኖ  ባሻገር በወቅቱ ትውልድ ሥነምግባር ላይም ራሱ ሥርዓቱ ከፍተኛ  ተጽዕኖ ይፈጥራል።  በተለይ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ በነፃ  ገበያ የሚመራ ከሆነ በገበያው ውስጥ የሚኖረው ውድድር ሁሌም ፍትሃዊ ውድድርን፣ ለደንበኛ አያያዝ መጨነቅን፣ ለአገልግሎት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት መስጠትን … ወዘተ  መልካም የገበያ ባህሪያትን በትልቁ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በነፃ ገበያ ውስጥ ግብይትና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ሥርዓት ያለው፣ የውድድር ሥነምግባርን የተላበሰና የተረጋጋ ይሆናል። ይህ በአቋራጭና በብልጠት ሳይሆን በፍትሃዊ ውድድር ማሸነፍን ለትውልዱ ያስተምራል። በአንፃሩ ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ውስጥ ወድቆ  የውስን ሞኖፖሊዎች መፈንጫ  ከሆነ  አጠቃላይ እንቅስቃሴ  ሁሉ ኢፍትሃዊ፣ ለደንበኛና ለጥራት እንዲሁም ለአገልግሎት የማይጨነቅ ይሆናል። ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ይሆንና ደንበኞች ጥራት በሌለው ምርትና አገልግሎት ይስተናገዳሉ። ሥርዓቱም የተረጋጋ ግብረገብ ያለው አይሆንም።
በወያኔ ጊዜስ? …  የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ተቀላቅሎ  የፓለቲካ ድርጅቶች ከንግድ ድርጅቶች መለየት ያስቸገረበት ጊዜ ነው። ተዋናይ ግለሰቦችም እንዲሁ ፓለቲከኛም፣ ባለሥልጣንም፣ ነጋዴም፣ ኮንትሮባንዲስትም፣ ጉቦኛም በሆኑባትና የማዘናጊያ ወይም የውሸት የነፃ ገበያ ሥርዓት በነገሰበት የወያኔ ሥርዓት ውጥንቅጡ እጅግ ሰፊና  ምላሸ-ብዙ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደ ኤፈርት ዓይነት ያንድ ፓለቲካ ቡድን የንግድ ድርጅቶች ያለፍትሃዊ ውድድር፣ያለምንም ገደብ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከጥቅም ውጭ ሲያደርጉት ይታያል። የእነዚህ ድርጅቶት መሪዎች የፓለቲካ መሪዎች ሆነው ስናይ፤ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለሥልጣናት ትላልቅ የሙስና ወንጀል ውስጥ ተዘፍቀው ሲዋኙ ስናይ እና ጫት ነጋዴ ባለሥልጣናት በፈሉበት ዘመን ትውልዱ የሚማረው ከቶ ምን ሊሆን ይችላል? ካለውድድር መክበርን፤ በአቋራጭ መበልጸግን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ሙሰኝነትን፣ ብልጠትን፣ ተንኮልን … ወዘተ ካልሆነ በስተቀር። በአናቱ ድህነትና ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሲጨመርበት መዘዙ የከፋ ይሆናል። የወያኔዋ  ኢትዮጵያ ሰዎች በዘራቸውና በፓለቲካ ድጋፋቸው ምክንያት በሁለት ቀን ፎቅ ዘርተው የሚያበቅሉባት አገር ሆናለች።
7.   የፓለቲካው ሥርዓት
የፓለቲካ ሥርዓቶች (የመንግሥት ሥርዓቶች) በተፈጠሩበት አካባቢ እና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ  ላልታወቀ ጊዜ ለሚቀጥሉ መልካምም ሆነ መጥፎ ክስተቶችና አሻራዎቻቸው ቀጥታ ተጠያቂ  ናቸው።
የወያኔ ሥርዓት እንደ አንድ ሥርዓት  በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው እጅግ አደገኛ የተንሸዋረረ አካሄድ እና እያስከተላቸው ያሉ ውጤቶች ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። የወያኔ ብሔር ተኮር ፋሺዝም ከላይ በ5 ንዑስ ርዕሶች ሥር ለመጥቀስ ከተሞከሩ ጉዳዮች እስከ ለጊዜው ያልተገለጡልን ምስቅልቅሎች ተጠያቂ ነው። ሥርዓቱ ባህሪው ያደረጋቸው ዘረኝነት፣ ስርቆት፣ ዝርፊያ፣ ጨለምተኝነት፣ አውዳሚነት፣ ራዕይ አልባነት፣ ካልበላልኝ የፊት ጥርሴ ይርገፍ ባይነት፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባህሪይ፣ ቡድንተኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ ጥርጣሬ፣ አለመተማመን፣ ጥሎ ማለፍ ወዘተ  በትውልዱ ላይ ጥቁር ጥላቸውን እያጠሉ ነው። ለትውልዱ ተስፋን የሚተልም ሥርዓት ጠፋ። ሞዴል የሚሆን የፓለቲካ (የመንግሥት) አመራር ማግኘት ሕልም ሆነ።
ታድያ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ት/ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ተቋማት የፓለቲካ ሥርዓቱ የእኔን ትውልድ በሥርዓቱ አንጾ ኃላፊነት መሸከም የሚችል እና ነገን በራዕይ፣ በተስፋ የሚያይ ማድረግ ካልቻሉ ትውልዱ የት ሄዶ  ግብረገብነትን፣ ራዕይተኝነትን፣ ታላቅነትን ይማር? መቼ? እንዴት?
የእኔ ትውልድ እየናወዘ ነው። የእኔ ትውልድ ወኔው እየሞተ ተስፋው እየሟሸሸ፣ እየደነዘዘ ነው። ነገ የሚባል የተፈጥሮ ሥርዓት መኖሩንም እየረሳ ነው። ባለራዕይ መሆን ቅሌት ራስን ለትልቅ ቦታ እና ለሀገር ኃላፊነት ማጨት እብደት እየመሰለ ነው ። ይኸን ለማለትና ለመገንዘብ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም – ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ይበቃል።
ለዚህ በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ቢቻልም ጥቂቶቹን ብቻ ለማሳየት ልሞክር
i.  ጫት፣ መጠጥና ኤች አይ ቪ ኤድስ
እስቲ ለደቂቃ ቆም ብለን እናስብ። ምን ያህል ወጣትና ጎልማሳ ነው በዛሬው ጊዜ የማይጠጣና የማይቅም? ጫት ከዚህ በፊት በስፋት ከሚታወቅባቸው ቦታዎች አልፎ ስሙ እንኳን እንደ ሳጥናኤል ያስፈራባቸው በነበሩ የአገራችን ሰሜናዊ ክፍሎች ወጣቱ  ያለጫት መዋል እየከበደው ነው። ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ መቀሌ  … ወዘተ ለአንድ ቀን ጫት ቢጠፋ ብጥብጥ ይፈጠራል። በእኔ እምነት ጫት መቃምን ያወግዝ የነበረ “ጨዋ” ነኝ የሚል ማኅበረሰብ ልጆች ጫት ቤት የመከተም ምክንያት የኔ ትውልድ የመንፈስ መድቀቅና የሞራል መላሸቅ ነው። ከዚህ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ምናልባት መቃሙ፣ መጠጣቱ ወደሌላ የተስፋ መቁረጥ አዙሪት ውስጥ ይከተው ይሆናል። መቃም ካለ መጠጣት ይከተላል። መቃምና መጠጣት ካለ ወሲብ ይኖራል – ያውም ሊቅ ወሲብ። ሊቅ ወሲብ ካለ  ኤች አይ ቪ ኤድስ አለ። እዚህ ላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ የስርጭት መጠን በ 2002 ዓም 15 % የደረሰበት የአገራችን ከተማ  አለ ብል አንዳንዶች ሊገረሙ ይችላሉ። መገረም ግን አያስፈልግም። የሞራል ዝቅጠትና መዘዙ መለኪያ ኖሮት ቢለካ ወይም ማሳያዎች በጥንቃቄ ቢጠኑ አስደንጋጭ ውጤቶችን እናገኛለን። ይህ ባለ 15% ከተማ ጫት በብዛት ከሚቃምባቸው ከተሞች አንዱ ነው። ትውልዱ የእኔ ነው የሚለው አንድም ነገር አጣ። ነገ እንደሰማይ ራቀችው። ስለሆነም ጫትቤት ተደብቆ ብትመጪም ለራስሽ ብትቀሪም ጉዳይሽ እያላት ይገኛል። በምርቃና ትዝ ስትለው በመጠጥ ይረሳታል።  ስካሩ ሲለቀው ደጋግማ እየተከሰተች እንዳትረብሸው በበሽታ ይገላገላታል።
ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች ይልቅ ጫት ቤቶችን መርጠዋል። የመንግሥትና የፓለቲካ ተቋማት ቢሮዎች ሰራተኛ ቁጥር ከምሳ ሰዓት በኋላ ቢያንስ በግማሽ ይቀንሳል። ባለሥልጣኖች አዳዲስ ሞዴል መኪናዎቻቸውን ሸራ አልብሰው በልጃገረዶች ታጅበው ሺሻቸውን እያንደቀደቁ ጫት ሲያመነዥኩ ይውላሉ። ይህን ምን ይሉታል?
ii.   ማኅበራዊ ሴሰኝነት
በኢትዮጵያ ሁኔታ እንደ ወያኔ ዘመን ማኅበራዊ ሴሰኝነት ነግሶ ልቅ የወሲብ ስሜት ትውልድን ለቁም ገዝቶ የሚያውቅበት ጊዜ ያለ  አይመስለኝም። ወጣቱ በአንድ መወሰንን የኋላቀርነት (“የፋራነት”) መገለጫ አድርጎታል። በአንድ ቀን ከሶስትና ከዚያ በላይ ሴቶች ጋር የወሲብ ግኑኝነት መፈፀም የአሪፍነት መለኪያ ከሆነ  ሰነባብቷል። በአጠቃላይ ትምህርት ቤቱ፣ የመንግሥት ተቋሙ፣ ከተማው፣ ገጠሩ፣ በሙሉ አገሩ ሴሰኝነት ሴሰኝነት ሸቷል። የዚህ ትዕይንት ግንባር ቀደም ተዋንያን ደግሞ የመንንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው። ባለሥልጣናቱ ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ የሕዝብን ልጆች ያማግጡበታል። በግሌ በዚህ ድርጊት ውስጥ የማውቃቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብዙ ናቸው። ከቡናቤት ሴቶች ዘለው በየሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቸና ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በደላላ ሴት ሲያስመለምሉ ይውላሉ። ከዘረፉት ገንዘብ  አፍሰው ያሸክማሉ። ስለሆነም ለጋ ሕፃናት እህቶቻችን የንዋይ ውድድር ውስጥ ይገባሉ።  በዚህም ምክንያት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ያሉባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የእህቶቻችን ስም ዝርዝር ከነ ፎቶዓቸውና የስልክ አድራሻ ያካተተ ማውጫ በየሆቴሉ ውስጥ ተቀምጦ ያገኛሉ። እርስዎ መርጠው መደወል ወይም ማስደወል ነው። ይህንንስ ምን ይሉታል?
በኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአንድ የግል ክሊኒክ ብቻ 300 ሴት ተማሪዎች ጽንስ አስወርደዋል።  ይህንንስ ምን እንበለው?
ማኅበራዊ ሴሰኝነት የሚባል በሽታ ለክፎን  ከነሰቆቃችን እያሳቀና እያስደሰተ እየገደለን ነው።
iii.  ስደት
ወጣቱ ሞት በፊት ለፊቱ እንደ ጅብራ ተገትሮ ተመለስ እያለው እንቢ ብሎ  እየተሰደደ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር “ሜደተራንያን ውስጥ ልስመጥ፤ የውስጥ አካሌ ይሸጥ፤ ከፎቅ ልወርወር፤ በቡድን ልደፈር፤ በፈላ ውሃ ልቀቀል፤ ሠሃራ ይብላኝ” እያለ  የሚሰደደው ገንዘብ ፍለጋ  አይመስለኝም   በሀገሩ ያጣውን ተስፋና ራዕይ ፍለጋ እንጂ።
iv.  ውሸትና ብልጠት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዋሻል። ፓርላማው ይዋሻል። ቴሌቪዥኑ ቀን ተሌት ይዋሻል። ትንሹ ትልቁ ይዋሻል። ምድሪቱ የውሸት ምድር ሆነች። እውነት መናገር እና ብልህነት ሞኝነት ሆነ። ውሸትና ብልጠት ብልህነት ሆነ። አዋቂና ብልሆች በብልጦችና ውሸታሞች ማኅበረሰባዊ ሚናቸውን ተነጠቁ:: የውሸት መማር፤ የውሸት መቆፈር፤ የውሸት መሳቅ፤ የውሸት መናገር፤ የውሸት ሪፖርት፤ የውሸት ስብዕና፤ የውሸት  መኖር፤ ባጠቃላይ ዛሬን የውሸት አደረጉት። ዛሬ የውሸት ሁኖ  ነገ እውነት አትሆንም። “የውሸት እየሠሩ፤ የእውነት መብላት” ወንዝ አያሻግርም።
እነዚህ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው። በእኔ የግንዛቤ  አድማስ የተወሰኑ ናቸው። የእድሜ እና የእውቀት ታላላቆቼ ከዚህ የባሰ እና አስፈሪ የትውልድ መበስበስ ሊታያቸው እንደሚችል እርግጠኛ  ነኝ።
8.   መፍትሔ
በእኔ እምነት የእዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሔ አንድ ነው፦ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆነውን ወያኔን በፍጥነት ማስወገድ ዋናውና የመጀመሪያው ነው። ስርአቱን ለማስወገድ ሲሞከሩ የቆዩ የተለያዩ የትግል ስልቶች በግልጽ እያሳዩት የመጡት ጉዳይ ቢኖር ወያኔን በፍጥነት ማስወገድ የሚቻለው ህዝባዊ እንቢተኝነትን አና የመሳሪያ ትግልን ባጣመረ ሁለገብ የትግል ስልት ነው :: ወያኔን ማስወገድ  ብቸኛው እና የመጨረሻው መፍትሄ  ሊሆን ግን አይችልም:: ይልቁንም በህዝብ ነጻ ፍላጎት ወደ ስልጣን በመጣ የፖለቲካ ስርአት መተካት ያስፈልጋል:: ስለዚህ በህዝብ የተመረጠ እና ለህዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ ስርአትን መፍጠር ሁለተኛው ወሳኝ ምእራፍ ነው:: እንዲህ ሲቀርብ ታዲያ ቀላል ይመስላል:: ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይ ደግሞ ራሳቸውን ካደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተቆርቋሪዎች እጅ  ተሰርቶ እንዲቀርብ የሚጠበቀው የቤት ስራ እጅግ ከባድ እና ውስብስብ ነው:: ከላይ የተዘረዘሩ ሃቆች ባለቤት የሆነ ሃገር እና ትውልድ ተሸክመን፣ አሳዛኝ ወቅት ውስጥ ቆመን የምንመኘውን በዴሞክራሲያዊ ስርአት ላይ የቆመ ነፃ ሃገርና ነፃ ህዝብ ማየት፣ ማግኘት፣ መኖርና መሆን የምንችለው ከችግሩ ፊት በድፍረት መቆም እና መጋፈጥ አልፎም መፍትሄ አፍላቂ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ስንችል ብቻ ነው:: የምንፈጥረው ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚተከልበት ብሎም ለዘመናት ተጠብቆ  የሚቆምበትና የሚፋፋበት ለም መሬት የመፍጠር ጉዳይ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ  እንዳላየን ተሸፋፍነን የምናልፈው/የምንሻገረው/ ጉዳይ አይደለም:: ጠንካራና ነጻ ተቋማትንና የምንመኘውን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚያሳትፍ የሁላችን የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርአትና ሃገር ለመገንባት ከራሱ ጋር የታረቀ፣መንፈሰ ጠንካራ፣የነቃና፣ለነገ የሚጓጓ ማህበረሰብ በተለይ ወጣት ትውልድ ያስፈልጋል::ይህ ሲሆን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር ምቹ መደላድል አስቀመጥን ማለት ነው:: እዚህ ደረጃ ላይ ቆሞም ዘላቂ የሆነ የባህል ህዳሴን እና ማህበራዊ አብረሆትን መመኘትም ማሳካትም ይቻላል:: የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ወያኔን በመሳሪያ ትግል ማስወገድ የመጀመሪያው ዋና ምእራፍ ነው ብሎ ሲነሳ ለሁለተኛው ምእራፍ መፈጠር የሚያስፈልገው ዋናው ቅድመ ሁኔታ ያስጨንቀዋል:: ሰው::!!! ራዕይ ያለው ነገን በተስፋ የሚያይ ሰው::!! የዴሞክራሲንና ነፃነትን ትርጉም የተረዳ ና በውስጡ ያሰረጸ ወጣት ትውልድ::!!!!  ስለሆነም ወያኔ የዘመኑ ትወልድ ላይ እየፈጠረ ያለው የመንፈስ ድቀት እና ልሽቀት ሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለሰከንዶች ሊዘናጋበት የማይገባ የዴሞክራሲ ስርዓት ምስረታችን ፈተና መሆኑን በጥልቅ መገንዘብ በእጂጉ ያስፈልጋል:: በመሆኑም የወጣት ምሁራንን ትኩስ አቅም ከሀገሪቱ አንጋፋ ፖለቲከኞች የዘመናት የትግል ተሞክሮ ጋር በማዋሃድ ተመስርቶ የሚመራው ድርጅታችን ተዋጊ ብቻ ሳይሆን ለዴሞክራሲያዊ ስርአት መፈጠርና በዘላቂነት መቀጠል እንዲሁም ለህዝባችን ሁለንተናዊ ለውጥ  እርሾና አጋዥ የሚሆን ብቁ የሆነ የሰው ሀይል የመፍጠር ጉዳይ ያሳስበዋል:: አቅዶ ይሰራበታል:: እየሰራበትም ይገኛል:: ስለሆነም  ለጋራ ሃገራችን እጣ እና መጭ ተስፋ በዚህ ረገድ በጋራ በመስራትና በመነቃነቅ የትግሉን እድሜ ማሳጠር ብሎም የትግሉን ውጤት ማሳመር ይኖርብናል:: ለዚህም ብዙ ይጠበቃል:: በጋራ በጽናት መቆም ይኖርብናል: ይህን ማድረግ ከቻልን በጋራ፣ ለጋራ የሚሆን አጓጊ ነገን መፍጠር እንችላለን።

No comments:

Post a Comment