Thursday, May 16, 2013

ሚያዝያ 27-የኢትዮጵያ ትንሳኤ!


ዘንድሮ (ማለትም 2005 ዓ.ም) የትንሳኤ በዓልና የሚያዝያ 27ቱ የድል በዓል ተገጣጠሙ፡፡ ባሕረ ሃሳብ እንደሚያሳየው ከሆነ የትንሳኤ በዓልና የሚያዝያ 27 ቀኑ የድል በዓል በ1994 ዓ.ም ተገጣጥመው ነበር፡፡ ወደፊትም በ2016 ዓ.ም፣ በ2089 ዓ.ም፣ በ2100 ዓ.ም፣ በ2184 ዓ.ም፣ እና በ2263 ዓመተ ምህረትም ይገጣጠማሉ፡፡ ሁለቱ በዓላት ከመገጣጠማቸውም በተጨማሪ የሚያመሳስላቸው አንድ ቁብ አለ፡፡ ያለ ፍርድና ያለ ምንም ሃጢያቱ ሰሞነ-ሕማማቱን ተሰቃይቶና ተንገላቶ በቀራኒዮ ዓደባባይ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስና፣ ያለጢያቷ የወልወል ግጭትን ሰበብ አድርጎ ፀብ በጫረው ፋሺስታዊ ኃይል ፍዳዋን ያየችው ኢትዮጵያ፣ ማይጨው ላይ ሙሉ-ለሙሉ ከተፈታች በኋላ ፋሺስታዊ እባጭ ጫንቃዋን ነክሷት ያለ ፍርድ የተገደለችበት በመሆኑ ነው፡፡ ሞትን ድል አድራጊው ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን፣ በዕለተ ሰንበት ከሙታን መካከል እንደተነሳ ሁሉ፣ የኢትዮጵያም ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ነፃነት ከአምስት የጽልመት ዓመታት በኋላ ዳግም ትንሳኤውን አገኘ፡፡ ያም ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ሆነ፡፡ የነፃነት ችቦ የተለኮሰበትና የኢትዮጵያም ትንሳኤ የተረጋገጠበት ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ሆነ፡፡
ከአምስት ዓመታት በፊት በሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም የፋሺስትን ግፈኛ ድል ለማብሰር፣ ማርሻል ባዶሊዮ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አስወርዶ፣ ቀይ-ነጫና-አረንጓዴውን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን ነበር፡፡ ልክ በአምስት ዓመቱ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት ዓደባባይ ላይ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አስር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ (ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፡፡ 2005 ዓ.ም፣ ገጽ-409/10)፡፡ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ነፃነት ትንሳኤና የመላ ሕዝቦቿም ድል አድራጊነት (ታሪክ ሠሪነት) ተረጋገጠ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱና ኢትዮጵያዊያንም ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን የነፃነት “አዲስ ዘመን” ዜሮ-ዜሮ አንድ (001) ብለው ጀመሩ፡፡

ሚያዝያ 27 ቀንን ስናስብ በዐይነ ሕሊናችን የሚመጣብን ሌላም ውዝግብ አለ፡፡ እርሱም፣ በደርግ ዘመን ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ የሚያዝያ 27 ቀኑ የድል በዓል ወደ መጋቢት 28 ቀን እንዲዛወር ተደርጎ የነበረው ነው፡፡ የደርግ አባላቶቹ በዋናነት ያሰሙት ርካሽ ፕሮፓጋንዳ የሚለው፣ “ይህ 34ተኛው የድል በዓል ወደ መጋቢት 28 ቀን የተዛወረው፣ እንደቀድሞው የንጉሡን ታሪክ ለማሞካሸት ሳይሆን፣ የድሉ ባለታሪክ የሆነውን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ፣ እውነተኛው የታሪክ ቀን ስፍራውን እንዲያዝና ሕዝቡም በራሱ ደም የገነባውን ታሪክ በእጁ መልሶ እንዲጨብጥ ለማድረግ ነው፤” የሚል ሃተታ ያቀርባል (አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 28/1967 ዓ.ም፣ ገጽ-1 እና 9)፡፡ ቀሽም ሀተታ ነው፡፡ በመጀመሪያ በመጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ሜጀር ጄኔራል ካኒንግሃምና ኮሎኒያል ጦሩ አዲስ አበባን የተቆጣጠሩበት ዕለት እንጂ የሠፊው ሕዝብ እውነተኛው የታሪክ ቀን አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀን ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከስምንት ወራት ያህል ኢትዮጵያ በእንግሊዞች የኮሎኒያን ሞግዚት አስተዳደር ስር የወደቀችበት ዕለት ሆነ፡፡ ኢምፔሪየሊስትና ካፒታሊስቶችን አልወድም የሚለው ደርግ፣ ጭራውን ሸጉቦ በኢምፔሪያሊስቷ እንግሊዝ ብብት ውስጥ ገባ፡፡ ሁለተኛ፣ ሚያዝያ 27 ቀንን “ለሠፊው ሕዝብ” እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስገድደው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ሁሌም ገዢዎች በተቀያየሩ ቁጥር የድል ቀናት፣ የስታዲዮሞች ስያሜ፣ የአዳራሾችና የተቋማት መጠሪያም መቀያየሩ የአገዛዞች ባሕሪ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከ1967 ዓ.ም (ከ34ተኛው የድል በዓል አንስቶ) እስከ 1988 ዓ.ም (የ55ተኛው የድል በዓል) ድረስ ለሃያ ዓመታትም ያህል መጋቢት 28 የድል በዓል መከበሪያ ዕለት ሆነ፡፡ ሚያዝያ 27 ዓደባባይም ስሙ ተቀይሮ (ሌላ የአብዮት ስም ወጥቶለት) መጋቢት 28 ዓደባባይ ተባለ፡፡
የደርግ ዘመን ጭፍን ጥላቻውን (እንደወረደ) ከምስራቁ ዓለም ዘርፎ፣ የ1917ቱ የሩሲያ አብዮተኞች ያደረጉትን ሁሉ እንዳለ ኮርጆ አረፈው፡፡ (የሩሲያ ዕብዶች የዛሩን መንግሥት ከገረሰሱ በኋላ ያደረጉት የከተሞች ስም መለወጥና የተለያዩ ተቋማትን ስያሜ መቀያየር ነበር፡፡ ይኼንኑ የግንጥል ጌጥ የማንጠልጠል በሽታ፣ የኢትዮጵያም “አብዮታዊ ነን” ባይ ዕብዶች ደገሙት፡፡) መቼም ቢሆን፣ በምን ተዓምር በመጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የድል ቀን ሊሆን እንደሚችል ሊያስረዱን አይችሉም፡፡ በዕለተ መጋቢት 28 ቀን ንጉሠ ነገሥቱ በደብረ ማርቆስ በንጉስ ተክለ ሃይማኖት ዓደባባይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በሰቀሉበት ዕለት አመሻሹ ላይ አዲስ አበባን የተቆጣጠረው ጄኔራል ካኒንግሃምም የኢትዮጵያን ባንዲራ አዲስ አበባ ላይ አሰቅሏል፡፡ በሚያዝያ 27 ቀን ከፍ ያለው ሰንደቅ ዓላማችን፣ የመላው ኢትዮጵያውያንን የአንድነትና የብሔራዊነት መለያ በሆነውን የምኒልክ ፀዐዳ ቤተመንግሥት ዓደባባይ መሰቀሉ የበለጠ ውክልናና ግርማ እንደሚኖረው ሳያይመረምሩ ሚያዝያ 27ን ወደ መጋቢት 28 ቀን ቀየሩት፡፡ ረብ የለሽና ተራ የፖለቲካ ቁማርም ቆመሩ፡፡ (ደርግ ተገርስሶ ወያኔ/ኢሕአዲግ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ (በሰፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርምና) ደርግ ታሪክ ሠራሁበት፣ ለሦስት ሺህ ዘመናት የተንሰራፋውን ንጉሳዊና ፊውዳላዊ አገዛዝ ገረሰስኩበት ያለውን ቀን (መስከረም 2ን) ድራሹን አጠፋው፡፡)
ስለሚያዝያ 27 ቀን ስናስብ ከፊታችን ድቅን የሚሉብን በርካታ ታሪካዊ ቀናት አሉ፡፡ 1ኛ. ከላይ እንደገለጽነው ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም የሽንፈታችንም የውርደታችንም ማሳያ ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ዕለቱ ወራሪዎች እስከምን ድረስ ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ እንደሚጥሉት ቅልጥጥ አድርጎ ያሳየ ዕለት ነው፡፡ 2ኛ. ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ነፃነት ትንሳኤውን ያየበትና ብሔራዊ ሉዓላዊነታችን የተመለሰበት እንደሆነ አውስቻለሁ፡፡ 3ተኛው የሚያዝያ 27 ቀን ታሪካዊነት የሚገለጽበት ዕለት ደግሞ ሚያዝያ 27/1935ና ሚያዝያ 27/1936 ዓ.ም ናቸው፡፡ በሚያዝያ 27/1935 ዓ.ም የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጦ በሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም የተመረቀው የድል ሐውልት (አራት ኪሎ ላይ የቆመሙና በመኪናና በእግር እየገረመምነው የምናልፈው ይህ ሐውልት) ተሠርቶ የተመረቀበት ዕለት ነው፡፡ ሁለት ዓመት ከስምንት ወራት ከቆየው የእንግሊዞች “በላዔ-ነፃነት” የሞግዚት አስተዳደርም በትክክል ነፃም የወጣነው በዚህኛው የሚያዝያ 27 ቀን ነው፡፡ 4ኛ. ሚያዝያ 27/1947 ዓ.ም ነው፡፡ ከ10 ቀናት በፊት በሚያዝያ 17/1947 ዓ.ም ትልቁን ፀሐፌ ትዕዛዛቸውን (ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን) የአርሲ አገረ ገዢ አድርገው ከሸኙ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ መጋረጃቸውን ሙሉ ለሙሉ ገልጠው፣ “ከሥልጣን አራስ ቤት” ያለምንም ተቀናቃኝ በድል አድራጊነት የወጡበት ዘመን ነው፡፡ 5ኛ. አስራ አምስት ሚኒስትሮቻቸውን፣ አገረ ገዢዎችንና ባለሟሎቻቸውን (በተለይም የድልና የነፃነት ታላቅ አርበኛ የነበሩትን ራስ አበበ አረጋይን ካጡ በኋላ) በ53ቱ መፈንቅለ መንግሥት ያከበሩት የሚያዝያ 27/1953ቱ ዓ.ም የድል በዓል መጥሮ ጥላ ያጠላበት ነበር፡፡ ከ13 ዓመታት በኋላም የተከበረው የሚያዝያ 27/1966 ዓመተ ምሕረቱ የድል በዓል እጅግ አሳዛኙም አስገራሚውም ነበር፡፡ አሳዛኝነቱ ንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ የድል በዓልን ያከበሩበት ዕለት በመሆኑ ሲሆን፤ አስገራሚነቱ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በዚያች ቀውጢም ሰዓት ለ30 ዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን የሚያዝያ 27 ቀን ፕሮግራም ያለማዛነፍ ማድረጋቸው ነበር፡፡ ይባስ ብለው አበባ እያስነሰነሱ ክብረ በዓሉን በተለመደው መርሀ-ግብር መሠረት አከናወኑት፡፡
እዚህ ላይ አንባቢያን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው የበዓሉ አከባበር ፕሮግራም እንዴት ነበር ብለው መጠየቃቸው እንደማይቀር እርግጠኞች ነን፡፡ ስለሆነም፣ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ የነበረውን መርሀ-ግብር ከአዲስ ዘመንና ከኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጦች ባገኘነው መረጃ መሠረት እናቀርብላቸኋለን፡፡ ልክ ከጧቱ 12፡00 የክብር ዘበኛና የፖሊስ ማርሽ ቡድኖች ሰልፋቸውን ከአራት ኪሎ እስከ ምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ድረስ ይይዛሉ፡፡ ልክ ከጧቱ 12፡15 ሲሆን መኳንንቱ፣ መሳፍቱ፣ ሚኒስትሮችና ወይዛዝርት በምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ከጧቱ 1፡00 ሲሆንም፣ ጃንሆይ ከኢዮቤልዩ ቤተመንግሥታቸው (ከውጭ ጉዳይ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው) ተነስተው ወደ ምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በሞተረኛ ታጅበው ይሄዳሉ፡፡ ከጧቱ 2፡00 ሰዓትም ሲሆን የክብር ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊት፣ የፖሊስና የሀገር ፍቅር የሙዚቃ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያ ተገኝተው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን ያሰማሉ፡፡ ከጧቱ 2፡45-3፡00 ሲሆን ደግሞ ከምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን እስከ ኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ድረስ ያለው መንገድ ለትራፊክ ዝግ ሆኖ፣ ንጉሠ ነገሥቱ በሞተረኛ ታጅበው ከቅዳሴ የሚመለሱበት ሰዓት ይሆናል፡፡ ከ3፡00-3፡05 ባሉት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ዕለቱን በማሰብ የአዲስ አበባ አብያተ-ክርስቲያናት ደስታቸውን ያለማቋረጥ ደወላቸውን በመደወል ይገልጣሉ፡፡ ከረፋዱ 4፡00 ወይም አንዳንዴ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት ሲሆን የውጭ አገር መንግሥታት ወኪሎችና ታላላቅ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች በተዘጋጀላቸው የክብር በዝገብ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ፡፡ ልክ 5፡00 ሲሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ በከተማው ሕዝብ ሥም በድል ሐውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 26/1945፣ 1953፣ 1966፣ ገጽ-1)፡፡ (ባሕረ ሃሳብ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የትንሳኤ በዓልና የሚያዝያ 27ቱ የድል በዓል ተገጣጥመው አያውቁም፡፡)
ከላይ እንዳተትነው፣ ደርግ (አባ-ጉልቤ) ሚያዝያ 27 ቀንን በኃይል መቀየሩ ሳያንሰው፣ ካኒንግሃም አዲስ አበባን የያዘበትን መጋቢት 28 ቀን ማክበሩም ሳያንሰው፣ የበዓሉን ማክበሪያም ቦታ ሦስት ጊዜ ቀያይሮታል፡፡ የ1967ቱ የድል በዓል የተከበረው በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ (ጊዮርጊስ አጠገብ) ነበር፡፡ ከ35ተኛው የድል በዓልም አንስቶ እስከ 50ኛው የድል በዓል ድረስ ያከብር ነበረው በአብዮት ዓደባባይ ነበር፡፡ ምናልባትም ከደርግ ዘመን የድል በዓል አከባበር ስነ-ሥርዓት ውስጥ በጎ ሊባል የሚችለው፣ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮም በዋና ዋና ከተሞች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መጋቢት 28 የተባለውን (የድል ቀን) እንዲያከብር አድርጓል፡፡ መጋቢት 28ም በሕዝቡ ልብ ውስጥ ሰርፆ እንዲገባና የበለጠ እንዲታወቅ ሲልም የተለያዩ መዝሙሮችንና ዘፈኖችንም አዘፍኗል፡፡ ብዛቻችን የምናስታውሰው የተስፋዬ ገብሬ “መጋቢት 28፣ የድላችን ቀን፤ ይከበር ዘላለም በሀገራችን፡፡ እና “መጋቢት 28፣ በያመቱ ይምጣ፤ የናንተም ጦር ጋሻ፣ ከያለበት ይውጣ!” የሚለው ጣዕመ ዜማ ያንን ወቅት የሚመሰክር አብነት ነው፡፡ (ተስፋዬ ገብሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ፣ ሚያዝያ 27፣ የድላችን ቀን፤ ይከበር ዘላለም፣ በሀገራችን!” ብሎ ሊከልሰው (Remix) ሊያደርገው ይችል እንደነበር እገምታለሁ፡፡)
የድል ቀን ዘፈንና ዝማሬዎች ሲያንሱት ነው፡፡ የነፃነት መጀመሪያው ድል ነው፡፡ ከአምስት ዓመቱ የባዕድ ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነት የታደሰበት፣ መታሰቢያ “የድል ቀን” ተብሎ መከበሩ መሠረታዊ ምክንያትና ትርጉምም አለው፡፡ ያለ ድል ነፃነት አይገኝም፤ ያለ ድል ነፃነት አይጠበቅም፡፡ አንድ ሕዝብ የነፃነቱም ባለቤት ለመሆን የድሉም ጌታ መሆን አለበት፡፡ የድል ራስና ፊታውራሪዎች ደግሞ ትግልና መስዋዕትነት ናቸው፡፡ ክርስቶስ የመንፈስ አርነትን ለሰው ልጆች ለመስጠት በመጀመሪያ ሞትን ድል ነስቷል፡፡ ሞትን ድል ለመንሳት ደግሞ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ትንሳኤም ሆኗል፡፡ ለጥቅምና ለፍርፋሪ (ለሠላሳ ብር አበል ሲሉ ሀገርንና ወገንን አሳልፎ መስጠትን የሚያክል ቅጥረኝነት የለም፡፡ ከዚህ ወዲያም ይሁዳነት የለም፡፡ ከዚህም በላይ እየሳሙ አሳልፎ መስጠት የለም፡፡) ይሁዳዊነት ደግሞ ድሉን የበለጠ ያረጋግጠዋል እንጂ አያስቀረውም፡፡ በባዕዳን መገዛትና በቅጥረኞቻቸውም መመራት በቁም መሞት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ትንሳኤ ያለው ሞት ይሻላል፡፡ ሞቶ በድል መነሳት፤ በነፃነት መኖር ይበልጣል፡፡ ከትነሳኤው በዓልና ከሚያዝያ 27ቱ የድል ቀን መገጣጠም የምንማረው ትልቁ ቁምነገር ይኼው ነው፡፡
ለነገሩ ያህል ነው እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልም፣ ድልም፣ ነፃነትም አዲስ ነገሮች አይደሉም፡፡ ከብዙ ሺህ ዘመኖች አንስቶ ከሩቅ የመጣን ቅርብም የተነሳን ጠላትን እየተከላከለ ትጥቁን ሳይፈታ፣ ሐሞቱም ሳይቀጥን በጀግንነቱ ተመክቶ በነፃነቱ ኮርቶ ኖሯል፡፡ በብሔራዊ ነፃነት አጠባበቅ ረገድም የተዝናናበት (ወይም የተዘናጋበት) ዘመን የለም፤ ኖሮም አያውቅም፡፡ ምንም እንኳን የጠላት አመጣጥና የነፃነት አጠባበቁም እንደጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ቢለያይም ቅሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ነፃነቱን እንደዐይኑ ብሌን ነው የሚጠብቃት፡፡ ሥውር ጠላት አለ፤ ሥውር ባርነትም አለ፡፡ ሁሉንም እንደአመጣጡ ለመመከት ካስፈለገም ከጀግንነት ጋር ድርጅት፤ ከድርጅትም ጋር ብልህነትና ብልህ መሪም መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ፣ የማይጨው ጦርነት ውጤት በሽንፈት የተደመደመው በድርጅት ማነስ ነው፡፡ የመሣሪያ ኃይል ነው፡፡ የዘመናዊ አደረጃጀት ኃይል ብልጫ ነው፡፡
የፋሺስት ኃይል ኢትዮጵያ ድል ለማድረግ ያሰለፋቸው 25 ሺህ የጦር መኮንኖች፣ አምስት መቶ ዘጠኝ ሺህ ወታደሮችን፣ አንድ መቶ ሠላሳ ሁለት ሺህ እንሰሳትን፣ ሰባት መቶ ሰማኒያ ሁለት ሺህ ጠመንጃዎችን፣ ሃያ ሦስት ሺህ መትረየሶችን፣ ሁለት መቶ ሺህ ስድስት መድፎችን፣ ሃያ ስድስት ሺህ ታልኮችን ከነአዳፍኔያቸው፣ አንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊዮን ጥይቶችን፣ ሰባት ሚሊዮን አምስት ሚሊዮን የመድፍ ጥይቶችን ያደራጀ ነበር፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ግዙፍ ድርጅት ነበራት፡፡ ይህም ሁሉ አልበቃ ብሏት፣ በመርዝ ጢስና በመርዝ ጋዝም ተጠቅማለች፡፡
ቆራጦቹ የኢትዮጵያ ጀግኖች ግን የጦር ታክቲካቸውን ቀይረው፣ በማይጨው የጦር ግንባር ቢያፈገፍጉም እንኳን በጭራሽ በፍርሃት አልተፈቱም፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች በየዱር ገደሉ ተሰማርተው “ነፃነት ገዳሜ” አሉ፡፡ የፋሺስትን ኃይል በየጦር ሜዳው ፊትለፊት ተፋጠጡት፤ በየጋራው ተዋጉት፤ በየዓደባባዩመረ ተጋደሉት፡፡ ሞት አላስፈራቸውም ነበር፡፡ ድካም አላሸለባቸውም ነበር፡፡ በማይበገር እልህ በማያወላውል የመንፈስ ብርታት ፋታ አሳጥተው በወረራ የመጣውን ኃይልም ፋታ አሳጡት፡፡ የፋሺስትንም ኃይል ፋታ አሳጡት፡፡ የፋሺስት ኃይል ኢትዮጵያን ወረረ እንጂ ከቶ ኢትዮጵያውያንን ሊገዛ አልቻለም ነበር፡፡
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ባለፉት ክፍለ ዘመናት እንዳደረጉት ሁሉ፣ እንደሽምብራ ኩሬው፣ እንደዶጋሊው፣ እንደመቅደላው፣ እንደመተማውና እንደዓድዋው ሁሉ የትግሉን ምዕራፍ በማያዳግም ድል ዘጋው፡፡ በዚህ የድል መታሰቢያ ዕለትም ሁለት ነገሮችን በልቦናችን እናስባለን፡፡ ይኼንን ድል ለማስገኘት የተጋደሉትንና የተሰውትን ከልብ እናስባቸዋለን፡፡ በአምስት ዓመቱ የመከራና የግፍ ዓመታት በአካልም በመንፈስም የተጎዱትን ማሰብና መዘከር አለብን፡፡ ውለታቸውን የምንከፍላቸው ደግሞ የትግሉን ችቦ ተረክበን ለነፃነታችን ስንታገልና እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ፍትሕአዊነት የሰፈነባት፣ የሕዝቦች መብት የተከበረባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ስንችል ነው፡፡ ዛሬ ነፃነታችንን በሥውር የተነጠቅንበት ሰዓት ላይ ነን፡፡ ትንሳኤውና ሚያዝያ 27 የሰጡንን ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ለነፃነት ቀበኞች (ፀሮች) አስረክበን፣ “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል!” በሚል የፍርሃት መጽናኛ ውስጥ እንዳክራለን፡፡ የነፃነት መንፈስ ተንቦግቡጎ፣ እንደፋመና እንደተቀጣጠለ ለተከታዩ ትውልድም ድል አድራጊነትን ከነሙሉ ወኔውና ጀግንነቱ እንድናቀብለው ካስፈለገ፣ መጀመሪያ “የመንፈስ ትንሳኤ” ያስፈልገናል፡፡ ሚያዝያ 27 ደግሞ ያንን የመንፈስ ትንሳኤ እንዳይጠፋ አድርጎ ለኩሶታል፡፡ የክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ፣ ሞትን ድል አድርጎ የሰውን ልጅ ነፃ ያወጣበት ዕለተ-ፋሲካ ጋር ሲገጣጠም ደግሞ ከፍ ያለ ትርጉምና መልዕክት አለው፡

No comments:

Post a Comment