Monday, April 8, 2013

የችግራችን ጥልቀቱ – መክፈቻው መጥፋቱ



ዘግይቼ ነበር ይህን ጹሑፍ ከከረነት ያዬሁት „የሲፒጄውን ተሸላሚ” ዳዊት ከበደን መጨረሻ ማየት ናፈቀኝ ከጸሐፊ ክፈሌ ስንሻው አኔሳ“
እኔ ብዙም ድህረ ገፆችን አልጎበኝም። ውስኖችን ነው የማያቸው። አውራንባ ታይምስን ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን ገብቼ አዬሁት። የቀረበውን መረጃና የተሰጠውን አሰተያዬት ማገናዘብ ስለነበረብኝ። ኢሳት መኖሩ፤ መፈጠሩ የሚያንገበግባቸው የመኖራቸውን ያህል የሚያስደስታቸው ወገኖች ደግሞ እንዳሉ ከተሰጡት አስተያዬቶች ማንበብ ችያለሁ። ሁሉም የራሱን፤ የሚመስለውን፤ የግሉን አስተያዬት መስጠቱ መብት ነው። ነፃነት ፈላጊነታችን የሚለካበት፤ የሚሰፈርበት፤ የሚመዘንበት መሰፈርቱ ይህ ነውና። ዕድሉ ቢኖረን ይህን መሰል ነፃነት መስጠት ካልቻልን … ?!
በነፃነት ሕይወት ውስጥ የማይመቸውንም ተቀብሎ ተስማምቶ መኖር። በነፃነት ፍቅር ውስጥ ሁሉም የውስጡን ዘርግፎ እራሱን አስጎብኝቶ፤ ወደ አንድ የሚያስማማ፤ የሚያገናኝ፤ መስመር መጓዝ እንዲችል የፍቅር ሐዲድ መዘርጋት ነው። የሚሰጡ ትችቶች፤ የሚጠቀሱ ድክመቶች፤ የሚጠረቡ አስተያዬቶችን ተከታትሎ በአዎንታዊ ዕይታ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን በማስተዋልና በመርመር፤ ሊታረቁ የሚገባቸውን በትእግስት በማስታረቅ፤ የተዛቡትን በአዎንታዊ ቅን ዕይታ በማረቅና በማስተካክል ወደሚፈለገው አቅጣጫ ማቅናት የሚፈለግ ሲሆን፤ ይህንንም ወደነውና ከልብ ተቀብለነው ልናሳተናግደው የሚገባ ክስተት ሊሆን ይገባል። ከሁሉ በላይ ልምድና ተመክሯችን ከግብታዊነት ሊያድን እንዲችል በፍጹም ልቦናችን ልንፈቅድለት ይገባል።

ከአውራንባ ታይምስ ሆም ፔጅ እንደ አነበብኩት ከሆነ፤ ይህ ሁሉ ሰው በኢሳት ላይ በረዱን ሲልክ የኢሳት ተግባር ጎርብጦታል ማለት ነው። ስለዚህ የበለጠ ሰርቶ ጎርበጣው ላይቶለት ወይ እንዲፋራርስ ወይ ሰልቶ አጋር እንዲሆን ጠንክሮ፤ ብርትቶ፤ ተግቶ መስራትን ይጠይቃል። በሌላ በኩልም የኢሳት ደጋፊ መሆንም ሌላው የትግሉ አካል ነውናኢሳት … የበለጠ ጠንክሮ ለጠላቱ ጎርባጣ፤ ኮረኮንች፤ ጠጠርማ፤ ረመጥማ፤ ጦሮ፤ ወጀብማ፤ ሆኖ የብዙኃኑን ራዕይ ከግብ ለማደረስ እንዲችል ቀዳዳውን መሙላት – መሸፈን – የሚታዩ ግድፈቶችን ሳይሰስቱ ወይንም ሳይቆጥቡ ካለይሉኝታ መግለጽ ይገባል። የእውነት እንደ እራስ የውስጥ አካል በማዬት …. እልህ የጥንካሬ አዋልጅ ነውና!
ሂስ የሰላ ወይንም የዶደመ ቢሆንም የኑሯችን ወሳኙ አካል ስለሆነ፤ ልንለምደውና የራሳችን አድርገን ልንቀበለው ይገባል ብዬ አስባለሁ። የኢሳት ሀገር ውስጥ መረጃ አቅርቦቱ ፍሰቱ በሌላ ኃይል፤ ለዛውም በርቀት ስለሆነ ሊዛባ፤ ሊዛነፍ ይችላል። አይደለም በእሸቱ ኢሳት  በአደጉት፤ በበለጸጉት፤ በአንጋፋዎቹ ዓለምዓቀፍ የሚዲያ አውታሮች እንኳን ስንት ስህተት ይፈጠራል። እንኳንስ በለጋው ሚዲያ።  እንዲያውም በዚህ በሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች አሉ። የሚዲያ አውታሮችን በመደበኛ የሥራ ዘርፍ ቁጭ ብለው የሚተቹ። በሚዲያ ሥራ ስህትት ሊኖር ባይችል፤ በዚህ ሙያ የሚመረቁም፤ የሚሰሩም ዕውቅ የቴሌቪዢንና የራዲዮ ኃያሲ ባልኖሩ ነበር።
ሌላው በአደጉት ሀገሮች የህግ ባለሙያ ጋዜጦኞችም አሉ። ስለምን? ሰውና ስህተት፤ ፍጡርና ግድፈት ሊኖሩ ግድ ናቸውና። ጥፋቶችና ግደፈቶች በሚዲያ ህግጋት ደንብና አንቀጻት በዓለምዓቀፍ፤ አህጉር አቀፍና በብሄራዊ ደረጃ በፍትህ አደባባይ ይዳኛሉ። ማለት በእኛ ነው ሁሉ ነገር ብርቅና ድንቅ እንጂ በሌሎቹ የተለመደ ዕለታዊ ተግባር ነው። ለነገሩ ያለማደጋችን ምልክትም ነው። ኋላቀርነት ማለት አኮ ያልተመታጠነ ኢኮኖሚዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ተዛነፍ አሰተሳብንም ያካትታል።
ውድ አንባብያን ወገኖቼ። ድርጊቱን ቁጭ ብዬ ሳስበው ብዙ ነገር መጣብኝ። በዬዕለቱ ራህብ ብቻ ስንት ሰው በዬጎጆው ይገድላል? ይህ አለንገበገበነም ማለት ነውን? … የተፈለገው በበቀለ በአዲስ ቡቃያ ሚዲያ ላይ ስህተት ፈልጎ ቅጥቀጣ ነውን?! የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ስንት ወገን በብሄረሰቡ እዬተነጠለ ከሥራ በዬዕለቱ ይፈናቀላል? አንድ አባወራ ወይንም እማ ወራ ስንት ቤተሰብ ያስተዳድራል? የወር ገቢ ኖሮ ያልተቻለው ሕይወት የወር ማህያ ሲያቆም ምን ያህል ፈተና በዬቤቱ አለ? በዬቤቱ የለምን ፈጽሞ የማያወቁ ስንት የሀገር ተረካቢ ህጻናት በጠኔ እዬተቆሉ ነው? ከቶ ይህ አላንገበገበነም ማለት ነውን? የእኛ ፍለጋና የምርምር ተግባር የምንከውነው ማን? – ምን አጠፋ ነውን? የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
የቅርቡ እንኳን ባነሳ …  ያነ ለጋ ለእኛ ሲል እራሱን በቤንዚን አቃጥሎ፤ ነፍሱ እሱን እያደመጠችው ተርምጥምጦ፤ እንደ በግና በሬ ስጋ በእሳት ተጥብሶ የሞተው ሰማዕቱ የኔ ሰው ገብሬ መራር ሃዘን በተጨባጭ ኢሳት ሲዘገብ ወያኔ እርር ኩምትር ሲል …. ከቶ ይህ ዜና በአግባቡና በወቅቱ መጠናቀሩ እኛ ራሳችን፤ በትግሉ ውስጥ አለን ለምንለውም እንዴት ነበር ይሆን ያስተናገደንው? በነብዩ፤ በሽብሬ፤ በሰማዕቱ አሰፋ፤ በፕ/ አስራት እና በሚሊዮኖች ሥም በፖለቲካ ጥገኝነት ሥም መኖሪያ ፈቃዳችን ስናገኝ፤ ባለፈም ስንሸለም – ስንሾም ደማቸው ከቶ አይጠይቀንም ብለን ይሆን?! ኦ አምላኬ! የችግራችን ጥልቀቱ – መክፈቻው መጥፋቱ።
ህም! በታሪካችን፤ በህይወታችን ያዬነው — አራስ ጋዜጠኛ በእስር ቤት ከአራስ ልጇ ተነጥላ ስትታስር ከቶ ይህ ደልቶን ኖራልን?! ትናንትና መሳሪያ ደብቀኃል የተባለ ንጹሕ ገበሬ ነፍሰጡር ሚስቱ የባለቤቷን ብልት በጥርሷ እዬጎተተች በተፈጠረችበት፤ በኖረችበት፤ ማህበረስብ ኃፍርትን ተገዳ እንድተቀበል ሲፈረድባት – ከቶ ይህ ተመችቶን ነበርን?! ገና ሳይፈጠር ሞት የተፈረደብት ቀንበጥ ጽንሷስ እንደ ሰው ስናስበው ይህን የግፍ ክምር ከቶ ምን ልንለው እንችል ይሆን? ይህን መረጃ ኢሳት አጠናቅሮ ሲያቀርብ ያን ጊዜ እንደ አረሙ ወያኔ እኛም ድብን ብለን፤ ጭምትር ብለን ከቶ ተቃጥለን ነበር?! የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ወይ ጉድ! እንደ ሰው ሳይሆን እንደማይፈርስ ጣዖት እጅግ ይመልክባቸው የነበሩት ሄሮድስ መለስ ዜናዊ የዴሞክራሲ ገዳይነት፤ ዘረኝነት፤ የነፃነት ጠላትነት፤ ነብዩ አበበ ገላው ለዓለም ህዝብ ሲያጋልጥ፤ ኢሳት አውነቱን በድርጊት ዘግቦ ሲሳዬን፤ ከዚህ ቀጥሎም በነፃነት ታጋይ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሞት ፍርድና ጽኑ እስራት በተሰጠ ማግስት የጠ/ሚር ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ሕይወት፤ ሂደቱ በፍቅር እስከ መቃብር በካቴድራሉ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን በተከታታይ ሲፈጸም  ቆጥቁጦን ነበርን? አቤት! የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ወያኔ ከገባ ጀምሮ ሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ፤ ቀያቸውን ተገደው ለቀው በሀገራቸው መሬት ለዳግም ስደት ሲዳረጉ፤ ልጆቻቸውን እንደ ዕቃ የሚገዛላቸው ሲያፈላልጉ፤ ይህ ለትውልዱ የአደራ መክሊት ከቶ ጣፋጭ ነበርን?! በአራቱም ማዕዛናት አካላችን፤ ደማችን፤ ዘራችን በገደል ሲወረውር፤ በባሩድ ሲቃጠል፤ በጉማሬ ሲንገበገብ፤ ሲታሰር፤ ሲሰደድ ከዜግነት በታች ውርዶ ሲዋረድ፤ ሲንገላታ፤ ሲጋፋ፤ ሲደፋ፤ መብቱን ወያኔ እንዳሻው ሲያርሰው ይህም አልጋ በአልጋ ሆነልን ነበርን? የኛ ነገር ለሰሚው እኮ ግራ ነው። የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
እህህ! … ስንት ሳንሰማው፤ ስንት ሳንድርስበት የኦሾቲዝም ሚስጢር በዘመነ ወያኔ ተፈጽሞ ይሆን /// አንድ አመት ባስቆጠረው የእስልምና እምነት „የድምጻችን ይሰማ“ እንቅስቃሴና ወያኔ ያደረሰው ጥቃት፤ በ495 ዓ.ም የተገደመው ገዳማ ዋልድባ ንዑዳን ስደትስ? ይህስ የጫጉላ ሽርሽራችን ነበርን? የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ዛሬ የራሳችን አንደበት ኖሮን ህዝባችን፤ ወገናችን፤ ደማችን ድረሱልን የሚለውን ያን … አሳዛኝ፤ መራራ ድምጽ ከቤታችን ቁጭ ብለን መስማት መቻላችንም አቃጠለን፤ አንገበገበን? ከቶ በምን ስሌት ይሆን እኛ ለእኛ የምንገኝለት?! ከቶ በምን ቀመር ነው ፍላጎታችን ሳንዋሸው፤ ሳንሸሸው፤ ሳንሸውደው በግልጽነት አብረን ቁጭ ብለን ከፍላጎታችን ጋር ፊት ለፊት ልንመካካር የምንችለው።  የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ ….
እኛ! እንጃ! ምን አዚም እንዳለብን አይታወቅም? ማንምም አዚም እንዳደርገብን አይታወቅም። …. ወያኔ እንዳትሉኝ …. አናሳብብ። እራሳችን ለራሳችን መርዞች ሆነናል። አንድ መልካም ነገር በቅሎ፤ አድጎ፤ ለምልሞ ማዬት በሽታችን ነው። ወያኔ ከሞት ፍርድ ጀምሮ ዕድሜ ልክ ፍርድ የሰጣቸውን ወጎኖቻችን ባለ በሌለ ኃይለችን ስንወቅጥ፤ ስንቀጠቅጥ ትንሽ ከራሳችን ጋር መሆናችን መመርምር አለመቻላችን እንጃ፤ ማንነት አለኝ ለሚል ዜጋ ግራ ነው። ለመሆኑስ …. በጠላታችን ሞት የተፈረደባቸውን ወገኖቻችን፤ ሆነ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ለተፈረደባቸው ወጎኖቻችን እነሱን ለመተቸት፤ አቅሙ አለን? እንቻላለን? ይገርማል፤ የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ዖዬ! ትልቁ ችግራችን የኮፒ ራይት መሆኑ ደግሞ የችግራችን ጥልቀቱና መክፈቻው መጥፋቱን አንጥሮ፤ አበጥሮ ያሰዬናል። ተግባሩ እዬተሰራ ነው አይደለም? ይህ … ጉዳያችን አይደለም። ሩጫው ስህተት ፍለጋ። ለመዘንጠል። ለመገንጠል። ስንገርም። ማንም ይስራው? የማንም ይሆን? ደግሜም እላለሁ ማንም ይስራው? የማንም ይሁን?  ያ … በጠኔ፤ በስጋት፤ በባይታዋርነት ለሚንገላታው ወገንተኛ ነኝ ለሚል ክቡርና ጨዋ ወገን ይህ ጥያቄ ምኑም ሊሆን በተገባ ነበረ። መሰረታዊው የህሊና ጉዳይ የህዝባችን ተስፋ ጥግ አግኝቷል ወይ – ሊሆን በተገባ ነበር። የችግራችን ጥልቀቱ መክፈቻው መጥፋቱ።
ሚዲያ የአንድ ህዝብ ሆድ እቃ ነው። አብሶ ነፃነቱ በግፍ ለተነጠቀ፤ በእብሪት ለተቀማ ህዝብ ነፃ ሚዲያ ቅዱስ መንፈሱ ነው። ዓውደ ምህረቱ ነው። የሥርዬት መሰላሉ ነው። የርትህ መተንፈሻ ቧንቧው ነው። የነፃነት ጎጆ መውጫ – ማጫው ነው። የሰቀቀኑ ማሰታገሻ ፍቱን መዳህኒቱ ነው። ለራዕዩ ሙቀት – ጥንድ ድርቡ ነው። ለፍላጎቱ ስምረት – ሰጋር በቅሎው ነው። ከገዢዎቹ የሚላቀቅበትና የሚገላገልበት መንገድ – መሪው ነው። ማንነቱ ተከብሮ፤ ኢትዮጵያዊነቱ ጎልቶ፤ ሰንደቁ ደምቆ የሚታይበት ልዩ መንበሩ ነው።
መረጃ ድል ነው። መረጃ ገዢ መሬት ነው። መረጃ የራዕይ አውራ ጎዳና ነው። መረጃ ዛሬ ለነገ እንዲያበራ ቀንዲሉ ነው። መረጃ የተስፋ አንባሳደር ነው። ታዲያ በመላ አፍሪካ የተቋዋሚ ኃይሎች ትግል ታሪክ ውስጥ በአብነት ሁለቱንም አጣምሮ የራዲዮና የቴሌቪዢን ፕሮግራም ከፍቶ በሶስት አውራ ስትዲዮች የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የቻለው ወጣቱ ኢሳት ሊከብር ሊታገዝ ይገባል። ባለቤት አለው ካላችሁም፤ እንደ እኔ የልቤን እያደረሰ ስለሆነ ባለቤቱ ሊሸልም ይገባል ባይ ነኝ።
እህ! በገንዘብ ስብሰባውም ላይ ሰፊ አስተያዬት አውራንባ ላይ የተፃፉትና አነበብኩ። ኢሳት እኮ የዲታው የኤፈርትባለቤት አይደለም። ኢሳት እኮ በዘረፋና በሙስና የተዘፈቀ አንድ የዘር ድርጅት የሚያስተዳድረው አይደለም። አዎና! ኢሳት ድሃ ነው። ድህነቱ አያሰፍርም። ድህነቱ ግን የኢኮኖሚ ነው። ምክንያቱም ኢሳት ህጋዊ፤ መንግስታዊ በሆነ ሀገራዊ አስተዳደር ስር ያለ ሚዲያ አይደለም። ስደት ላይ የሚገኝ ሁለገብ ነፃ ሚዲያ ነው። ስደት ደግሞ ሁላችሁም እንደምታውቁት የቅበላ ሽርሽር አይደልም። በእያንዳንዳችን በስደት የሚደርስብን መከራና ፍዳ በእሱም ይታደማልና።
ኢሳት የህዝብ ሃብት ነው፤ ሃብትነቱ አባላቱ ሲያጠፋ ሊያርሙት፤ ሊያስተካክሉት ይቻላሉ። በማንኛውም ጊዜ። ምን ያህል ፍቅርን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ አፈራ ደግሞ ሁላችንም ያዬነው ነው። ሌላው ግን ግልጽነቱ ደግሞ አንቱ የተባለ መክሊቱ ይመስለኛል። ከዬትኛውም ወገን አይደለም አዎንታዊ አሉታዊ ሁነቶችን ሁሉ በማስተናገድ እረገድ ለታዳሚዎቹ የሰጠው ሙሉ ነፃነትና መብት ይበል ያሰኛል። ተሰዳቢዎችንም እኮ ሳይታክት ያስደምጠናል። … እኛ ትእግስት እናጣለን እሱ ግን በመቻቻል ወደ ራዕያችን አብረን በሚል መርህ ይመስላል … ያለገደብ ነፃነቱን ሰጥቷል … ወሸኔ ነው።
ሌላው የምደሰትብት ሰፊ ሥነ-ምግባር ደግሞ የኢሳት ጋዜጠኞች“በእፍታ ወይንም በእሁድ ወግ“ ሲታደሙ የተለያዬ ሃሳብን ይዘው እርስ – በርሳቸው ሲፋለሙ ማዬት ሌላ ዓለም ነው። አሁን ጋዜጠኛ ሲሳይና ጋዜጠኛ ተክሌ /ሞገደኛው አለቃ ተክሌ/ ሁለቱም በዬራሳቸው ዕይታ ሲከራከሩ፤ ሲጠራረቡ፤ ይቆዩና በሚያሰማማቸው ደግሞ ሲደጋገፉ ይታያሉ። በመጨረሻም በማዕዶተ የኢሳት ባልደረባነት ይታደማሉ። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ዓለም አለ። ሃሳብና ሃሳብ ብቻ እንዲታገሉ መፍቀድ፤ ለአሸነፈው ሃስብ ተሸናፊው ሃሳብ በፍቅር መገዛት በቃ! የነፃነት መንገዱን ኢሳት ጀምሮታል። እኔስ እደጉ ብያለሁ። …
… ይህም በመሆኑ የማነው? ለሚለው እኔ የእኔ ነው ብዬ ለመቀበል ችያለሁ። እኔ ደግሞ ፈንገጥ ያለ ተፍጥሮ ስላለኝ እንዲህ እንዳለ የምቀበለው ነገር ፈጽሞ አልነበረም። ግን አምኘበት ኢሳትን ተቀበልኩት። እና የእኔ ለሆነው አካሌ ደግሞ የምችለውን ማደረግ ፈልጌ እንጅ ተገድጄ ባለመሆኑ በነፃነት ጥሞኝና ተመችቶኝ አደርገዋለሁ።
አንድ ነገር ላንሳ ከቅድም ማሳረጊያዬ በፊት፤ … ብዙ ጊዜ ዋና ነገርን እንስታለን። እኛ መስራት ያልቻልነውን ነገር ሌላው ከሰራልን ደስ ብሎን ልቀበለውና በአክብሮት ልናስተናግደው ሲገባ ለምን እንጣላዋለን? መልሱን እናንተው። ከዚህም አልፎ  የጸረ ወያኔ ትግሉ አካል ሆንን መልካም በሚሰሩ ግለሰቦች፤ ድርጅቶች ላይ ጣት መቀሰር ደማችንና የተገንበት መሆኑ ደግሞ እስከመቼ ይሆን የምንገፋበት …?!  …. የችግራችን ጥልቀቱ መፈክፈቻው መጥፋቱ ነው።
ለማንኛውም የኢሳት መፈጠር የነፃነት ትግሉን ተከታታይነት በድርጊት አብሥሯል። ሰብዕናችን ልንጠይቀው የሚገባ ቁምነገር ትናንት ሲያልፍ ለዛሬ ላደረሰው የነፃነት ትግል፤ ከዚህ ያደረሰውን ህዝባዊ ተሳትፎ ዝክረ ሂደትና ውጤቱን ትንፋሹ ማደረግ እንዲችል ነው። ስለምን? ማናቸውም ተሳትፎ ወያኔን እንቅልፍ ከነሳ፤ ከላስደሰተ ለእኛ ድላችን ነውና። የተግባራችን ሰብላችንም ነው። ለነገም ለትውልዱ ታሪክ የጥሪት ትራስ።
እንደ ማሳረጊያ። ትችት ጥሩ ነው። አብሶ ለሥነ – ጥበብ የእናት ጡት ነው። ስህተት መፈጠሩ ደግሞ የግድ ነው። አብሶ የወገንን ስህተት ማጋናኑ ግን ፈጽሞ የተገባ አይደለም። ሲሆን ቀዳደውን ለመሸፈን መሞከር የተገባ በሆነ ነበር። የሆነ ሆኖ እንኳንስ ለጀማሪ። በዛ ላይ ወያኔ ስንት ጊዜ ነው ኢሳትን ፈርቶ የታገለውና ስርጭቱ እንዲቋረጥ ያደረገው። ከተንቀሳቀሰ ስህተት ይኖራል። ነገም አዲስ ስህተት ይኖራል። ለዚህ ኢሳት ቃል እንዲገባ አይገደድም። ፍሬ ነገሩና ብልህነቱ ስህተቶች እንዳይደገሙ ማደረጉ ላይ ነው። ሌላው እኛ ልንሰራ የሚገባን ብቻ እንሰራ … ዓላማ ላላው ማንነት መስካሪው – ድርጊቱ፤ ሚዛኑ – ውጤቱ፤ ዳኛው – ሰፊው ህዝብ ፤ታሪኩ – መሆን መቻሉ፤ ብቻ ነው።
እግዚአብሄር አምላክ የሰጠንን ማስተዋል እንጠቀምበት ዘንድ ሁላችንም ይርዳን።

No comments:

Post a Comment