ቀኑ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 1998 ዓ.ም፤ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ገደማ… አንድ የከተማ አንበሳ አውቶብስ ተሳፋሪ ሳይጭን ከመርካቶ ተነስቶ ወደ ጎማ ቁጠባ አቅጣጫ በባዶ እየከነፈ ቁልቁል ወርዶ ..ተ/ሃይማኖት ቤ/ክርስቲያን አደባባይን ከዞረ በኋላ ጥግ ይዞ ቆመ። ሹፌሩ አውቶብሱን ገትሮ ወዲያው ከአካባቢው ጠፋ። ለሁለት ሰዓት ገደማ አውቶብሱ እንደተገሸረ ቆየ።…በዚህ ቅፅበት አንዲት ነጭ ቶዮታ ፒካፕ (ታርጋ የሌላት ወይም ያለጠፈች) ከሱማሌ ተራ አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት እየከነፈች ከመጣች በኋላ < በላይ ተክሉ ኬክ> ቤትን አለፍ ብላ ቆመች። ከሹፌሩ ጎን ሲቪል የለበሰና ኮፍያ ያጠለቀ ሰው የተቀመጠ ሲሆን ከመኪናው ጋር ከተገጠመው ሬዲዮ መገናኛ በተጨማሪ ሁለት ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ይዟል።… 25 ወጠምሻዎች፣ ሁሉም ረዘም- ወፈር ያሉ ዱላዎችን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ገጀራ እንደጨበጡ እንዲሁም ከመካከላቸው ሁለቱ አነስተኛ ጀሪካን እንደያዙ…ከመኪናዋ ዘለው ወረዱ። ሁሉም የተቀዳደ ተመሳሳይ ድሪቶ አጥልቀዋል፤ « አደገኛ ቦዘኔ» መሆናቸው ነው። ነገር ግን « ሆን ተብሎ » የተዘጋጀ ድሪቶ እንደሆነ የሚያሳብቀው ….በግልፅ የሚታየው የሁሉም ፈርጣማ ጡንቻ ከጥሩ እንክብካቤ ጋር በስፖርት የዳበረና ወታደራዊ አቋም እንዲይዝ ተደርጎ የተገነባ መሆኑ ነበር።
ከመኪናዋ ዘለው ከወረዱ በኋላ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ « አትነሳም ወይ…አትነሳም ወይ …ወያኔ…ወያኔ..» እያሉ በመጮህ አንበሳ አውቶብሱን ተጠጉ። በያዙት የብረት ዱላና ስለታማ ገጀራ አውቶብሱን እንክትክቱን ካወጡ በኋላ በያዙት ነዳጅ አርከፍክፈው አቃጠሉት፤…ተመሳሳይ ጩኸትና ቅስቀሳ እያሰሙ ሽቅብ ወደ ሲኒማ ራስ አመሩ። ነጯ መኪና ከኋላ ደርሳ ሁሉንም ጫነች…ከዛም ወደፊት በፍጥነት እየካለበች አዲስ ከተማ ት/ቤት አካባቢ ደረሰች። ወጠምሻዎቹ ..የ <አትነሳም ወይ…> ቅስቀሳቸውን ሲቀጥሉ.. እግረመንገዳቸውን በቅርብ ርቀት የሚገኘው የቴሌ መ/ቤት ላይ ድንጋይ በመወርወርና ከደጃፍ ቆመው የነበሩ ሁለት መኪኖችን መሰባበር ይዘዋል። ከዚሁ ጐን ለጎን በመ/ቤቱ ግቢ የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ከድራማው መጀመር ቀደም ብሎ እንዲገቡ ተደርጎ ነበር። ያ ድርጊት ወይም ድራማ ሲፈፀም አይተው እንዳላዩ በማለፍ ቀጣዩን ይጠብቁ እንደነበረ በሰአታት ልዩነት አፈሙዝ በንፁሃን ላይ ሰድረው ይወስዱት የነበረው የጭካኔ እርምጃ በቂ ማመላከቻ ነበር፤ ዘግይቶ የሆነውም ይኸው ነው።..
በሰኔ ወር ግድያ ሲፈፀም በመጀመሪያ ኢላማ የነበረው ይህ ት/ቤት ነበር፤ በዛ ድርጊት ገና ያልሻረ ቁስል አለ። በሌሎች አካባቢዎችና ከተሞች የነበረው የተዳፈነ የተቃውሞ ቁስል ከዚህ የተለየ አልነበረም። በሕወሐት/ኢህአዴግ አስተዳደር የተንገሸገሸው ሕዝብ..እንኳን ቀዳዳ አግኝቶ ቀርቶ እንዲሁም፥ ትንሽ ነገር ቁጣውን እንደሚያገነፍለው ግልፅ ነበር። የተሰረቀ ድምፁን ለማስከበረም በፅኑ ይፈልጋል።.. በዚሁ መሰረት በአዲስ ከተማ ተማሪው ከአካባቢው ህዝብ ጋር በአንድነት ሆኖ.. <በተለኮሰው> ተቃውሞ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባበት።.. የተዳፈነው የሕዝብ እሳት በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተዛመተ ሔደ።
ያቺ ነጭ መኪና <ሴራዋን> ከውና በጎጃም በረንዳ በኩል ወደ ግራ ታጥፋ እየከነፈች…አባኮራን ሰፈርን እያሳበረች በዮሃንስ ቤ/ክ አድርጋ ወደ ሰሜን ሆቴል አመራች።.. <ቅልቦቹ> ተመሳሳይ የተቃውሞ ድራማ አቀጣጠሉ። ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በቦዘኔነት <ሽፋን> ያሰማራቸው ቅልብ ሃይሎች በኮልፌ ቀራንዮ አካባቢ አሰማርቶ ተመሳሳይ <ድራማ> እያቀጣጠለ ነበር። ..የተቃውሞ እሳት የጫረችው ነጯ ቶዮታ ..የማሳረጊያ ግዳጇን በሰሜን ሆ/ል አካባቢ ከተወጣች በኋላ ወጠምሻዎቹን ጭና ቁልቁል በመውረድ ወደ ማእከላዊ ወንጀል ፖሊስ መምሪያ ቅጥር ግቢ ነበር ሰተት ብላ የገባችው። በዚች መኪና ከፊት ተቀምጦ ትእዛዝ በመስጠትና ከበላይ አለቆቹ ጋር መረጃ ልውውጥ በማድረግ ሴራውን ሲመራና ሲያከናውን የነበረው ግርማይ (በቅፅል ስሙ ማንጁስ) የተባለ የሕወሐት አባልና በፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊ እንደሆነ በወቅቱ ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ባሻገር በአንዱ ስልክ ከጠ/ሚ/ሩ ጋር በቀጥታ ይገናኝ እንደነበረ ተረጋግጦዋል። (በነገርራችን ላይ ስለዚህ ጉዳይ መረጃው ለህዝብ ሳይደርስ ጋዜጦች ወዲያው ተዘጉ)
…ባጠቃላይ በዚህ መልክ በገዢዎቹ ሆነ ተብሎ በተለኮሰው የጥፋት <ሴራ> በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን በአደባባይ በጥይት እንዲቀጠፉ ሲደረግ፣ በ10ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ እስር ቤት ተጋዙ። የነመለስ/በረከት ቀጣዩ <ኢላማ> የቅንጅት አመራሮችንና ደጋፊዎችን፣ጋዜጠኞችን እንዲሁም ሌሎች ወገኖችን ማሰርና ማሰቃየት ስለነበር፥ ያሰቡትን ተግባራዊ አድርገዋል። ከትግራይ ሃውዜን የጀመሩት ህዝብን በጅምላ የማስፈጀት አረመኒያዊ የሴራ ተግባራቸው፥ በአርባባ ጉጉ፣ በበደኖ፣ ትግራይ ሆቴል(ፒያሳ)፣ ጋምቤላ …እያለ በመቀጠል የ97/98 ምርጫን ተራምዶ እነሆ በህዝበ ሙስሊሙና በአማራ ተወላጆች ላይ ቀጥሎ ይገኛል። ከቤኒሻንጉል እንዲፈናቀሉ የተደረጉት የአማራ ተወላጆች በተራ የወረዳ ካድሬዎችና ሹሞች ትእዛዝ እንደማይፈፀም በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ለዚህ ማስረጃው በጋምቤላ አሰቃቂ ፍጅት እንዲደርስ የተደረገው በወቅቱ የፌደራል ጉዳዮች ሹማምንት በነበሩት አባይ ፀሃዬና በምክትላቸው ዶ/ር ገብረአብ ባርናባስ ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጪነት እንደሆነ የተረጋገጠና በወቅቱም የሁለቱ የሕወሐት ሹሞች ስም ጭምር ተጠቅሶ በኢትኦጵ ጋዜጣ ይፋ መደረጉ ነበር። እንዲያውም አባይ ፀሃዬ በግምገማ ላይ ዶ/ር ገ/አብን ጥፋተኛ ከማድረጋቸው በተጨማሪ < አብሬው መስራት አልችልም፤ ስለዚህ በአስቸኳይ ይነሳልኝ> በማለት የጋምቤላውን ፍጅት በዶክተሩ ላይ ከመደፍደፋቸው ባሻፈር ለ/ጠ/ሚሩ ጥያቄ አቅርበው ይኸው ተፈፀሚ ሆኗል። …ይህ በሆነበት ሁኔታ በቤኒሻንጉል በወገኖቻችን ላይ የደረሰውና ሆን ተብሎ እንዲደርስ የተደረገው መሰሪ ተግባር ከሕወሐት/ኢህአዴግ ቱባ ሹማምንት እውቅና ውጭ ብቻ ሳይሆን የነርሱ ቀጥተኛ ትእዝዛ ያለበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
በመጨረሻም ፥ በህዝበ ሙስሊሙ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ የመብት ጥያቄና ተቃውሞ ውስጥ የተስተዋለው ጉዳይ፥ ህዝብ ምን ያክል ገዢዎቹን በአስተሳሰብ በልጦ እንደሄደ የሚያመላክት ጭምር ነው። ይኸውም በአንዋር መስጊድና ሰላማዊ ተቃውሞ በሚሰማባቸው አካባቢዎች አንበሳ አውቶብሶችን ሆን ተብሎ በማቆም ሙስሊሙ እንዲሰብራቸው በገዢዎቹ ሲሞከር ታይቶዋል፤ ገዚዎቹ እንዳቀዱት አውቶብሶቹ ሲሰባበሩ… የ97/98 ድራማ ለመድገምና በለመዱት ጭካኔ በጥይት የጅምላ ግድያቸውን ለመተገበር ነው። የሃይማኖቱ ተከታዮች ግን « አንሰብርም….አንሰብርም…» እየሉ በአንድ ድምፅ የነበረከትን የሴራ ድራማ በማክሸፍ ለመብታቸው መቆምንና ሰላምዊ ጥያቄ ማቅረብን ነው የቀጠሉት። ህዝብ ምን ያክል ቀድሟቸው እንደሄደ ጥሩ ማሳያ ነው።
No comments:
Post a Comment