Monday, April 8, 2013

የህወሓት/ኢሕአዴግ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ መቆም አለበት!



የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP) (ዴሞክራሲያዊ/Democratic)
ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ በመረጡት ሥፍራ የመኖር፤ ሠርቶ ሃብት የማፍራት፤ ቤተሰብ የመመሥረት…ወዘተ በማንም ሊሰጣቸው ወይም ሊነፈጋቸው የማይችል ሁለንተናዊ የዜግነትEthiopian People's Revolutionary Party (EPRP Democratic)መብቶቻቸው ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በዓለማችን የተነሱ የጎሣ እንቅስቃሴዎች ሁለንተናዊ የዜጎችን መብቶች በሚፃረር መልኩ አንድ-ወጥ የሆነ ወይም ከሌሎች ዘር የፀዳ ሀገርና መንግሥት ለመፍጠር ጥረዋል። ዓላማቸውን ሊያሳኩ ባልተቻሉባቸው ኅብረብሄር በሆኑ አገሮች ውስጥ ደግሞ የኤኮኖሚ፤ የፓለቲካና የወታደራዊ ኃይሉን በአንድ ዘር የበላይነት ለመያዝ ሲባል የዘር ማጽዳት ዘመቻ (ኤትንክ ክለዚንግ)ና የዘር ማጥፋት ዘመቻ (ጄኖሳይድ) ወንጀል መፈጸም የተለመደ ክስተት ሆኗል።
በዘጠናዎቹ መጀመሪያ ላይ የምሥራቁ የሶሻሊስት ካብ በተፈረካከሰበትና የሥልጣን ክፍተት በተፈጠረበት ወቅት፤ እነዚህ የጎሣ የወንጀል ቡድኖች በሕዝብ ውስጥ የነበሩ የፍትህ፤ የእኩልነትና የነፃነት ትክክለኛ ጥያቄዎችን በማጣመምና ለራስ እኩይ ዓላማ በማዋልና ሕዝብን በማሳሳት የጎሣ ወታደራዊ ኃይሎችን በማቋቋም አሰቃቂ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ፈጽመዋል። ዓለምአቀፍ የዜና ሽፋን ባገኙት ሀገሮች፤ ለምሳሌ በዩጎዝላቪያ፤ በሩዋንዳ፤ በኮንጎ፤ በሱዳን….ወዘተ ወንጀለኞቹ በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት መፈለጋቸውና አንዳንዶቹም ተይዘው ለፍርድ በመቅረባቸው ዘግናኝ ወንጀላቸውን እንዲያቆሙ ወይም እንዲሰወሩ አድርጓቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ግን ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ባለማግኘታቸው ወንጀሉ አሁንም በማንአለብኝነት በሰፊ እየተካሄደ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ወንጀል የተጀመረው የትግራይን ሪፕብሊክ እንመሠርታለን ባሉት እንደ መለሰ ዜናዊና ስብሃት ነጋ በመሳሰሉት በዘር ጥላቻ አባዜ የተለከፋ ግለሰቦች በድርጅቻቸው ውስጥ የበላይነት ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ነበር። መሠረታዊ ማጠንጠኛቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ለነበረው የባላባታዊ ሥርዓት ጭቆናዎች ተጠያቂው የአማራ ሕዝብ ነው የሚል ነው። ለዚህም ነው ለትግራይ ሪፕብሊክ ምሥረታም እንቅፋት ሊሆን የሚችለው አማርኛ ተናጋሪው ነው በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ፀረ-አማራ ኃይል እንዲፈጥሩና በአማራው ላይ እንዲዘምቱ ያደረጋቸው። አሁንም ከሃያ ሁለት ዓመት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ የምናየው ይኼው የፀረ-አማራነት ፖሊሲ በተግባር ሲተረጎም ነው። ይህንንም መርዘኛ የህወሓት ፓሊሲ በየቦታው በፈጠሯቸው ተለጣፊ ጅርጅቶችና ባደራጇቸው የጎሣ ወታደራዊ ኃይሎች አማካኝነት የዘር ማጽዳት ዘመቻውን በስፋት ተያይዘውታል።
ከጥቂት ወራት በፊት በጉራፈርዳ ወረዳ የታየው አሁን ደግሞ በቤኔሻጉል-ጉምዝ አካባቢ በሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ላይ እየተደገመ ነው። ንብረትን ቀምቶ፤ ነፍሰጡርንና አራስን ሳይቀር አፈናቅሎ ማባረርና የድብደባና የግድያ ወንጀሎች በአማራው ሕዝብ ላይ መፈጸሙ ከበፊቱም የነበረውን ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ እያደረጉት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይህ ዓይነቱ ዘግናኝ ወንጀል በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች በተለይም በአኝዋኩ፤ በኦጋዴኑ፤ በኦሮሞው፤ በአፋሩ፤ በሙርሲው …ወዘተ ማህበረሰቦች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጽሟል፤ አሁንም እየተፈጸመ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ይህንን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመበት ዋናው ምክንያት የፓለቲካ፤ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነቱን ለማስጠበቅ ስለሆነ ለዚህ እኩይ ዓላማው መሳካት እንቅፋት ናቸው ብሎ በሚገምታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈጸም እንደማይቆጠብ ግልጽ ነው።
ህወሓት/ኢህአዴግና ተላጣፊ ድርጅቶቹ አንድ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በመረጠው ቦታ የመኖር፤ የመሥራት በሕጋዊ መንገድ ንብረት የማፍራት፤ ቤተሰብ የመመሥረትና ልጆች የማሳደግ የማይገሰስ የዜግነት ሁለንተናዊ መብቱ እንደሆነና ማንም ፈቃድ ሰጪም ከልካይም ሊሆን እንደማይችል፤ ነፃ ፍርድ ቤቶች ባሉባቸው ሀገሮች በዘር ማጽዳት ወይም በዘር ፍጅት የተሰለፉ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ተከሰው በፍርድ ቤት ቅጣት እንደሚበየንባቸው የተገነዘቡት አይመስልም ወይም ሊቀበሉት አይፈልጉም። የአገር ሉዓላዊነት በሚል ሽፋን ከሕግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል ሊገነዘቡት ይገባል። በመሆኑም ማንኛውም ለሀገሩ የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ/ት በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለዓለም ኅብረተሰብ እንዲያሳውቀና ዓለምአቀፋዊ የዜና ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ግዴታ አለበት። እንዲሁም በወንጀለኛ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ መረጃዎችን በመሰብሰብ በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት ክስ መመሥረትም መታለፍ የሌለበት ጉዳይ እንደሆነ ልናሳስብ እንወዳለን።
በመጨረሻም ይህን በአደባባይ የሚፈጸመውን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለአንዴና ለሁል ጊዜ ለማስቆም የሚቻለው የፖሊሲው አራማጅ የሆነውን አምባገነን አገዛዝ በተባበረው የሕዝብ ክንድ ድባቅ ሲመታ ብቻ እንደሆነ ነው። አምባገነኑ አገዛዝ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተተካ ድረስ ይህ እኩይ ተግባር እየተስፋፋ መቀጠሉ የማይቀር ነው፤ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤት የሚያንኳኳበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም።
የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ተዋናኞች ባለፈው ሰሞን የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባዔ ተብዮው ላይ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ስለ ዴሞክራሲ፤ ስለመልካም አስተዳደርና ስለሙስና…ወዘተ በመናገር በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲያላግጡና ሲመፃደቁ ተስተውለዋል። “ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” የሚል ይትባሀል እንዳለ እያስታወስን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለህወሓት/ኢህአዴግ ልንነግረው የምንፈልገው በአምባገነኑ አገዛዝ የሚወራለት ዴሞክራሲውና መልካም አስተዳደሩ ቀርቶ ይህን ዘግናኝ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ባስቸኳይ እንዲያቆም ነው!
ዜጎች መብቶቻቸውን በትግላቸው ይጎናፀፋሉ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ለዘለዓለም ይኖራል!

No comments:

Post a Comment