ላለፉት አራት ዓመታት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቅዳሜ እና እሁድ የሄደ ሰው ወጣቷን ናርዶስን ሳያገኝ አይመለስም፡፡ ናርዶስ ገና የ20 ዓመት ወጣትእና በኪያሜድ የመጀመሪያ ዓመት የነርሲንግ ተማሪ ናት፡፡ ናርዶስ ዘሪሁን በየሳምንቱ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የምትመላለሰው በ‹‹አሸባሪነት›› ‹በእነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ› ከተከሰሱት 36 ሰዎች መካከል ዕድሜ ልክ የተፈረደባትን እናቷን ልትጎበኝ ነው፡፡ እነዚህ እስረኞች ሚያዝያ 16/2001 አመሻሹ 12 ሰዓት አካባቢ ነበር ሁሉም በያሉበት በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡ እኛም 4ኛ ዓመታቸውን ለማሰብ ተሰባስበን ወደቃሊቲ ማረሚያ ቤት በተለይ እማዋይሽ ዓለሙን ለመጠየቅ ሄደን ነበር፡፡ እንደተለመደው ናርዶስንም አገኘናት እና ብዙ ነገሮችን አጫወተችን፡፡
ናርዶስ ትረካዋን የጀመረችው እናቷን እና ሌሎችም በተመሳሳይ መዝገብ ተከሰው የተፈረደባቸውን ሰዎች አያያዝ ነበር፡፡ ‹‹ሳስበው የተረሱ ያህል እየተሰማኝ ነው፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሚዲያዎች ስለነሱ አይደለም እያነሱ ያሉት፡፡በእናቴ ክስ የታሰሩት ከ30 ሰዎች በላይ ናቸው፡፡ አንድ ሰሞን ከይቅርታ ጋር በተያያዘ ስማቸው እየተነሳ ነበር አሁን ግን ሁሉነገር የተረሳ ይመስለኛል›› በማለት የእስሩ ሕመም ለታሳሪዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ግን የሚረሳ ዓይነት አለመሆኑን ነገረችን፡፡
‹‹ሚያዝያ 16፣ አርብ ቀን ነበር ሁሉም የተያዙት›› በማለት ሲታሰሩ የነበረውን ጠቅላላ ሁኔታ በማስታወስ ትጀምራለች፡፡ ‹‹ለአንድ ሰው የመጡ የማይመስሉ ብዙ ሲቪል የለበሱ እና የፌዴራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች መሳሪያቸውን አቀባብለው ነበር ወደቤት የገቡት፡፡ ስልካችሁን አጥፉ ወደማንም እንዳትደውሉ አሉን፡፡ የብርበራ ማዘዣ ይዘው ነበር፤ ‹ቤት ልንፈትሽ ነው የመጣነው እማዋይሽ ዓለሙ በቁጥጥር ስር ውለሻል› አሏት ቤት ፍተሻው እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ቀኑ አርብ ነበር፤ እናቴ ደግሞ እስከ 12 ሰዓት ትጾም ስለነበር ከሥራ ወደቤት እንደገባች ‹ምግብ ስጡኝ› እያለች እያለ ነበር ፖሊሶች የገቡት ስለዚህ ምግብ ሳትበላ ውላ ነው ወደ እስርቤት የወሰዷት፡፡ ከዚያ በኋላ አራት ወራት ያክል ዓይኗን አላየነውም ነበር፤ ትሙት ትኑር የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ደግነቱ በሌላ ጉዳይ ታስራ በተፈታች ሴት አማካይነት መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ‹አንቺ ደህና ከሆንሽ ሽሮ እና ጎመን ሰርተሸ አስገቢልኝ፤ እኔ ደግሞ ደኅንነቴነን የባናና ማስቲካ ወረቀት እልክልሻለሁ፡፡ ደኅና ካልሆንኩኝ ግን ያ ነገር ይቀራል› ብላ ላከችብኝ፡፡ ከዚያ እኔም ሽሮ እና ጎመን ሠርቼ በመላክ፣ እሷም የባናና ወረቀት በመላክ ደኅንነታችንን የሚገልፅ መልዕክት እንለዋወጥ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ሰዓት እኛ በሌለንበት ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ይታይ ነበር፡፡›› በማለት ጉዳያቸው በኢ ፍትሐዊ መንገድ በመንግሥት እንደተያዘ አጫውታናለች፡፡