የእንክርዳድ ውርስ
ክፍል ፩
/The Inheritance of Chaffs/
/Part-I/
በዳዊት ፋንታ
በረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ“ የተሰኘ መፅሐፉን በሸራተን አዲስ ሲያስመርቅ ´´አሮጌዋ ኢትዮጵያ እየፈራረሰች በአዲሷ ኢትዮጵያ እየተተካች…………´´ እያለ ተናግሮ ነበር።በእርግጥ በሌላ በኩል ´´ሀገር ማለት ብሄር ብሄረሰቦች እንጂ ወንዝና ተራራው አይደለም፥የግዛት አንድነት ጉዳይ የነፍጠኝነት ጉዳይ ነው´´ እያሉ የወያኔ ርዕሳን ሲናገሩ መስማቱንም ለምደነዋል።
እስኪ በቅርቡ በተዘጋው የወያኔ የ21 ዓመት የመጀመሪያ ምዕራፍ ´´ገነባናት´´ ያሏትን ኢትዮጵያ እና ለትውልድ ያስተላለፉትን ውርስ እንመልከት።
ሀ. ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውርሶች
- 1. መሀይምነት /Illiteracy/
በኢትዮጵያ የወታደራዊው አስተዳደር ሲወድቅ ከመሀይምነት የተላቀቀው የህብረተሰብ ክፍል 60% ሲሆን ይህም ከነበረው ሃምሳ ሁለት ሚሊየን አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 31.2 ሚሊየን ይደርስ ነበር።ከ21 ዓመት የወያኔ አገዛዝ በኋላ ከመሃይምነት የተላቀቀው የህብረተሰብ ክፍል የቁልቁለት ጉዞውን ቀጥሎ 30% ብቻ ሲሆን ይህም ከ80ሚሊየን አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ መፃፍና ማንበብ የሚችለው 24 ሚሊየን ሲሆን ከዛሬ 21ዓመት በፊት ከነበረው በ7.2 ሚሊየን ያንሳል።በተጨማሪም 35.2 ሚሊየን አዳዲስ መሃይሞች ሲፈጠሩ በሀገሪቱም ያለው አጠቃላይ የመሃይም ቁጥር 56 ሚሊየን ደርሷል።
መሀይምነት በራሱ የጨለማ ኑሮ ከመሆኑ ባሻገር መሀይም ማህበረሰብ ለኢኮኖሚው ከሚያደርገው አስተዋፆ ይልቅ በሀገር ዕድገት ላይ ሸክም እና ጎታች መሆኑ በተለይ አሁን ካለው የአለማቀፍ ሁኔታ አንፃር የመሀይምነት ጠባሳ በሀገራችን ላይ የሚያስከትለውን ጫና በዚህ አጭር ፅሁፍ መዘርዘር የማይታሰብ ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱ ግን በሻዕቢያ ተፀንሶ በወያኔ እየተተገበረ ያለው ‘‘የመቶ አመት የቤት ስራ‘‘ ውጤት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ለመሆኑ ከ20 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችንና በርካታ ትምህርትቤቶችን የገነባው የወያኔ መንግስት ‘‘ቆመንልሃል“ የሚለውን ህዝብ እንዴት ከመሃይምነት የቁልቁለት ጉዞ ሊታደገው አልቻለም?
1.1 የተገነቡት ተቋማት አላማ ፖለቲካዊ አጀንዳ መያዛቸው፦ እንደሚታወቀው የወያኔ መንግስት በየክልሉ ብሎም በዞን ከተሞች ‘‘ዩኒቨርሲቲ“ እያለ በርካታ ተቋማትን የከፈተ ሲሆን በተጨማሪም በየወረዳውና በየቀበሌው ‘‘ትምህርት ቤት“ መክፈቱ ይታወሳል።ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ከላይ ሲታይ /From surface value/ በጎ የልማት ጅማሬ ቢመስልም ወደውስጥ ዘልቀን ስናየው ግን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚያስችል ሁኔታ ፖለቲካዊ አጀንዳ የያዘና በአካባቢው ላይ የወያኔን ተቀባይነት ለማስገኘት የሚደረግ ሩጫ ነው።ለምሳሌ ወያኔ በምርጫ -97 በጉራጌ ዞን መሸነፉን ተከትሎ ‘‘ጉራጌው ከነፍጠኛው ጋር ወግኗል“ በሚል በዞኑ ከፍተኛ ቅስቀሳ የተደረገ ሲሆን እንደ አርቲስት መሐሙድ አህመድ አይነት ስመጥር የአካባቢው ተወላጆች በተገኙበት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ለጉራጌ ህዝብ መብት ´´መከበር´´ ያደረገው አስተዋጽኦ በሰፊው ከተነገረ በኋላ መለስ ዜናዊ በወልቂጤ ከተማ በመገኘት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን የመሰረት ድንጋይ አኑሯል።ይህም በዋናነት የጉራጌ ህዝብ በወያኔ ላይ ያለውን ቅሬታ ለማለዘብ ተብሎ የተደረገ የፖለቲካ ስራ ነበር።የእነዚህና መሰል ተቋማት የመጀመሪያ አላማ ፖለቲካዊ ተቀባይነትን ለማግኘት ብቻ የተመሰረቱ በመሆኑ የወያኔ መንግስት ህዝቡን በጅምላ ለትምህርት ማንቀሳቀስ /Mass Mobilization/ ተስኖታል።
በቂ የትምህርት ተቋማት ባልተሟላበት የወታደራዊው መንግስት ዘመን ሰዎች ዛፍ ስር ሳይቀር እንዲማሩ ህዝብን ማንቀሳቀስ በመቻሉ ቢያንስ 60% የሀገሪቱ ህዝብ ከመሀይምነት መላቀቅ ሲችል በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ግን የተሻለ ቁጥር ያላቸው ትምህርትቤቶችና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተገነቡበት ሁኔታ የመሀይምነት አኃዙ ወደላይ ማሻቀቡ በእርግጥ ከወንዝና ተራራ በላይ ህዝቦችን የመውደድ ኢህአዴጋዊ ፍቅር ውጤት ይሆን?´´በኖራ የተለሰነ መቃብር ´´ እንዲል መጽሐፍ።ወትሮስ መቃብር የቱን ያህል ቢያስውቡት አጽም እንጂ ህያው አይኖርበት።
1.2 ትምህርትን ለማስፋፋት በሚል ሽፋን ቀጣይነት ያለው እርዳታ ለማግኘት፦በኢትዮጵያ ታሪክ እንደወያኔ መንግስት ከለጋሽ ሀገራት የውጭ እርዳታ ያገኘ መንግስት የለም።ይህም ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ወያኔ በኢትዮጵያ ትምህርትን አስፋፋለው የሚለው ፕሮፖጋንዳ ሲሆን ለጋሽ ሀገራትንም ለማማለል በየአካባቢው የሚገነቡ ተማሪ አልባ ትምህርት ቤቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።ለጋሽ ሀገራትም ስለተገነቡት ትምህርት ቤቶች እንጂ በውስጡ ስለሚማሩት ተማሪዎች አሀዝ ትኩረት ስለማይሰጡ በትምህርት ማዳረስ ሽፋን ስም ወያኔ ለሚያካሂደው ንግድ አመቺ ሁኔታን ሲፈጥር በኢትዮጵያ ውስጥም መሀይምነት እጅግ እንዲስፋፋ አድርጓል።
- 2. የከፋድህነትእናኢ-ፍትሀዊየሀብትክፍፍል /Abject Poverty and Unfair Wealth Distribution/
ወጣቱ ደራሲና ጋዜጠኛ መሐመድ ሰልማን ´´ፒያሳ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ´´ በተሰኘው መጽሐፉ ሁለት ኢትዮጵያዎች እንዳሉ ይነግረናል።የኢቲቪዋ ኢትዮጵያና በገሃዱ አለም የምናውቃት ኢትዮጵያ።
ሚሊየነር ገበሬዎች እንደአሸን የፈሉባት፣የኢኮኖሚ ዕድገቷ የምዕራቡን አለም እጅግ በማሳሰቡ ኒዎ ሊበራሎች ዕድገታችሁን ካላቆማችሁ እያሉ ባለስልጣኖቿን የሚወተውቱባት፣አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የውጭ ሀገር ዲፕሎማት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሷ ብዙ ሊማሩ እንደሚገባቸው የመሰከሩላትን የኢቲቪዋን ኢትዮጵያ ለወያኔና ሆድ አደር ጋዜጠኞቹ እንተወውና በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የድህነት መጠንና አይነተኛ መገለጫዎቹ እንዲሁም ስላለው ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንመልከት።
2.1 እጅግ የከፋ ድህነት /Abject Poverty/:- በኢትዮጵያ ያለውን የድህነት መጠን በቁጥር ከመግለፅ ይልቅ ዋና ዋና መገለጫዎቹን ማየቱ የበለጠ ግንዛቤ ይፈጥርልናል።ይህም ማለት ትርፍራፊ ምግቦች እንደ ምግብ መሸጣቸውን እና አብዛኛው ህዝብ ከቻለ በቀን ሁለቴ አልያም በቀን አንድ ጊዜ መብላቱን እንደዋና የድህነት መገለጫ ሳናነሳ ማለት ነው።
2.1.ሀ. የጅምላ ስደት/Mass Migration/ ፦ በኢትዮጵያ ቅድመ ወያኔ ታሪክ የኢትዮጵያ ወጣት በብዛት የተሰደደበት ወቅት ቢኖር የቀይ ሽብር ዘመን ሲሆን ይህም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ አፈና እንጂ እጅግ ስር በሰደደ ድህነት ምክንያት አልነበረም።ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት በጅምላ እየተሰደደ ሲሆን በሀገር ቤት ያለውም ቀዳሚ ምርጫው ስደት እንደሆነ በቅርብ የወጣውን የአለማቀፉ የቀውስ አጥኚ ቡድንን /International Crisis Group/ ጥናት ማየት ብቻ በቂ ነው።
አብዛኛው ስደተኛም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስደተኛ ሲሆን ከዕድሜ አንፃር በሁሉም የዕድሜ ክልል፣ከፆታ አንፃር ሁለቱም ፆታዎች፣ከትምህርት ደረጃ አንፃር የተማሩትም ያልተማሩትም የተካተቱ ሲሆን ህይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እያወቁ እንኳን ስደትን መምረጣቸው ዜጎቻችን በሀገራቸው መሰረታዊውን ነገር እንኳን ማግኘት እንዳልቻሉ ከማሳየቱም ባሻገር የድህነቱም መጠን ምን ያህል ስር እንደሰደደ ያሳየናል።
ሀገራችን ተማሪዎቿን እስከ ከፍተኛ ተቋማት ለማድረስ ዋጋ ያልከፈለችበት ያህል ዛሬ በህሊና ብስለት፣በዕውቀትና በዕድሜ አፍላ የሆኑ ወጣቶቻችንን በየስደተኛ ጣቢያው ተጥለው ስናይ ድህነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የግዛት አድማሱን እያሰፋ ከገዢዎቻችን እና በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች ውጪ ያለውን ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል እጅ ተወርች ጠርንፎ እንደያዘው ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።
2.1.ለ. ከድህነት ጋር ግንኙነት ያላቸው በሽታዎች ሥርጭት /Poverty Related Diseases/ ፦ ከድህነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ካላቸው በሽታዎች በዋናነት ኤች አይ ቪ ኤድስ፣የሳምባ ነቀርሳ፣ወባ፣የልጅነት ልምሻ የመሳሰሉት ሲሆኑ ያለምንም ማጋነን ከላይ በተዘረዘሩት የበሽታ አይነቶች የተጠቁ እና እየተጠቁ ያሉ በርካታ ዜጎች ከሚገኙባቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በተለይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እዚህ ደረጃ የደረሰው በወያኔ ዘመን ነው።ለዚህም እንደማስረጃ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ደርግ ወድቆ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ በየሆቴሎች እንግዳ መቀበያ ላይ /Reception/ ኮንዶም ይቀመጥ የነበረ ሲሆን ወያኔ አዲስ አበባ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ይህ ልምድ የተቋረጠ ሲሆን ቢያንስ ከ1983-1988 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በወያኔ መንግስት በኩል ግንዛቤን በህብረተሰቡ ውስጥ ለመፍጠር የተሰራ ነገር ባለመኖሩ በርካታ ህዝብ በዚህ በሽታ ሊጠቃ ችሏል።በሌላ በኩል ኤች አይ ቪ ኤድስም ሆኑ ሌሎች በሽታዎች ለወያኔ የውጭ እርዳታ መለመኛ መንገድ መሆናቸውን ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ ነው።
2.1.ሐ. የጎዳና ተዳዳሪነት /Street Life and Loitering/፦መጠኑ ይለያይ እንጂ የጎዳና ተዳዳሪነት በአብዛኛው አለም የተለመደ ሲሆን ለምሳሌ በጀርመን፣በኢንግላንድና በስካንዲኔቪያን ሀገሮች ሁሉም ዜጋ የመኖሪያ ቤት የሚሰጠው ሲሆን በነዚህ ሀገራት የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይህን ህይወት በፈቃዳቸው ፈልገው የሚያደርጉት ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመለስ ግን በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ድህነት ገፍቶ ወደ ጎዳና የጣላቸው ሰዎች ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ምሁራን፣ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ምሩቃን፣በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በተለያየ ሙያ ያገለግሉ የነበሩ ዜጎች ሲገኙበት ለዚህም እንደመንስኤ የሚነሳው ዜጎቻችን የወያኔ አባል ካልሆኑ አልያም ፖለቲካዊ አቋማቸው ወያኔን የሚጋፋ ከሆነ በሰፊው የድህነት ባህር ውስጥ እንዲደፈቁና ለጎዳና ህይወት እንዲዳረጉ ይገደዳሉ።
ከዚህም ባሻገር በገጠር አካባቢ መሬት የፖለቲካ መሳሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ ገበሬው በማዳበሪያ ዕዳ ኑሮው ስለሚናጋ በርካታ ህዝብ ወደከተማ እንዲፈልስ በዚያም በጎዳና ላይ ኑሮውን እንዲገፋ ይደረጋል።
2.2 ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል /Unfair Wealth Distribution/:-ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዕዝ ኢኮኖሚ ተላቃ ገበያ መር ኢኮኖሚ እየተከተለች ነው ከተባለ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ቢሆንም በማህበረሰቡ ውስጥ እየታየ ያለው የሃብት ክፍፍል ግን ፍጹም ገበያ መር ኢኮኖሚ ከሚያስከትለው ተጽዕኖ ተመጣጣኝ ካለመሆኑ ባሻገር በሃገሪቱ ውስጥም እየታየ ነው የሚባለው “ዕድገት“ የጥቂት ቡድኖች ዕድገት ሆኖ እናገኘዋለን።
በመሆኑም በሃገሪቱ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ለመጣው ድህነትና ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዐይነተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙትን ጉዳዮች እንመልከት።
2.2.ሀ. የፖለቲካ ተቋማት አወቃቀር /The Nature of Political Institutions/፦በግልፅ እንደሚታየው የወያኔ መንግስት የሃገሪቷን የፖለቲካ ተቋማት ያዋቀረበት መንገድ ሁሉን አሳታፊ /All-inclusive/ ያልሆነ ይልቁንም ጥቂት የአንድ አካባቢ ተወላጅ ኅሩያን /Elites/ በዋናነት የሚያሽከረክሩት መዝባሪ ተፈጥሮ /Extractive Nature/ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።ይህ አይነቱ የፖለቲካ ተቋማት አደረጃጀት በባህሪው እውነተኛ መድብለ ፓርቲ /Bona fide Pluralism/ እንዳይፈጠር በግልጽም ይሁን በህቡዕ /Overtly or Covertly/ ስለሚከላከል ተጠያቂነት የሌለበት ገደብ አልባ ሥልጣን /Unconstrained Power/ በጥቂት ኅሩያን እጅ በህግ ላልተገደበ ጊዜ እንዲቆይ ያደርገዋል።ይህም መዝባሪ የፖለቲካ ተቋም ለሀገር እና ለህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ከመስራት ይልቅ የጥቂት ቡድኖችን ሥልጣን ለማጠናከሪያነት የሚረዱ አቻ መዝባሪ የኢኮኖሚ ተቋማትን /Extractive Economic Institutions/ በመገንባት ላይ ይወሰናል።ከዚህም ባሻገር የስርዐቱ ዋነኛ አጀንዳ የፖለቲካ ሥልጣኑን ማስጠበቅ በመሆኑ የሀገሪቱን አብዛኛ መዋዕለ ነዋይ ህዝብን ለማፈን የተጋነነ የፖሊስ ኃይልን እና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት፣በካድሬ ምልመላ እና ስልጠና እንዲሁም በድርጅታዊ ተግባራት ላይ ስለሚያውለው በስርዐቱ ዙሪያ ካሉ ጥቂቶች ውጪ ያለው ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ለገዥዎቹ የሀብት ምንጭ ከመሆን በዘለለ የሃገሪቱ የሀብት ተካፋይ ሊሆን አይችልም።በተጨማሪም በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ስርዐት ውስጥ በሙስና ላይ የሚኖረው ተጠያቂነት ለዘብተኛ በመሆኑ ከግለሰብ ጀምሮ እስከተደራጀ የሙስና ወንጀል መመልከት የተለመደ ተግባር ይሆናል።ለዚህም ነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ እና የጦር ሹመኞች የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ እና በማሸሽ ተግባር የተጠመዱት።
2.2.ለ. የኢኮኖሚ ተቋማት አወቃቀር /The Nature of Economic Institutions/፦በኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚ ተቋማት አወቃቀር በዋናነት በሥልጣን ላይ ላለው ቡድን ተጨማሪ ኃይልን በሚፈጥር መልኩ መዝባሪ ባህርይ /Extractive Nature/ ያለው ሲሆን የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብትም ከሞላ ጎደል በዚህ ቡድንና በሥልጣኑ ዙሪያ ባሉ የጥቅም ተሳሳሪዎች /Cronies/ እጅ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም ከፍተኛ ብዥታ እየፈጠረ ያለው የእዚህ አናሳ ቡድንና በሥልጣኑ ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞችን የሀብት ዕድገት የመላው ህብረተሰብ እና የሀገሪቱ ዕድገት አስመስሎ የማቅረቡ ጉዳይ ነው።
በመሰረቱ መዝባሪ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማት እርስ በእርሳቸው ተመጋጋቢ ሲሆኑ እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ተቋም ሥልጣንን ያለገደብ በጥቂቶች እጅ በማድረግ አቻ የሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማትን ለመፍጠር፣የኢኮኖሚ ተቋማቱን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎችንና አዋጆችን ለማፅደቅ፣በገበያው ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር፣ነጻ ፉክክር እንዳይኖር እንቅፋቶችን ለመፍጠር /To erect entry barriers/ ሲረዳ በምላሹ እነዚህ መዝባሪ የኢኮኖሚ ተቋማት የሀገሪቱን ሀብት ከአብዛኛው ህዝብ በመዝረፍ በሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን በሀብት እና ኃይል ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጉታል።
ለዚህም አይነተኛ ማሳያ የሚሆነን የህወሃት ቡድን የፖለቲካ ሥልጣኑን ያለገደብ ሲቆጣጠር “ኤፈርት“ የሚባል መዝባሪ ግዙፍ የንግድ ኢምፓየር የገነባ ሲሆን ከኤፈርት የተረፈውን ክፍተት የፖለቲካ እና የጦር ባለስልጣናት እንዲሁም በሥርዓቱ ዙሪያ የሰፈሩት ጥቅመኞች በግላቸው እና በዘመዶቻቸው ስም ባስመዘገቧቸው የንግድ ተቋማት ስልጣንን ተገን ያደረገ ካፒታሊዝም /Crony Capitalism/ መመስረት ችለዋል።በመሆኑም የወያኔ መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸው ባለሁለት አሃዝ “ዕድገት“ በእርግጥም የኢትዮጵያ ዕድገት ሳይሆን የእነዚህ ጥቂት ቡድኖች ግዙፍ የንግድ ተቋማት እድገት ሆኖ እናገኘዋለን።
- 3. ሙስና /Corruption/
´´ምርኮ ፈጠነ፥ብዝበዛ ቸኮለ´´
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያን ሪቪው /ethiopianreview.com/ ድረ-ገጽ ላይ ´´አስራአንደኛው ትዕዛዝ´´ /The Eleventh Commandment/ የተሰኘ ጽሑፍ ጽፌ ነበር።በእርግጥ አስራአንደኛው ትዕዛዝ ማለት ´´በፖለቲካችን እስካልመጣህ፥የምንልህንም እስካደረግህ ድረስ ብትሰርቅም፣ብትዘርፍም ምንም አይደል´´ የምትለዋ የወያኔ ያልተፃፈች ህግ ናት።
ለዚህም ነው አንድ የወያኔ ባለስልጣን ለገጣፎ አካባቢ በስሙና በቤተሰቦቹ ስም 60 /ስልሣ/ የመሬት ይዞታዎችን የያዘ፣ለዚህም ነው በሲፒኤ ስኬል መሠረት ደሞዛቸው ከ5000.00 /አምስት ሺህ/ ብር የማይበልጥ ጄነራሎች ከ10,000.00 /አስር ሺህ/ ዶላር በላይ የሚከራዩ ቤቶችን የገነቡት፣ለዚህ ነው የሚንስትሮቻችን ሚስቶች ከቻይና አዲስ አበባ እንዲሁም ከዱባይ አዲስ አበባ የሚመላለሱ ሲራራ ነጋዴ የሆኑት፣ለዚህም ነው የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን በአንድ ቀን የአልባሳትና ጌጣጌጥ ግብይት 1.2 ሚሊየን ዩሮ ወይም በአማካይ 26.4 ሚሊየን ብር ማውጣታቸውን ከስፔን ጋዜጦች ያነበብነው።
እንዲሁ ለማሳያ ያህል ጠቀስኩት እንጂ ከግልገል ካድሬዎች ጀምሮ እስከሚንስትሮቻችን እና የጦር ሹመኞች ድረስ የመግባቢያ ቋንቋቸው ሁሉ ´´በዋሌትህ አስብ፥በእጅህ ተናገር´´ ከሆነ ዘመናት አልፈዋል።ዛሬ ከጥንት ጀምሮ በሙስና ከሚታወቁት ናይጄሪያን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀን በሙሰኛ ሀገራት የደረጃ ሠንጠረዥ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ እንገኛለን።
በሌላ በኩል በ1993 ዓ.ም. የተቋቋመው ´´ፀረ-ሙስና ኮሚሽን´´ በመባል የሚታወቀው መስሪያ ቤት ልክ እንደ ፍርድ ቤቶች ሁሉ የህዝብ አመኔታ የሌለው ተቋም ሲሆን ቀዳሚ አላማውም አስራአንደኛውን ትዕዛዝ የሚተላለፉ የወያኔ ባለስልጣናትን ለመቅጣት እንጂ በርግጥም እንደስያሜው ሙስናን ለመዋጋት የቆመ አይደለም።
» » » »(ክፍል ፪ ይቀጥላል)« « «
No comments:
Post a Comment