Sunday, November 11, 2012

‹‹ናፍቆት እኔ ብሞትም አንተ ንብረቴን ታስመልሳለህ›› እስክንድር ነጋ


(በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ) ከነገ በስቲያ (ማክሰኞ ህዳር አራት) በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የእስክንድር ነጋን ንብረት ለመውረስ ይሰየማል፡፡
በትላንትናው ዕለት የክስ ቻርጅና መንግስት እወርሳቸዋለሁ ያላቸውን የእስክንድር ሁለት ቤቶች ካርታ የተያያዙበት መጥሪያ ደርሶታል፡፡ (በነገራችን ላይ መንግስት ሊወስዳቸው ከተዘጋጁት ቤቶች አንዱ በእናቱ ስም ያለ ሲሆን የዛሬ ዓመት አካባቢ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የቤቱን ስም ለማዞር ፈልጋ ‹‹ካርታው የለም›› በሚል አንዴ ቀበሌ፣ ሌላ ጊዜ ክፍለ ከተማ፣ ቀጥሎ አዲስ አበባ መስተዳደር ስትመላለስ ከርማ ሊገኝ ስላልቻለ ሰልችቷት ትታው ነበር፡፡ ትላንት ግን ዓቃቢ ህግ ከክስ ቻርጁ ጋር አያይዞ አቅርቦታል፤ እናም ምንአልባት ያን ግዜ ‹‹ካርታው የለም›› የተባለው ሆነ ተብሎ ተደብቆ ሊሆን ይችላል)

I am Eskinder Nega
 Eskinder Nega
የሆነ ሆኖ እስክንድር ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤቴን አትውረሱብኝ›› ብሎ ስለማይከራከር ‹‹በዕለቱ ፍርድ ቤት መሄድ አልፈልግም›› ሲል ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ ግን ‹‹የግድ ማቅረብ ስላለብን ይዘንህ እንሄዳለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እናም እስክንድር በዕለቱ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምንም አይነት ምላሽ ላለመስጠት ወስኗል፡፡ ባለቤቱም ‹‹የሚስትነቴን ድርሻ አትውረሱብኝ›› ብላ አትከራከርም፡፡ ፍርድ ቤቱ የፈለገውን ይወስን የሚል አቋም ነው ያላት፡፡
በዛሬው ዕለት ሊጠይቀው ቃሊቲ የመጣውን የሰባት ዓመቱን ህፃን ልጁን ጠባቂ ፖሊሶች እየሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹ናፍቆት እኔ ብሞትም አንተ ንብረቴን ታስመልሳለህ፡፡ አይዞህ! ስርዓት ተቀያየሪ ነው፤ ንጉሱ የወረሱት በደርግ ተመልሷል፤ ደርግ የወረሰው በኢህአዴግ ጊዜ ተመልሷል፤ ኢህአዴግ የወረሰው ደግሞ ኢህአዴግ ሲወድቅ መመለሱ አይቀሬ ነው›› ብሎታል፡፡ በ1993 ዓ.ም ግምቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የእስክንድር እናት ቤት በግፍ እንደተወረሰ ይታወቃል፡፡
ዜናውን ያደረሱልን ጋዜጠኛ ተመስገን በመጨረሻ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “እስቲ አሁን እንኳን ምንአለበት ትንሽ እንደ ሰው አስባችሁ ልጁን የሚያሳድግበትን ንብረት ብትተውለት? …ዛሬም በትላንቱ መንገድ፣ ዛሬም በመለስ ጫማ፣ ዛሬም በመለስ ራዕይ… አቤት! እንዴት ልብ የሚያደማ ነገር ነው! ይህ ምን አይነት ጭካኔ ነው?” ብለዋል

No comments:

Post a Comment