Sunday, November 11, 2012

34 ፓርቲዎች በ2ዐዐ5 ዓም በሚካሄደው ምርጫ ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ


                                                                                                                ጥቅምት 29 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- ጥቅምት 15 ቀን 2ዐዐ5 ዓም በአዳማ ከተማ ቦርዱ ‹‹በ2ዐዐ5 ዓም በሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ አፈፃፀም
የጊዜ ሰሌዳ ረቂቅ›› ላይ ከፖለቲካ ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባአደረገው ምክክር ፕሮግራም ተገኝተው
ፔቲሽን ከፈረሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበ ጥያቄ ስለማቅረብ፣


1. አጠቃላይ፡-

ከላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ቦታና ርዕሰ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራር (ቦርድ)  እና ሥራ
አስፈፃሚ (ጽ/ቤት ኃላፊና ሠራተኞች) በተገኛችሁበት 66 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተን ውይይት
ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በዚህ የምክክር ፕሮግራም ላይ ከተሣተፉ የፖለቲካ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ‹‹የአገሪቱ
የፖለቲካ ምህዳር እየጠበበ መምጣቱንና የምርጫ ውድድር ሜዳው የተስተካከለ ያለመሆኑን፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ
ምርጫዎች በአፈፃፀም ችግሮች የተተበተቡ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በየደረጃው ባሉት የምርጫ ቦርድ አመራርና
አስፈፃሚ አካላት ተአማኒነትና ተቀባይነት ላይ ያለውን ጥያቄ ተጨባጭ መገለጫዎችንና መሣያዎችን በማቅረብ  
ካስረዱ በኋላ በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ከጊዜ ሠሌዳው ረቂቅ ላይ ከመወያየት ቅድሚያ ሊሰጠው
ይገባል›› የሚል ሃሳብ ማቅረባችን በእለቱ በተቀረፀው ኦዲዮ-ቪዲዮ ላይ ይገኛል፡፡

በወቅቱ ላነሳናቸው ጉዳዮች በቂ መልስ ባለማግኘታችን በፕሮግራሙ ላይ የተሣተፍን 33 የፖለቲካ ድርጅቶች ከጊዜ
ሠሌዳው በፊት የምርጫው ፍትሐዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ነፃ መሆን ላይ የሚደረግ ውይይት እንዲደረግ ፔቲሽን
ለመፈራረም ተገደናል፡፡ የፔቲሽኑ ይዘት (1 ገጽ) እና የፈረሙ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ዝርዝር (2 ገጽ)
ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም ፔቲሽንኑን የፈረምነው ፓርቲዎች ተጠሪዎች በ25/ዐ2/2ዐዐ5  ዓም
ተገናኝተን በጉዳዩ ላይ በጥልቀትና በስፋት ተወይይተናል፡፡ ጥያቄአችን በዚህ መልክ እንዲቀርብ ተስማምተናል፡፡
እነዚህ  ከላይ በጥቅል ከታች ደግሞ በዝርዝር የቀረቡ ከምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት ጋር በቀጥታ
የተያያዙ ጉዳዮች እንኳን በ33  የፖለቲካ ድርጅቶች ቀርቶ በአንድ ድርጅትም በተጨባጭ መረጃዎች ተደግፈው
ከቀረቡ የቦርዱ ትኩረት ሊነፈጋቸው እንደማይገባ እናምናለን፡፡

 ለምርጫው ተአማኒነትና ተቀባይነት ያላቸውን ፋይዳም ጠንቅቀን እንረዳለን፡፡በመሆኑም የዜጎች
ህገ-መንግሥታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ሆነው ሁላችንም በነፃ፣ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና
አሣታፊ ምርጫ ተሳትፈን ለአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ሠላምና ልማት
የየድርሻችንን እንድናበረክት ይቻል ዘንድ በቀደሙ ምርጫዎች ያጋጠሙ ችግሮች እና ጥያቄዎቻችን  እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

2
በዚህ አጋጣሚ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤትን የምናሳስበው እነዚህ ጥያቄዎቻችን  በአዳማው የምክክር ፕሮግራም
ላይ ብቻ የተመሠረቱ ያለመሆኑንና ከዚህ በፊትም ተመሣሣይ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ለቦርዱ ያሰማን መሆኑን
መግለፃችንን ነው፡፡ ለዚህም የምርጫ አፈፃፀምና አስተዳደር በጊዜ ውስጥ   በልምድና ተሞክሮ እየተሻሻለ መሄድ
ቢጠበቅም በተቃራኒው አዘቅት ወርዶ ‹‹ 2ዐዐ2 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ በዘመነ ኢህአዴግ ከተካሄዱ ምርጫዎች
ሁሉ የከፋና የገዢ ፓርቲን አምባገነንነት ያረጋገጠ ሆኖ አልፏል፡፡››  በማለት በምርጫ የተሣተፉ 5ዐ የፖለቲካ
ፓርቲዎች መጋቢት 24/2ዐዐ3   ዓም በግዮን ሆቴል ‹‹የ2ዐዐ2  ዓም የድህረ ምርጫ ግምገማ
(EVALUATION)  ረቂቅ››  ላይ በአንድ ድምጽ የደረሱበትን ድምዳሜ (ገጽ 4.ተ.ቁ. 1.3.2.2)
የሚያሳየውን የ4ቱ ቡድኖች ሪፖርቶች ጥንቅር (14 ገጽ) በአባሪነት አያይዘናል፡፡ በዚህ የሪፖርቶች ጥንቅር የተነሱ
የምርጫውን ሂደት የሚመለከቱ ጉዳዮችና ፓርቲዎቹን ከዚህ የጋራ ድምዳሜ ያደረሱ ችግሮች በቦርዱ ምንም ቦታ
ያልተሰጣቸውና በባሰ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ስለሆነ ቦርዱ እንደገና እንዲመለከታቸው እንጠይቃለን፡፡

2. ዝርዝር ጉዳዮች
ዝርዝር ጉዳዮች ስንል የምናነሳቸው ነጥቦች   በምርጫ ሂደት የታዩ ችግሮች ማሣያ/መገለጫ መሆናቸውን እንጂ
ከአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት   ግንባታ፣ ከህገ-መንግሥቱ መከበር፣ ከሠላማችንና ልማታችን ጋር ያላቸውን
የምክንያትና ውጤት ግንኙነት የተለየዩ አገሮች ልምድ ለቀሰመው ቦርድ በዝርዝር ለማስረዳት አይደለም፡፡ እነዚህ
ጉዳዮች  አዲስ ያለመሆናቸውን ስለምንረዳ እንዲሁም እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ከላይ በአባሪነት በጠቀስነው የሪፖርቶች
ጥንቅር ሰነድና በተለያዩ ፓርቲዎች በተጨባጭ መረጃ ተደግፈው ለቦርዱ በቀረቡ የቅሬታ አቤቱታዎች ውስጥ ተካተው
በቦርዱ ጽ/ቤት  እንደሚገኙ ስለምናውቅ ወደ ጥልቅ ዝርዝር አንገባም፡፡

2.1  የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ አባል እና /ወይም ደጋፊ በመሆናቸው በየደረጃው በምርጫው  ሂደት ላይ
ወገንተኛ መሆናቸው፤

  2.2   የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች የወከሏቸው ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያ መባረራቸው፤ በምርጫ  እለት መታሠራቸው፣ 
ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ መከልከላቸው፤

2.3    የሕዝብ ታዛቢዎች በመንግሥትና ገዢው ፓርቲ መመረጣቸውና ለተለያዩ ተጽእኖዎች  የተጋለጡ  
መሆናቸው፤

   2.4   የመንግሥት አስተዳደር፣ ፍትሕ ፣ፖሊስ፣ እና አካባቢ ታጣቂዎች  በምርጫው በቀጥታ ወገንተኛነት
መሰለፋቸው፤

   2.5  የመንግሥት ሀብት (ሠራተኞች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ገንዘብ፣ . . . ወዘተ) ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ማስፈፀሚያ
መዋላቸው፤

   2.6  ፍትሀዊ የፌዴራልና የአካባቢ/ክልል የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ያለመኖሩና የግል ፕሬሶችና የፓርቲ
ልሣኖች እንዲዘጉ ወይም እንዳይታተሙ መደረጋቸው፤
         (ችግሩ ዛሬም ቀጥሎ በፍትሕ ጋዜጣና ፍኖተ-ነፃነት ላይ ተፈፃሚ ሆኗል፡፡)

2.7   ለምርጫ ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ፍትሐዊ ያለመሆንና በተገቢ ጊዜ ያለመከፋፈል፣  የገዢው ፓርቲ
ጠቅልሎ በመውሰድ ከህግ አግባብ ውጭ አከፋፋይ መሆኑ፤3

2.8   የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሱ በደሎች፣ እሥራት፣ ማፈናቀል፣ ስደት፣ የእርዳታ
እህል መከልከል፣ የእርሻ ምርት ግብአቶች (ማዳበሪያና ምርጥ ዘር)  በወቅቱ እንዳያገኙ ማድረግ፡፡

2.9   የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች አባልና ደጋፊ ናቸው የሚባሉ መራጮች እንዳይመዘገቡ ማድረግ፣
ማስፈራራት፣ እንዳይመረጡ ማድረግ፣

2.10 ነፃና ገለልተኛ አገራዊና ዓለማቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች እንዳይሣተፉ፤ በነፃነት ተግባራቸውን እንዳያከናወኑ፣
ሽፋናቸው ውስን እንዲሆን ማድረግ፣

2.11 ገዢው ፓርቲ የመንግሥት  ቤቶችና  ቢሮዎችን በነፃ በሚጠቀምበት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢሮዎችን
በኪራይ እንኳ እንዳያገኙ የሚደረግበት፣ ቢሮዎች በአስተዳደር የሚዘጉበት፣ በዶዘር የሚፈርሱበት፣

2.12 ተቃዋሚ  የፖለቲካ ድርጅቶች ከመራጩ ሕዝብ ጋር የሚገናኙበት መድረክ የተዘጋበት፣ የግል የስብሰባ
አዳራሾችን እንኳ እንዳይጠቀሙ የተደረገበት፤

2.13 በምርጫ አፈፃፀም ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በደንቡና በስምምነት መሠረት የማይስተናገዱበት፣

2.14 የፓርቲ መሪዎችና የነፃ ፕሬስ አባላት በፈጠራ ወንጀል የሚታሠሩበትና ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በታፈነበት፣
መራጩ ሕዝብም  በተሸማቀቀበት፣ (ዛሬም በእሥር ላይ የሚገኙትን ያጤኗል፡፡)

2.15 መራጩ ሕዝብ በነፃነት እንዳይመርጥ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች 1 ለ5 ተጠርንፏል፣ የድምጽ አሰጣጥ
ሚስጥራዊነት ተጥሷል፡፡ አማራጭ መረጃዎችን እንዳያገኝ ታፍኗል፤

2.16 ለመራጩ ሕዝብ የሥነ-ዜጋ፣ ስለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ቦርዱ በበቂ ካለማስተማሩም በዚህ መስክ
የተሰማሩ የሲቪል ማህበራት በአዋጅ ታግደው በገዢው ፓርቲ የሴቶችና ወጣቶች . . . ፎረሞችና ሊጎች
የተተኩበት፤

2.17 በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መንግሥትና ገዢው ፓርቲ አንድ ሆነው የሚቀርቡበት፣ ሕዝቡ የውጭ የዜና
አውታሮችን ጃም እስከማድረግ በደረሰ እርምጃ አማራጭ ሃሳቦችንና መረጃዎችን እንዳያገኝ የተደረገበት፣

2.18 ከለጋሽ አገሮች በእርዳታና ብርድ የሚገኘው ገንዘብና ማቴሪያል ለገዢ ፓርቲ የድምጽ መግዣ፣ በተቃራኒው
ለተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መቀጣጫ የሆነበት፣ . . . ወዘተ፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው እነዚህ ለአብነት የቀረቡ ማሣያዎችና መገለጫዎች እንጂ ችግሮችን ለመፍጠር ገዢው ፓርቲ
የተጠቀመባቸውን የአፈና ስልቶችና ሴራዎችም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅሮች እንዴት
በወገንተኛነት ድጋፍ እንደሰጡ በዝርዝር የሚያሳዩ አይደሉም፡፡
በተጨማሪም እንደመነሻችን የምርጫ ሠሌዳ ምክክር ርዕሰ ጉዳይ ሁሉ ከላይ የተገለፁትን ጉዳዮች በሚመለከተ
በሚወጡ የማስፈፀሚያ ደንቦችና መመሪያዎች ረቂቆች ላይ ቦርዱ ለውይይት የጋበዘን ቢሆንም በውይይቱ ላይ
ያነሳናቸው ጥያቄዎች ሳይመለሱ፣ ያቀረብናቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ከግምት ሣይገቡ ‹‹ ረቂቅ›› ተብለው የቀረቡት
ሁሉ ባሉበት ሁኔታ መጽደቀቸውን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፡፡ በተመሣሣይ ይህ እውነታ በዚህ ርዕሰ ጉዳይም ላይ
መደገሙን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የመንግሥት ሚዲያ ሰምተናል፣ አይተናል፡፡

3. ጥያቄአችን4
እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው ጉዳዮች መፍትሔ ሳይበጅላቸው በጊዜ ሠሌዳ ላይ መነጋገርም ሆነ በምርጫ መሣተፍ
ለአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለህገ መንግሥቱ መከበር፣ ለህግ የበላይነት መስፈን፣ ለሠላማችንና
ልማታችን ከሚያደርገው  አስተዋጽኦ ይልቅ ለተቃራኒው ውጤት የሚከፈል መዋጮ ስለሚሆንና ህዝባችንም ከቀደምት

ምርጫዎች በእጅጉ ለከፋ አደጋና እንግልት ፣ እሥራት፣ መፈናቀል፣ ድብደባ፣ ስደት፣ ሞት . . . ማጋፈጥ ነው፡፡
ይህ ደግሞ ለአገራችንና ለሕዝቦቿ ባለን ኃላፊነት የምንቀበለው አማራጭ ባለመሆኑ ወቅታዊና ተገቢ የሆነ የጋራ
እርምጃ እንወስዳለን፡፡

ስለዚህ ቦርዱ እንደ ተቋም አመራሩና አስፈፃሚው እንደ ዜጋ በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚጎለብትበትን፣ የሕግ

የበላይነት የሚሰፍንበትን፣ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድልኦ የሌለበትና ሁሉም በእኩል የሚስተናገዱበትና የሚሳተፉበት

የምርጫ ውድድር ሜዳ የሚፈጠርበትን፣ በህገ መንግሥቱ የተከበሩ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያው መብቶች ሳይሸራረፉ
ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታ የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነዚህ ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች እውን እንዲሆኑ
ሁላችንም የየድርሻችንን ሚና እንድንጫወት ከምርጫው የጊዜ ሠሌዳ በፊት ከላይ ለገለጽናቸው ችግሮች የጋራ
መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል የጋራ ምክከር እንዲደረግ ነው፡፡

በተባበረና የቀናጀ ሠላማዊ ሕዝባዊ ትግል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!
ግልባጭ

- ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

- ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

አዲስ አበባ

አባሪዎች፡-

1. የፔቲሽን ይዘት (1 ገጽ)

2. የፔቲሽን ፈራሚዎች ዝርዝር (2 ገጽ)

3. የምርጫ 2ዐዐ2 ድህረ ምርጫ ግምገማ ረቂቅ ሪፖርቶች ጥንቅር (14 ገጽ) ናቸው፡፡
የጥያቄ አቅራቢዎች ተወካዮች፡-

   ተቁ   ሥም ከነአባት     የሥራ ኃላፊነት
 
1.      አቶ አሥራት ጣሴ   ሰብሳቢ  
2.      አቶ ወንድማገኘሁ ደነቀ       ም/ሰብሳቢ  
3.      አቶ ግርማ በቀለ    ፀሐፊ    
4.      አቶ ስለሺ ፈይሳ        ም/ፀሐፊ  
5.      አቶ አለሳ መንገሻ   አባል  
6.      አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ        አባል    5
7.      አቶ ለገሠ ላንቃሞ            አባል

No comments:

Post a Comment