ኀዳር ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 31 መሰረት በህጋዊ መልኩ ተመዝግበው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቃስቃሴ የሚያደርጉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን በሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት በመፈረጅ የጥቃት ኢላማ ለማድረግ መታሰቡን ኢሳት የፌደራል መንግስት የጸጥታ ጉዳዮች ሰሞኑን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ካካሄደው ውይይት ለመረዳት ተችሎአል።
የትግራይ፣ቤንሻንጉል ጉሙዝና አማራ ክልል ሃላፊዎች ሰማያዊ ፣አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች ጽንፈኞች በመሆናቸው በአክራሪነት ሲሳተፉ የነበሩ ወጣቶችን በማሰባሰብ ለሽብር እያዘጋጁ ነው በማለት የገዢውን መንግስት ፖሊሲዎች በሰላማዊ መንገድ የሚቃዎሙትን ፓርቲዎችን በወንጀለኛነት ሲፈርጁ ተደምጠዋል።
መልካም ተሞክሮ ነው በማለት በየክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊዎች የቀረበው ሪፖርትና የወደፊት እንቅስቃሴ በመጭው ምርጫ 2007 የተፈረጁት ፓርቲዎች የህዝብ ድምጽ በማግኘት የገዢው መንግስት ስጋት እንዳይሆኑ ከማሰብ የተነሳ መሆኑን የውስጥ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።