
በፌዴራል ስም የተሸፈኑ ህውሃት/ኢህአዴጎች እና በአቶ መለስ ራዕይ የተጠመቁ የክልል ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ የዘር ማጥራት (Ethnic Cleansing) ወንጀል ስለመፈጸማቸው መዘገብ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ይኽ ዜና በኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል። ኢትዮጵያ እንድትበተን የሚፈልጉ ግን አፍና እጃቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከመንገዳቸው ላይ ተወግዳ ህልማቸው ወደሆኑት የቃል-ኪዳን አገሮቻቸው (Promised-land) ለመድረስ የጀመሩትን ጉዞ ፍጥነት እና ግልጽነት ሳያመቻቸው ዝቅ ሲያመቻቸው ደግሞ ከፍ ያደርጋሉ እንጂ አያቆሙም። የህውሃት ሕገ መንግስት (አንቀጽ 39) ግፉ በርቱ ይላል። ስለዚህ የቤንሻንጉል ጉምዝ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ናስር ቀደም ብሎ በቪኦኤ አማርኛ ፕሮግራም ሲጠየቅ አፉን ሞልቶ ሞቅ ባለ ስሜት አማርኛ ተናጋሪውን ያፈናቀልነው መሬቱን ለልማት ስለፈለግነው ነው እንዳላለ ሁሉ ድንገት ተነስቶ ሰሞኑን ይቅርታ መጠየቁ ማጭበርበሪያ ድራማ እንጂ ሃቅ አይደለም። ይኽ ይቅርታ ከራዕይ እና ከፖሊሲ ለውጥ የመነጨ ሳይሆን የተለመደው የህውሃት ማዘናጊያ እና አቅጣጫ ማስቀሪያ ፕሮፖጋንዳ ነው። ለአንድ ደቂቃ እንኳን መዘናጋት የለብንም። ላብራራ።