Friday, October 31, 2014

ፕሬስ በዘመነ ወያኔ

ፕሬስ(Press) ራሱን ለመግለጥ ከተፈቀደለትና ከተመቻቸለት መንግሥት አገርን በአግባቡ እንዲመራ የሚያግዝ ታላቅ የመርጃ መሣሪያ እንጂ ፀረ-መንግሥት አቋምም ሆነ ሚና የለውም። ፕሬስ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አስተዋጽዖ ከማድረጉም በላይ፤ የመንግሥትንም ሆነ የድርጅቶችን፤የግለሰቦችንና የአጠቃላይ ዜጎችን በጎ ጎን በማጉላት ለሕብረተሰቡ ይፋ በማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ከብዙ በጥቂቱ ነጻ ፕሬስ ሙስናንና ስግብግብነትን በመዋጋት ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ያጋልጣል፥የሕዝብን የበላይነት ያስረጋግጣል፥ እንዲሁ የሥልጣን ክፍፍልንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ተሳትፎን ያዳብራል። ከዚህም ባሻገር በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የአገሪቱ ሕገ መንግስ በሚደነግገው መሰረት ሕዝብን ያለምንም አድልዎና በደል እያስተዳደረ መሆን አለመሆኑን ለሕዝብ ያስተጋባል። የፕሬስ አገልግሎት ላወቀበትና በአግባቡ ለተረዳው አወንታዊው አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን አሉታዊውና ነቀፋው እንኳን ሳይቀር ገምቢ ነው። ስህተትን እየጠቆመ፥ጠማማውን እያቀና መንግሥትንም ቢሆን ለአስተዳደር ጥራት ያሰናዳል እንጂ አንድም ጉዳት የለበትም።  

ስለዚህ ፕሬስ ማለት የሕዝብን ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ እየጠበቀ የሚያስጠብቅ  የወቅቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ እውነትና ሂደት እየተከታተለ ለሕዝብ የሚያቀርብና ለዲሞክራዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ተግባራዊ ተቋም ነው። እንዲህ ያለው ነባርዊ ሐቅ ለወያኔዎች ባይዋጥላቸውም ቅሉ፤ የተባለለትም ሆነ የሚባልለት ሁሉ የፕሬስን የከበረ ዋጋ የሚመጥን አይደለም።


በነፃ ፕሬስ በሚመሩ አገሮች ዘንድ ፕሬስ ከህግ አውጪ፥ ከህግ ተርጓሚና ከህግ አስፈፃሚ አካላት ቀጥሎ ያለውን አንጋፋ የተካነ አካል የተካነ ሲሆን፤መንግስታቱ የየሀገራቸው ህግና ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት ሕዝቦቻቸውን በኣግባቡ እንዲያስተዳድሩ መጠን የለሽ እገዛ እንደሚያደርግ አስረግጠው ያምኑበታል። ከዚህ መርህ አንፃር በምናገኘው ሁነት የአገራችንን  ኢትዮጵያን ሁኔታ ስንቃኝ ሳለን፥ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ አምባገነን መንግሥት ፕሬስ በነፃነት እንዳይቀሳቀስ ጠፍሮ በመያዝ የሥርዓቱ ተቀናቃኝ አድርጎ የግልብጦሽ በመረዳትና አውቆ አጥፊ በመሆን ሌት ተቀን እያሳደደው ይገኛል።

የሕዝብን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚገባ ከመጠበቅና ከማስጠብቅ አኳያ
ሚዲያ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ከማበረታታት ይልቅ በሥልጣን ላይ የመቆየት ጥማቱን ለማርካት ሲል በተለያየ እኩይ መንገዱና አሰራሩ  እያቀጨጨውና እያሳደደው ይገኛል።

በቅርቡ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሴክረተሪ ጆን ኬሪ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የኢትዮጵያ የፕሬስ
ነፃነት አደጋ ላይ እንዳለና ምን ያህል እንዳሳሰባቸው ለመግለፅ በእስር እንግልት ላይ የሚገኘውን የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ስም በመጥቀስ በስልጣን ላይ ላለው የወያኔ መንግስት ስጋታቸውን ገልፀው ነበር። የስጋታቸው መነሾ ግልፅ ነው። ስርዓቱ ብሎገሮችንና ጋዜጠኞችን፥የፖለቲካ መሪዎችንና አባላትን ብሎም ደጋፊዎቻቸውን አስሮ እያሰቃየና እየደበደበ ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረግ ላይ ለመሆኑ፥ አንዳንዶቹም የሚወዷትን አገራቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ መሆናቸውን በቂ መረጃ ስላላቸው ነው። በስደት ላይ እያለ ውድ ሕይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ ነገር እንደ እግር እሳት የሚያቃጥል የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።

ለዚህ ዘግናኝ ተግባሩ ዋቢ ካስፈለገ ይህንን ፀረ ፕሬስ አቋሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማራመድ ይረዳው ዘንድ ሃገር አቀፍና አለም አቀፍ እውቅና የሌለው የፕሬስ ህግ በማፅደቅ ጋዜጠ   ኞችንና ብሎገሮችን ባሸባሪነት እየፈረጀ በማንገላታት ላይ መገኘቱ የማካድ ሐቅ ነው።

እንደተለመደው በመጪው ግንቦት 2007 ምርጫ “አሸንፌያለሁ” ለማለት ከወዲሁ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኙ ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና አበላትን ያለርሕራሄ ያንገላታል። ከተነሱበት ሕዝባዊ ዓላማ ለማደናቀፍም ቀንተሌት እየተንደፋደፈ ይገኛል።

በዚህ ብቻ አልተመለሰም። “እኛ የምንለውን ብቻ እንነጋገር፤እኛው ተነጋግረን እኛው እንወስን” በማለት የምርጫ ቦርድ ባለስልጣናት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን ለማሳመን ሲሯሯጡ ጥቅምት 7/2007 .ም በግዮን ሆቴል የጠሩትን ስብሰባ 12 ፓርቲዎች ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የወያኔ መንግሥት የምርጫ ምህዳሩን ማጥበቡና አመራሩ የብዙሐኑን ፍላጎት የማያካትት፥ከዲሞክራሲያዊ አሰራር ጋራም የሚጣረስ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የፕሬስ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ስለሁኑ ነፃ ፕሬስ በሌለበት ሥርዓተ መንግሥት ነፃ ምርጫ ከቶውኑ ሊኖር ስለማይችል ነው።     

እንግዲህ እየተደረገ ያለው የአደባባይ ምስጢር መሆኑን በመገንዘብ የሚያለያዩንን ጥቃቅንና ጊዜአዊ ሰበቦች ገለል አድርገን የጋራ የሆነውን ቁርጠኛ ገድል መጋደል የግድ ነው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለን የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት፤ የሕዝቦቿንም ሰላማና ፍትሕ የምንሻ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከመቸውም በበለጠ ትግሉን ማጠናከር ይኖርብናል። “ልብ ያለው ሸብ!’’ እንዲሉ ነገ ለሚመጣው ትውልድ ልናወርሰውና
ልናስረክበው የምንችለው ሕዝብም ሆነ ልሳነ ሕዝብ የሆኑት ነፃ ፕሬሶች እንዲያብቡ በማመቻቸት የነጻነት ደንቃራ የሆነውን ሥርዓት ከመቃወምና ከመታገል ወደ ኋላ እንዳንል የከበረ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

                                                                                        ምናሴ መስፍን
                                                 ከኦስሎ ኖርዌ


     

2 comments:

 1. Mr. Mesfin.
  Ethiopia is the leading African nation in respect of human rights, democracy and freedom of expression. There is no any journalist or blogger who is jailed because of his political opinion or view. Trying to destabilize the country and criticizing the Ethiopian government with baseless accusation will never let you free and you will pay for it.

  ReplyDelete
 2. አቶ ምናሴ!
  ስለማያውቁት ነገር ገብቶ መዘባረቅ መውጯው ከባድ መሆኑ መዘንጋት የለብህም።
  በጋዜጠኛም ሆነ በብሎገርነት ጥላ ስር በመሆን ከማንኛም አሸባሪ ከሆኑ ኅይሎች ጋር በማበር የሀገሪትዋን ህገ መንግት በሀይል ለመናድና ለልማትዋ እንቅፉት ፈጣሪ የሆኑ ሁሉ ከህግ ጥላ ስር መሸሽ አይችሉም። አንተም ብትሆን ዛሬ ከሃር ውጪ ስለሆን ብቻ የበሬ ወለደ ፅኡፍ ነገ በህግ ያስጠይቅሃል።

  ReplyDelete