Wednesday, August 13, 2014

2007ን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሲባል እስከ ምርጫ ወይስ እስከ ዴሞክራሲያዊ መንግስት

ዳንኤል ተፈራ — የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ

በጣም በቅርቡ አንድ ስላልነገርኩት ስሙን የማልጠቅሰው ጉምቱ የሚባል ጋዜጠኛ ወዳጄና ሌላ አንድ ጎልማሳ ጋር ኢ-ወጋዊ በሆነ መንገድ ስለተቃዋሚ ጎራው ማውጋት ይዘናል፡፡ የጨዋታችን መነሻ ደግሞ አንድነትና መኢአድ ከብዙ ውጣ ውረድና ድርድር በኋላ ከፍፃሜ ለማድረስ ደፋ ቀና እያሉበት ያለው ውህደት ነው፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካውን በቅርበት እንደሚከታተሉ አንዳንድ ግለሰቦች አስተያየት ‹‹ውህደቱ መሳካት አዎንታዊ ጎን ቢኖረውም ዘግይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የውህደቱ ጣጣ አልቆ፣ የሚተባበሩት ተባብረው ወደ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ የሚገቡበት ነበር›› ይላሉ፡፡ የውህደቱ መሳካት ጥሩ ሆኖ ውህደቱም ሆነ ትብብሩ ዘለቄታ ላለው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ወይስ ምርጫ ስለደረሰ ብቻ? የሚል ጥያቄ አንስቶ መመለስ ተገቢ ነው፡፡

ጎልማሳው ሰው ቀበል አድርጎ ለተቃዋሚው ጎራ ቅርበት አለው ብሎ ስላመነ ይመስለኛል አይኖቹን እንደ ቆመህ ጠብቀኝ መሳሪያ ፊቴ ላይ ወድሮ ‹‹በተቃውሞ ጎራው በኩል ተቀራርቦ፣ ተባብሮና ተዋህዶ የመስራቱ ነገር እምብዛም ባለመለመዱ ወይም እስካሁን ባለመሳካቱ ይመስለኛል ውህደት እንዳንድ አደረጃጀትን የሚያጠነክር የፖለቲካ ስራ ሳይሆን እንደግብ ይታያል፡፡ ከፖለቲካ ጠቀሜታ አንፃር ሳይሆን ከምርጫ፣ ከግል ጥቅምና ዝና አንፃር ይታል፡፡ ውህደት እንዳንድ የለውጥ ማምጫ ስትራቴጅ ባለመታየቱ በህዝቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡ መጠላለፍና ሴራ በብርቱ የሚያጠቃው የፖለቲካ ባህላችን ግን ‹‹እኔ ብቻ አዋቂ፣ እኔ ብቻ ንጉስ›› ከሚል ጨፍላቂ ሰርዓት ጋር ሲደመር ግራ ማጋባቱ ላይገርም ይችላል፡፡


 በአጠቃላም የተቃውሞ ጎራውን ከአሮጌና ምርጫን ግብ ካደረገ አስተሳሰብ አላቅቀው የራሱ መነሻና መድረሻ ያለው ስትራቴጅ የሚነድፉ መሪዎች ያስፈልጉታል›› አለ፡፡
ጎልማሳው ሁለታችንም ዝም ብለን የልቋጨውን ሀሳብ እንዲጨርስ እየጠበቅነው እንደሆነ ሲረዳ፡- ‹‹ለነገሩ መምራት የሚችሉ ግለሰቦች ለመምጣት ቢሞክሩም በጥርጣሬና በሴራ ፖለቲካ ተስተካካይ የሌላቸው ግለሰቦች እንዲርቁ ያደርጓቸዋል፡፡ ከነሱ ተረፉትን ደግሞ ኢህአዴግ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ ያስራል፡፡ ስለዚህ ውህደት ብቻ ሳይሆን ውህደቱን የሚመራ ጥብቅ መሪ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ ሞክሮ የሚሄድ ሳይሆን ከምርጫ ባሻገርም ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ የሚቀይስ ብርቱ ሰው›› በማለት ሃሳቡን ጠቀለለ፡፡

ያነሳው ሃሳብ ጥቅል ቢሁንም ለውይይታችን ማጠናከሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡ የጨዋታችንም ጭብጥ ሰፋና የተለያዩ ጋዜጦች ላይ ስለተቃዋሚው የሚፃፉትን አሉታዊ ትንታኔዎችን እያነሳን ነበር፡፡ የተቃዋሚ ጎራው መተቸት አለበት ወይስ የለበትም፤ ትችቱ ምን አይነት ቢሆን ለሀገር ይጠቅማል፤ ገዥው ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን አይነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፤ ለምን? የሚሉ ጉዳዮችም ተነሱ፡፡ መቼስ ተቃዋሚው መተቸት የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ካቴና ይዞ የሚመጣው ‹‹ለምን ነካችሁኝ፤ ለምን ተቻችሁኝ›› ብሎ አይደል እንዴ? ታዲያ እንዴት አሁን ካለው ስርዓት የተሻለ ሀገር መምራት እችላለሁ ብሎ እየታገለ ያለውን ተቃዋሚ አይነካ ማለት ይቻላል? እያልን ስናነሳ ጋዜጠኛው ወዳጄ የተቃውሞ ጎራ አሁን ባለበት አቋም የሚያስፈልገው ገንቢ ትችት ነው የሚል ነገር ዱብ አደረገ፡፡ በድማሜ ውስጥ ሆኜ ‹‹ለምን?›› የምትል ቤሳ ጥያቄ ማቅረቤ አልቀረም፡፡ እሱም እንዲህ መለሰልኝ፡፡

‹‹አየህ ተቃዋሚው ባጠቃላይ ከአፈጣጠሩ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚፈጥረው ችግር ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ለባለፉት 23 ዓመታት ተቃዋሚው በተበታተነ አሰላለፍ፣ ምርጫን ብቻ ግብ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ይህ አሰላለፍም ዘላቂነት ላለው ድልና የማይናድ የተቃዋሚ ግንብ ለመገንባት አላስቻለውም፡፡ ግልፅ ራዕይና ስትራቴጅ በማስቀመጥ፣ ተተኪ ፖለቲከኞችን በማፍራትና በውስጡ ተሰግስገው እንደ አሜባ የሚራቡትን ሰርጎ ገቦች ማጥራት አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ ‹‹ተቃዋሚዎች እግር እስከሚያወጡ መጠበቅ ተገቢ አይደለም›› በሚለው የተበላሸ አመለካት የተነሳ ከፍተኛ ወጭ መድቦ ተቃዋሚ ጎራውን በአይነ ቁራኛ ይጠብቃል፡፡ ከተራ ስም ማጥፋትና በውስጥ ክፍፍል ለመፍጥር ከመስራት ጀምሮ እስከ ‹‹ሽብርተኛ›› ብሎ እስከማሰር የደረሰ መዋቅር ዘርግቷል፡፡ ስለዚህ አሁን መሆን ያለበት ተቃዋሚውን ሃይል መተቸት ሳይሆን  መደገፍ ነው፡፡ 

በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ፣ በሰላማዊ ትግል አምኖ እየታገለ ያለን ሃይል እንደ ጠላት የሚቆጥር መንግስት ባለበት ሀገር፤ ተቃዋሚው የስብሰባ አዳራሽ፣ የሚከራይ ቢሮ ለማግኘት በሚቸገርበት ሁኔታ፤ አባሎቹን እየተከታሉ ‹‹ወይ ከስራህ አሊያም ከተቃውሞህ አንዱን ምረጥ›› በሚባልበት ስርዓት ውስጥ ቀዳሚው ነገር ተቃዋሚውን መተቸት ሳይሆን ተቃዋሚው እግር እንዲያወጣ ማገዝ ነው፡፡ እግር አውጥቶ የቡጢ ሚዛኑ ሲስተካከል ግን ገንቢ ትችት ብቻ ሳይሆን አሁን ኢህአዴግ በሚተችበት ደረጃ መተቸት ነው›› የሚል ትንሽ ትንታኔ አቀረበ፡፡
በርግጥ በጋዜጠኛው ወዳጄ በጎ ሃሳብ የሚስማሙም የማይስማሙም ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶች መጠንከርም ሆነ መልፈስፈስ የተቃዋሚው የራሱ ምርጫ ነው የሚሉ አጋጥመውኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚው ጠንካራም ሆነ የተልፈሰፈሰ እንዲሆን የሚያደርገው ህዝቡ ሊሆን ይገባል የሚሉም አሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ የሚቋቋመው ለህዝብና ለሀገር አገለግላለሁ ተብሎ ነው ስለዚህ ባለድርሻው ህዝብ ከሆነ ጠንካራ ለሚለው ድጋፍ በመስጠትና በአጉል አቅጣጫ ለሚነጉደው ትብብር በመንፈግ ለተቃዋሚው አቅም ሊፈጥር ይችላል፡፡ እኔም አዳምጨ ሳበቃ ይህንን ሃሳብ ተመርኩዤ የራሴን ምልከታ ለመሰንዘር ወደድሁ፡፡

‹‹ጋንግስተሪዝም››

አስቀድሞ ትውስ ያለኝ ጋንግስተሪዝም ነው፡፡ ለሀሳቤ መነሻ ሆነኝ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ በቅርቡ ያሳተመው ‹‹የትግራይ ሕዝብ፤ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ›› የሚለው መፅሀፍ ነው፡፡በመፅሐፉ በ1993 ህወሃት ለሁለት ስትሰነጠቅ መሰረታዊ ልዩነቶች ምን እንደነበሩ ስብሃትን ጠይቋቸው ሁለት ነገር አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም በኤርትራ ጉዳይ አንደኛው እነ ስየ መለስን ‹‹ተንበርካኪ ሆናችኋል›› የሚል ሲሆን የነ መለስ ቡድን በበኩሉ በመልሶ ማጥቃት ተንበርካኪነትን ባለመቀበል ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ጠፍቷል ‹‹ጋንግስተሪዝም›› እያደገ ነው በማለት ለመመከት ተገድደዋል፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ እንጅ እነ መለስ ለዴሞክራሲ ተጨንቀው እንዳልሆነ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምስክር ነው፡፡ ጋንግስተሪዝም በተገላቢጦሽ በክፍፍሉ አሸናፊ ሆኖ የወጣው የነ መለስ ቡድን መለያ መሆኑ ፈገግ ያሰኛል፡፡

ጋንግስተሪዝም (ቦዘኔነት) ዋናው የተቃዋሚ ጎራ ችግርም ነው፡፡ ቦዘኔዎች ዋና ተግባራቸው ስራ መስራት አይደለም የሚሰሩትን እየተተከተሉ ማጥቃት እንጅ፡፡ አሁን ያለው ወጣት ትውልድ ግን ከጋንግስተሪዝም ይልቅ ዴሞክራሲ ልዩ መለያው እንደሆነ መመስከር ይገባኛል፡፡ ጋንግስተሪዝም በዋናነት የአባቶቻችን ትውልድ መለያ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ የሃሳብ ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ማጥፋት የተለመደ ነው፡፡ በተቃዋሚው ጎራም አባራሪና ተባራሪ አለ፡፡

 ‹‹የተቃዋሚዎች እናት አንድ ናት›› እንዲል አስራት አብርሃም በቅርቡ እንኳን ታዋቂውን ፀሃፊና ፖለቲከኛ አስገደንና ሌሎችን አረና አባሯል፡፡ አረና ወደ ማባረሩ የገባው ሌላው በአጭር ጊዜ በፖለቲካ ስራውና በሚያቀርባቸው ፅሁፎቹ እውቅና ያተረፈው አብርሃ ደስታ ከታሰረ በኋላ ነው፡፡ ታዲያ የተያዘው ማጠናከር ወይስ ማላላት? ፕሮፌሰር እንዳሉት የስላሴዎች እርግማን ይሆንን? አደህይቶ መግዛት፤ አጎሳቁሎ ተስፋ ማሳጣት፤ ባዶ ማድረግ፡፡ ጋንግስተሪዝም፡፡ ይሄ የትውልድ ውልቃት መጠገን አለበት፡፡ ቅድሚያ ለውጥ ፈላጊነት ጋንግስተሪዝምን ማሸነፍ አለበት፡፡

በመቀጠል የተቃውሞ ጎራው ከተከላካይነትና ከተጠቂነት ወደ አጥቂነት የሚሸጋግርበትን የፖለቲካ ስትራቴጂ የሚነድፍ መሪ ያፈልገዋል፡፡ ትግሉን ከምርጫ ፖለቲካ በላይ አሻግሮ የሚመለከትና የኢህአዴጋውያኑን የጠቅላይ አምባገነንነት አባዜ ተረድቶ የመስበሪያ ስልት የሚቀይስ የፖለቲካ ማሃንዲስ መፍጠር ይገባል፡፡ የተቃውሞ ጎራው እስካሁን በመጣበት መንገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ አሁንም ስለለውጥ ከፍተኛ ዋጋ ዕየተከፈለ ነው፡፡ ነገ ትልቅ መሪ የሚሆኑ የኢትዮጵያችን ተስፋዎች ጨለማ ክፍል ውስጥ ተጥለዋል፡፡ እነ አንዷለም አራጌ፣ ኦልባ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ናትናኤል መኮንን፣ የሽዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሺና ሌሎች በፖለቲካ እምነታቸው ብቻ ወደ ጨለማ ክፍል የተወሰዱ ዜጎች የከፈሉት ዋጋ ፍሬው መታየት አለበት፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ምርጫ ስለደረሰ ብቻ ሱፋቸውን አሳምረውና ጫማቸውን ወልውለው ከተቻለ ፓርላማ፤ ካልተቻለ ደግሞ ሌላ አምስት አመት እስከሚመጣ እቤታቸው በሚቀመጡ ፖለቲከኞች አይደለም፡፡ ለውጡ ሊመጣ የሚችለው ያለ ፋታ በሚሰሩ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች እንጅ፡፡

ጋንግስተሪዝምን (ቦዘኔነትን) አሸንፎ ምርጫ ካለና በአግባቡ ከተጠቀሙበት የለውጥ ማምጫ መሳሪያ ነው፡፡ አሁን ያለው ገዥ ፓርቲ ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኝነቱ አለው ተብሎ አይገመትም፡፡ ነገርግን የተቃዋሚው ስራስ ምን መሆን አለበት? አፋኝነቱን ከመተንተን ያለፈ የማስገደድ ሃይል ያለው ጡንቻ ያስፈልገዋል፡፡ በምርጫው መሳተፍ ይገባል ወይስ አይገባም፤ ብንሳተፍ ምን ምቹ ሁኔታዎች አሉ፤ ምን ተግዳሮቶች አሉ፤ በአማካይ ስንት ወንበር አሸንፈን ስልጣን መያዝ እንችላለን፤ ምርጫው ኢፍትሃዊ እንዳይሆን ምን ምን ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፤ ህዝቡን የማንቂያ ስትራቴጅዎች፣ ህዝባዊ ንቅናቄ የመፍጠሪያ ስልቶች፣ የችግር አፈታት ስልቶችና የታሰሩ አመራሮች ለምርጫው ያላቸው አጋርነት መፈተሽ ይገባል፡፡

በአመራር ደረጃም በምርጫው ተቃዋሚ ጎራው ሞካሪና አዳማቂ ሆኖ ሳይሆን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ስትራቴጅ የሚነድፉ፤ የተነደፈውን ስልት ወደ ውጤት የሚቀይሩ የኦፕሬሽን ሰዎች፤ ይህንን የሚደግፉና የሚያሰርፁ አባላት በብዛት ያስፈልጋሉ፡፡ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢዎ አንደታዘበው ግን በተቃውሞ ጎራው ስለ ግልፅ የማሸነፊያ ስትራቴጅና ስለ ስልት እምብዛም አይወራም፡፡ ሕዝቡ ካለበት የኑሮ ጫና፣ የነፃነት እጦትና የስርዓቱ ሹማምንት ከሚያደርሱበት ምሬት አንፃር የተቃውሞ ጎራውን በስፋት ይደግፋልና ይመርጣል የሚለውን ግምት በተግባር መፈተሽና በአግባቡ የዚህን የተገፋ ህዝብ ይሁንታ የሚያገኙበትን ተክለ ቁመና መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ዞሮ ዞሮ ከላይ ለመግለፅ በሞከርኩት መንገድ የተቃውሞ ጎራው ከውህደት ባሻገር ከአመራር አንፃርና አጠቃላይ ትግሉ ያለበትን ነባራዊ ሁናቴ ፈትሾ፤ የሚፈለገውን ቁርጠኝነት አሳይቶ ለውጥ ከማምጣት አንፃር መሰራት እንዳበት አንስተን የኢ-ወጋዊ ውይይታችን ማጠቃለያ የሆነው በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሃገራቀፍ ምርጫ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ ምርጫ፣ ምርጫ ስል ምርጫ አለ እንዴ! በ2002 ምርጫ ተደርጎ ነበር እንዴ! በማለት ታማኝነትን ያተረፈ ምርጫ ካልተደረገ እንደተደረገ አይቆጠርም በማለት ጠንከር ያለ መከራከሪያ የሚያቀርቡ እንዳሉ ሳይዘነጋ ማለት ነው) በአንፃራዊነት ጠንካራ የሚባሉ ፓርቲዎች 2007ን እንዴትና ለምን ግብ ሊጠቀሙበት እያሰቡ ነው? ምርጫውን ለመሞከር ወይስ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ላለው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት? የሚለው ዋና ጥያቄ ነው፡፡

የምርጫ ጊዜ ወፎች
ከጋንግስተሪዝም ለጥቆ የሚመጣው የምርጫ ግርግር ፈጣሪው ነው፡፡ ስለ ሰላማዊ ትግል ስናስብ ስለ ውጤትም ማሰብ ይገባል፡፡ ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን እንደ መስቀል ወፍ ምርጫና የምርጫ ወሬ ሲሰማ የሚሉትን የምርጫ ጊዜ ወፎች መታገል ይገባል፡፡ የነዚህ ወፎች ግብ ከላይ እንደገለፅኩት ዘለቄታዊ ለውጥ በማምጣት የሚፈለገውን ዴሞክራሲ መገንባት አይደለም፡፡ ዘላቂነት ያለው የለውጥ ስሜትም ሆነ ስትራቴጅ ስለሌላቸው በምርጫ ጊዜ ብቻ ብቅ ይሉና ‹‹ሲያቃጥል በማንኪያ ከበረደ በእጅ›› የምትል የጮሌ ስትራቴጅ በመያዝ ምርቻ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉት ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይሎች ካራባት በማሳመር ምርጫ ማሸነፍ ይቻል ይመስል ‹‹የ2007ን ምርጫማ መሞከር አለብን›› ይላሉ፡፡ መሞከር ብሎ ትግል፡፡ ሰው የሚወዳደረው ለመሞከር ሳይሆን ለማሸነፍ ነው፡፡ የምርጫ ጊዜ ወፎች ግን ‹‹ኸረ እባካችሁ ህዝብና ሃገር መሞከሪያ አይደለም፤ ኢህአዴግ በዚህ ጭቁን ህዝብ ላይ የሞከረበት ይበቃል፤ ዘላቂነት ያለው ስትራቴጅና ራዕይ ካላችሁ ወዲህ በሉ›› ሲባሉ ያኮርፋሉ፡፡ ይፈርጃሉ፡፡ ያችኑ የሚውቋትን የሴራ ጨዋታ ከች ያደርጓታል፡፡ ያ የፈረደበት ምርጫ 97 ይጠቀስና ‹‹ስንት ዋጋ ከፍለን፤ ደማችን ፈስሶ አጥንታችን ተከስክሶ…›› የምትል ‹ፉከራ› በማምጣት ጉዞ ወደ ምርጫ ሙከራ ይሆናል፡፡

ዋናው ቁምነገር የተከፈለውን ዋጋ ለማሳነስ አይደለም፡፡ በ97 ደግሞ የስርዓቱን አስከፊ ገፈት ያልቀመሰና ዋጋ ያልከፈለ የለም፡፡ ዳሩ ግን ከታሪክ መማር እንጅ በታሪክ መኖር አይቻልም፡፡ በታሪክ መኩራት እንጅ በታሪክ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ማሸነፍ የሚቻለው ዛሬ ላይ አቅዶ፣ እቅዱን ወደ ተግባር ለውጦ፣ ህዝቡን አሳትፎ መጓዝ ሲቻል ነው፡፡
አንድነትና መኢአድ ጀምረውታል፡፡ ቢያንስ የሁለቱን ትላልቅ ፓርቲዎች ሃይል በአንድ መስመር ማስገባት የሚቻልበት ታሪካዊ ስራ ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ አሁንም ዳርላይ የቆሙ ፓርቲዎች አሉ፡፡ የተናጠሉ ጉዞ አያዋጣም እየተባለ ነው፡፡ 2007ን በአግባቡ ለመጠቀም የተሰባሰበ አንድ የተቃውሞ ሃይል መፍጠር አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ የተቃውሞ ሃይል የሚመጥንና ወደ ፊት የሚያራምድ አመራርም ያፈልገዋል፡፡ የምርጫ ጊዜ ወፎች ምርጫ መግባትን እንደ ግብ ስለሚያዩ ከተቻለ ትግሉ ምርጫ የመሞከር ሳይሆን ትግሉ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ለማምጣትና ለትልቋ ሀገራችን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ስለሆነ ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ አልገባም ካሉ እነሱንም መታገል ነው፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢዎ በድጋሚ እንደታዘበው አሁን በተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ሁለት አይነት የውስጥ ትግል እየተካሄደ ነው፡፡ ይሄ ትግል የሚካሄደው በለውጥ ፈላጊ ሃይሎችና (ይሄ በብዛት የወጣቱን ቀልብ የሳበ ይመስላል) በቀደመው መንገድ ማዝገም በሚፈገልጉ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከእኛ በላይ ላሳር ብለው የሚምኑ፤ ነገርግን በተግባር ውጤት ያላስመዘገቡ ሃሎች መካል ነው፡፡ በዚህ መልኩ መታገል መብት ነው፡፡ ፖለቲካ ውስጥ የውስጥ ትግልና የውጭ ትግል መኖሩ የተለመደ ነው፡፡ የሚዳኘው ግን አባላትና ህዝቡ ይሆናል፡፡

የግል ይዞታነት
በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ትግሉን ፍሬያማ ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነ የሚታመነው የግል ዞታ አመለካከት ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከምርጫ ባለፈ የምንመለከት ከሆነ በተቃዋሚ ጎራው የሚታየውን ፓርቲን እንደግል ንብረት የመመልከት ዝንባሌ ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ በትግል ውስጥ ዋጋ መክፈል ማለት ፓርቲውን የግል ንብረት ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ፓርቲ የሚቋቋመው ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ርዕዮተ ዓለምና የማስፈፀሚያ ስልት ይዞ እሱን ተግባራዊ ለማድረግ እንጅ የግል ዝናና ሞገስ ለማግኘት አይደለም፡፡

እኔ አይነኬ ነኝ የሚሉ እንዳንድ ግለሰቦች ‹‹እኔ አንደዚህ፣ እንደዚህ አድርጌ በመሰረትኩት ፓርቲ…›› የምትል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ ፓርቲ ውስጥና ፖለቲካ ውስጥ ‹‹እኔ›› የምትል የግለኝነት ሃሳብ መነሳት ከጀመረች ህዝብና ሀገር ተዘንግቷል ማት ነው፡፡ ፓርቲን እንደ ግል ዞታ መመልከት የሚመጣው እኔ ከሚል ያልተባረከ ሃሳብ ነው፡፡ ማንም ሰው ማወቅ የሚገባው ወደ ኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ የሚመጣው ሊሰጥ እንጅ ሊቀበል አይደለም፡፡ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መስጠት ሳይሆን መቀበል የሚፈልግ ካለ ወደ ኢህአዴግ ዘንድ ቢሄድ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ያለው ግን መስጠት ብቻ ነው – ያውም ክቡር የሆነውንና የመጨረሻ ውዱን ህይወት፡፡ ስለዚህ በተቃውሞ ጎራ ያለውን የግል ይዞታ አመለካከት መታገል ወደሚፈለገው የለውጥ ግብ ያደርሳል፡፡

ለማጠቃለልም አሁንም ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን ሀገራቀፍ ምርጫ አለ፡፡ በኢህአዴግ በኩል ግልፅ የሆነ  የመጠቅለል አካሄድ እየታየ ነው፡፡ ይህንን የአፈና አካሄድ መስበር የሚቻለው የምርጫ ግርግር ውስጥ በመግባት ወይም ለመሳተፍ በመጓጓት ብቻ አይደለም፡፡ በቅድሚያ ምርጫ እንዲኖር መታገል ያስፈልጋል፡፡ 2007ን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ መጠቀም የሚቻለው እስከ ምርጫ ብቻ በማሰብ አይደለም፡፡ ከምርጫ ባሻገርም ተቃውሞ ጎራው ላይ አስተማማኝ መሰረት ጥሎ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መመስረቱም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሁለንተናዊ ችግሮችን ፈትሾ፣ አካዶችን በግልፅ ተችቶ መድረሻ ጎል ማስቀመጥ፡፡ አዎ ጊዜው እየሮጠ ነው፡፡ ህዝቡም የተጫነበት ቀንበር ከብዶታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ልክ መሮጥ ያስፈልጋል፡፡ ጎበዝ እንሩጥ፡፡

No comments:

Post a Comment