‹‹ተመስገን፣ የህዝብ ልጅ ነው፤ ነገም ከነገወዲያም የህዝብ ልጆች ይፈጠራሉ››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹ስለተመስገን ደሳለኝ ሃሳቤን አስተላልፍልኝ›› ካለኝ የተወሰደ
ከትናንት በስትያ፣ ሰኞ ዕለት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአንድነት ፓርቲ ጸሐፊ የሆነውን አቶ አንዷለም አራጌን በ2007 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ላገኛቸው ችዬ ነበር – ለአቤል አለማየሁ ጋር፡፡ ባለፈው ሳምንት የ‹‹ባንዲራ ቀን›› በተከበረበት ዕለት ቃሊቲ ከወዳጄ እዩኤል ፍስሐ ጋር ሄጅ እነስክንድርን መጠየቅ ሳንችል ተመልሰን ነበር።
የሆኖ ሆኖ፣ ከእስክንድር ጋር ለ15 ደቂቃ ያህል ለማውጋት ችለን ነበር። እስኬው፣ ሁሌም መንፈሱ ጠንካራ ነው። ሰኞም ያ አስደማሚ ጥንካሬው፣ ትህትናው፣ እውነተኛ ቅንነቱ፣ ብርታቱ፣ ቀናኢነቱ…አብረውት ነበሩ።
ሰዓት ደርሶ ከእስክንድር ጋር ቻው ከተባባልን በኋላ ‹‹ኤልያስ፣ አንዴ ላናግርህ›› ብሎ ከጠራኝ በኋላ ‹‹እባክህ አንድ መልዕክት ስለተመስገን ደሳለኝ አስተላፍልኝ›› አለኝ፡፡ እስንክድር፣ ሁሌ ሀሳቤን አስተላልፍልኝ ሲለኝ ግልጽነቱ እጅግ ይማርካል።
‹‹እሺ›› አልኩት››
‹‹ተመስገን፣ ጥሩ ታጋይ እና ጥሩ ሰው ሆኖ ከእስር ይወጣል። ተመስገን የህዝብ ልጅ ነው። ነገም ከነገወዲያም የህዝብ ልጆች ይፈጠራሉ። እስሩ ስለሀገሩ ያበረታዋል፤ ያጠነክረዋል። ብዙ ነገር እንዲረዳ ያደርገዋል። ሰዎች ይታሰሩ እያልኩ አይደለም። ይሄ አንዱ የሰላማዊ ትግል መስራት ውጤት ነው። በለውጥ እና በትግል መስመር ላይ ያሉ ኢትዮጵኖች መታሰራቸው ነገ ለውጥ ያመጣል።››
ካለኝ በኋላ ለሁሉም ‹‹እወዳችኋለሁ፣ አከብራኋለሁ፣ በተሰማራችሁበት የህይወት
መስመር፣ በሰላማዊ መንገድ በርትታችሁ ለለውጥ ታገሉ!›› በልልኝ ብሎኛል።
እኔም ዛሬ ‹‹የሀገሪቱን ህዝቦች አንድነት እንዲፈርስ እና በሀገሪቱ ሕዝቦች መካከል ጸብና ቁርሾ እንዲፈጠር በማሰብ …›› የሚል ከባድ ክስ ብቀበልም የእስክንድርን መልዕክት ለማስተላለፍ አልተቆጠብኩም።
ፍቅር ያሸንፋል!
Elias Gebru Godana
No comments:
Post a Comment