Friday, October 17, 2014

ሰማያዊ፣ መኢዴፓና ኢብአፓ የምርጫ ቦርድን ስብሰባ ረግጠው ወጡ


ከደቡብ ኅብረት ፕሮፌሰር በየነ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል


ምርጫ ቦርድ በጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመወያየት በጊዮን ሆቴል የጠራውን ስብሰባ “ጥያቄዎቻችን የሚመልስ አይደለም” በሚል የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ በተጨማሪም የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በትናንትናው ዕለት ከምርጫ 2007 ዓ.ም በፊት ውይይት ሊደረግባቸውና ሊፈቱ ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ ያስገቡ ቢሆንም በዛሬው ስብሰባ በደብዳቤ ካሳወቋቸው ችግሮች ይልቅ የጊዜ ሰሌዳ ቅድሚያ የተሰጠው በመሆኑ የምርጫ ምህዳሩን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡


ስብሰባውን ረግጠው ከወጡት መካከል የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ዋና ጸኃፊ ወ/ት መሊሃ ጀሃድ “ትናንትና 12 ፓርቲዎች ሆነን ፈርመን ያስገባነው ደብዳቤ ነበር፡፡ በዚህ ደብዳቤ ባነሳናቸው ጥያቄዎች ላይ መልስ ካልተሰጠን በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ እንደማንነጋገር ገልጸን ነበር፡፡ ቦርዱ ደግሞ ትናንትና ባስገባነው ደብዳቤ ላይ ከመነጋገርና ለጥያቄዎቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ነው የምንነጋገረው አለን፡፡ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንድንነጋገር ሲያደርጉ እኛ በአካሄድ ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲሰጥ ጠየቅን፡፡ የቦርዱ ተወካዮች እሱን በሌላ ጊዜ ስብሰባዎች ላይ እንፈታዋለን፣ ዛሬ ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንነጋገር በማለታቸው ስብሰባውን ረግጠን ወጥተናል” ስትል ረግጠው የወጡበትን መነሻ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡

በተመሳሳይ የመኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ኑሪ ሙደሂር “ምርጫ ቦርድ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አደርጋለሁ የሚለው አባባሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጥያቄዎችን አቅርበን ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ የዛሬ 5 አመትም ጠይቀናል፡፡ ትናንትም በጋራ በደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ከጀመረ 5 አመቱ ነው፡፡ ይህን ቅስቀሳ የሚያደርገው በመንግስት ገንዘብ ነው፡፡ የእኛ ጥያቄ የምርጫ ምህዳሩ መስፋት አለበት ነው፡፡ ትርጉም ያለው ምርጫ መደረግ አለበት ነው የእኛ እምነት፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው እኛ ስብሰባውን ረግጠን የወጣነው” ብለዋል፡፡

ሌላኛው የመኢዴፓ ተወካይና የፓርቲው ዋና ጸኃፊ አቶ ዘመኑ ሞላ በበኩላቸው “እነሱ ካቀረቡት የጊዜ ሰሌዳ ይልቅ የሚቀድመው ሜዳውን ማስፋት ነው፡፡ ትናንትና 12 ፓርቲዎች ተፈራርመን ያስገባነው ደብዳቤ ነበር፡፡ እኛም ቀድመን በተነጋገርነው መሰረት የጊዜ ሰሌዳው ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን የለበትን የሚል አቋም ይዘናል” ሲሉ ስብሰባውን ካዘጋጀው ምርጫ ቦርድ ጋር ያላቸውን ልዩነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በሚቀጥለው ስለ ችግሮቻችሁ ቁጭ ብለን እንወያያለን በሚል የማባበል ስራ እንደያዘ የገለጹት አቶ ዘመኑ “የ2002ትን ምርጫን ገምግመናል፡፡ ፓርቲዎች ያስገባነው ደብዳቤ አለ፡፡ አሁንም ገዥው ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሜዳውን እያጠበበና ራሱ ብቻ እየተጫወተበት ይገኛል፡፡ ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ ከታሰበ እናንተም ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቆም ብላችሁ አስቡበት ብለናቸዋል፡፡ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ቅድሚያ ስላልተሰጣቸው ስብሰባውን ረግጠን ለመውጣት ተገደናል” ብለዋል፡፡

ዘግይቶ በደረሰን መረጃ የኢትዮጵያ ማህረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ተግልጾአል፡፡

በትናንትናው ዕለት 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ከምርጫ ከጊዜ ሰሌዳው በፊት በውይይት መፈታት አለባቸው ብለው ያመኑባቸውን ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ (ምንጭ፤ ነገረ ኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment