• ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምህዳር እንዲኖር እንስራ የሚለው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም
ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥቅምት 7/2007 ዓ.ም በ2007 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን 5ኛው አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ከአገራዊ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት በጊዮን ሆቴል የጠራውን ስብሰባ ረግጦ ወጣ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባውን ረግጦ የወጣው የምርጫ ቦርድ ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን መስራት ያለበትን ነገሮች ሳይሰራና ፓርቲዎችም ያሉባቸውን ችግሮች አቅርበው መወያየት ሳይችሉ ስለ ጊዜ ሰሌዳ ማውራቱ አስፈላጊ አይደለም በሚል መሆኑን ስብሰባውን ለመሳተፍ ሄደው የነበሩት ተወካዮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ስለ ጊዜ ሰሌዳው ከመወያየት በፊት ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር በመስራት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን በ1997 ምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ያሉባቸውን ችግሮች በዝርዝር መወያየታቸው ቢያንስ ቅድመ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማገዙን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከ1997 ምርጫ በኋላ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ችግራቸውን በዝርዝር በመወያየት፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ስለሚያስችሉ ጉዳዮች መነጋገር ባለመቻላቸውና ምርጫ ቦርድም በጉዳዩ በህገ መንግስቱና በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣቱ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደተዘጋም በመግለጽ ምርጫ ቦርድን ወቅሰዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በ2005 የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋና የአካባቢ ማሟያ ምርጫዎች በፊት ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ሳይወጣ አዳማ ላይ ‹‹ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንወያይ›› ብሎ ስብሰባ በጠራበት ወቅት ‹‹መጀመሪያ ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር መወያየት አለብን›› ብለው ጥያቄ ቢያቀርቡም ቦርዱ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ገልጸው በዚህ አመትም ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር እንደሚፈልጉ አሳስበዋል፡፡