Saturday, June 7, 2014

የኢህአዲግ/ህወሃት ቁልፍ ተግባር:- አራት ኪሎን መጠበቅ


የኢህአዲግ/ህወሃት ቁልፍ ተግባር:- አራት ኪሎን መጠበቅ

ልብ ብላችሁ ተመልከቱ:: ኢህአዲግ/ህወሃት ስልጣን ከያዘበት “ግንበት” 1983 ጀምሮ የሚፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያልሙት ቤተ መንግስን ለመጠበቅ ያለሙ ናቸው።  ላፍታ ወደ ኋላ ልመላሳችሁ።  ብዙ ሀገሮች ዋና ከተማቸውን የሚመሰርቱበት ቦታ ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ውጭያዊ እና ሌሎች ስትራቴጅ ጠቀሜታዎች የሚያበረክተውን አንድምታ መሰረት በማድረግ ነው። በተለይ የባህር በር ያላቸውን ሀገሮች ስንመለከት ብዙዎቹ ዋና ከተማቸው የባህር በርን የተንተራሰ ነው።  ኢትዮጵያ ረጅም የባህር በር የነበራት ሀገር ነበረች። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ምስራቅ (ከአማሴን ሰሜን ጫፍ እስከ ጅቡቲ ደቡባዊ ክፍል) ድረስ በቀጭን መስመር የባህር አዋሳኝነቷን ማጣቷ የኢትዮጵያን ካርታ የሚመለከት ባዕድ እንኳን የሚያጤነው ጉዳይ ነው። ይሄ ለምን ሆነ? የቀደሙ መንግስታት እራሳቸውን ከውጭ ወራሪ በህዝብ ለመከለል ይረዳናል ሲሉ ባላቸው ግንዛቤ እንደሆነ አንድ የታሪክ መምህሬ ክፍል ውስጥ ሲናገር አስታውሳለሁ:: ለእኔም ትርጉም ሰጥቶኛል። እናም ቤተ_መንግስትን ለማስከበር በማሰብ ዘላለማዊ የሀገር ማንነት እና ጥቅምን ወደ ጎን በመተው ዋና ከተማን መሃል ሀገር እና ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ቦታ (ኮረብታ) ላይ መመስረት የተለመደ ሆኖ የዘለቀ እውነታ ነው። 



የአሁኑ “መንግስታችን” ደግሞ አላማው ተመሳሳይ፥ ስትራቴጅው ለየት ያለ በማንኛውም ኪሳራ (cost) ቤተ_መንግስትን ብቻ የመጠበቅ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል።  ይህን አባባሌን የሚያስረዱልኝን በጣም ግልጽ መረጃዎች ብቻ ለማሳየት ልሞክር።  የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ጋር :- ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ ጋር ያለው ግንኙነት በሙሉ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አይደለም። ትስስሩ ነፍጥ ያነሱ ተቃዋሚ ሃይሎች ጎረቤት ሀገሮችን እንዳይጠቀሙ በተነደፈ ስውር እና ውስጣዊ ስትራቴጅ ነው። ይህን በተመለከተ መሃሪ ታደለ(ዶ/ር) የተባለ ውስጥ አዋቂ የሆነ ግለሰብ በሪፖርተር ጋዜጣ (አማርኛ እትም) እሁድ ግንቦት 18/2006 በወጣው “ቆይታ” አምዱ ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ መረዳት ይቻላል። ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረግ የድምበር ድርድር ነው።  እስካሁንም እንደታየው ወደፊትም ቢሆን ከየትኛውም ሀገር ጋር የሚነሱ የድምበር ጥያቄዎች የኢትዮጵያ መብት ሲቀር፥ ለይገባኛል ባዮች እየተተወ መቀጠሉ ገሃድ ነው። ታዲያ ከኤርትራ ጋር ስለምን ወደ ጦርነት ተገባ የሚል ካለ መልሴ የኤርትራው ሻዕብያ አራት ኪሎ ድረስ እጁ ስለነበረበት ጦርነቱ አሁንም ዋናውን አላማ 4 ኪሎን የማዳን እርማጃ ነው።  በርግጥም ጦርነቱ 4 ኪሎን እንጅ ድምበሩን/ዛላምበሳን አላዳነም። ብዙ ጊዜ ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት ሉዓላዊነትን እና ክብርን በሚነካ መልኩ የሚፈጸም ነው። 

ሌላው አክንዮ ደግሞ መከላከያ ሰራዊት ግምባታ ነው። በምግብ እራሷን ያልቻለች ሀገር የትዬለሌ ሰራዊት እና አጠቃላይ መከላከያ ግምባታ አሁንም አራት ኪሎን ከመጠበቅ ያለፈ ፋይዳ የለውም።  ምናልባት ኢንቨስትመንት ነው ሊባል ከተቻለ አላውቅም።  ምክንያቱም የሰራዊት አባላቱን ለተባበሩት መንግስታት እና ለአፍሪካ ህብረት በመሸጥ አንደኛ ስለሆንን። እንዲሁም በዚህ ምክንያት ምዕራባውያን እርዳታ ስለሚለግሱ በእግረ መንገዳቸውም የአራት ኪሎን ጥበቃ ስለሚጠነክሩ።  ከዚህ ጋር ተያይዞ መከላከያ ሰራዊቱ ከህዝብ ጎን ሳይሆን ከአራት ኪሎ ሰዎች ጋር መቆሙን በተደጋጋሚ አሳይቷል።  በታደሉት ሀገራት ባለፈው የአረብ አብዮት እንዳየነው በአመጽ ሰዓት እንኳ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠብቀው ህዝብን፣ ህጻናትን እና አሮጊቶችን ነው። 

ሌላም ላንሳ። ልማት ተሰራ ተብሎ የሚነገረው ልማቱ የህዝቡን ችግር ለመቅረፍ ካለው ጠቀሜታ አንጻር ሳይሆን ልማት ያመጣሁ እኔ ነኝ እናም ለመጭዎቹ ሽህ አመታት መንገስ አለብኝ ከሚል ያፈጠጠ ያገጠጠ መልዕክት ጋር ነው። ምናልባት በታደሉት ሀገራት እንደዚህ አይነት ልፈፋ የሚደረገው በምርጫ ዋዜማ ነው። በእኛው ጉድ ግን ነግቶ እስኪመሽ፣ መሽቶ እስኪነጋ (24/7 እንደሚሉት) አንድ እና አንድ ነው።  አሁን አሁን ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚነደፉት አራት ኪሎ ቅርሴ ሊሆን ይገባል ከሚል መንፈስ ነው:: የጸረ-ሙስና ትግል ተብየውም ቢሆን የተጀመረውም ሆነ እየተተገበረ ያለው አንዳንድ ባለስልጣናት ወደ አራት ኪሎ ወምበር ቀና ብለው ሲመለከቱ መኮርኮሚያ ነው።  

ስዬ አብርሃን እና ከዚያ በኋላ በሙስና ስም የታሰሩ ባለስልጣናትን መመልከቱ በቂ ነው። ብዙ እህት እና ወንድሞቻችንን ለእስር እና ስቃይ የዳረገው የአባይ ግድብም ቢሆን የተጀመረው ርዕዮት አለሙ በትክክል እንደጻፈችው ኢትዮጵያ ውስጥ የአረብ አብዮት እንዳይነሳ ብሎም ወደ አራት ኪሎ እንዳይዘልቅ ነው።  ኧረ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል። የህገ-መንግስቱን መንግስታዊ አወቃቀርም ሞያዊ በሆነ መንገድ ብትመለከቱ አራት ኪሎን ለማስጠበቅ የተቀመመ የወረቀት እና የቀለም ጥምረት ነው።  የ “ፌደራሊዝም” አወቃቀሩስ ቢሆን። ምንም እንኳ የመንግስቱ ተግባራዊ ማንነት አሃዳዊ ቢሆንም ስያሜው፣ “ፌደራሊዝም” አራት ኪሎ ን ለማስከበር የታለመ ነው።

እዚህ ላይ አንባቢ ሆይ ነገደ ጎበዜ ወይም ምናሴ ሃይሌ የጻፉትን የህገመንግስት ትንታኔ መጽሃፍ ቢያነቡ ቁልጭ ብሎ ይታይዎታል።  ከላይ ከተጠቀሱት ሁሉ አንድስ እንኳን በዋናነት ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ የታለመ የለም።  ይሄው ድግስ ባጋጣሚ ግን ወደፊት ካራመዳት የፈጣሪ ስራ ነው። በጉዳዩ ላይ ብዙ ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንም የመጨረሻ አንድ ነገር ብየ ላብቃ። ግብጽ ኩታ ገጠም ሀገር ሆና ቢሆን ኖሮ ኢህአዲግ/ህወሃት ሰሞኑን ያሳየውን የቃላት ውርወራም ሆነ ግድቡንም አይጀምሩም ነበር ባይ ነኝ። ምክንያቱም ጦር ያነሱ ተቃዋሚዎች ግብጽን እንደ መንደርደሪያ ይጠቀሙባት እና አራት ኪሎ ላይ ስጋትን ይፈጥራል ብለን ስለምናስብ ነው። 

No comments:

Post a Comment