Sunday, May 18, 2014

ሜይ 17ን ብመኘው?


ሜይ 17ን ብመኘው?

የኖርወይ ሕዝብ ሕገመንግሥታቸውን ያወጁት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1814 ማለትም የዛሬ 200 ዓመት ነበር።

አንድ መቶ አስራ ሁለት የአገሪቱ ታላላቅ ሰዎች በሀገር ፍቅር ቀናኢ ስሜት በመነሣሣት ሕገ መንግስቱን በዘመኑ ነባራዊ ሐቅ ላይ በመመሥረት እንዲሁም ጊዜ በፈቀደው ጥበብና ቋንቋ በአስደናቂ ክህሎት 
አረቀቁት ።
ታዲያ ይህ ሕገ መንግስት በወቅቱ የነበሩትን ባለስልጣናት የሚያገለግል ሳይሆን የሐገሪቱን ሕዝብን ማዕከል ያደረገና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዲሞክራሴያዊ ሕጎች ጋራ የተጣጣመ ረቂቅ ነበር ።

ይህ ሕገ መንግሥት በዚያን ጊዜ ተቀባይነትን አግኝቶ በከፍተኛ አድናቆት ቢፀድቅም ቅሉ፤እንደ ማንኛውም ሰው ሰራሽ ሕገመንግሥት ሁሉ፥ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ የሆኑ መሻሻሎች ተደርገውበታል። 
ለዚህ እውነታ ዋቤ መጥቀስ ካስፈለገም በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ እምብዛም ትኩረት ያልተሰጣቸው የሴቶችና የህፃናት መብት መከበርን የመሳሰሉት በጎላ ሁኔታ ተካተውበት ሕዝባዊነቱ የበለጠ ለዓለም ሁሉ ጎልቶ እንዲያንጸባርቅ ተደርጎአል። 
ታዲያ ይህ ሁሉ መሻሻልና ለውጥ የሆነው በሕዝብ ፈቃድ ብቻ እንጂ በማንም ግላዊ ውሳኔ አይደአለም።

    

ከዚህ የተነሣ ይህንን ቀን ለሐገራቸው ያላቸውን ፍቅር፥ ለባንዲራቸው ያላቸውን ክብርና ነጻ ሕዝብ መሆናችቸውን የሚያውጁበት የድል ቀናቸው አድርገው በደመቀና ባሸበረቀ ሁኔታ በሰላምና በነጻነት ያከብሩታል። 

ዓመቱ ተጠቅልሎ ያ አንጋፋ 17ኛው ‘መይ’ እስኪመጣ ድረስ ቀኑን በናፍቆትና በጉጉት ይጠብቁታል። ለዚህ ቀን የሚሰጡት ክብር ራሳቸውን ማስደሰቱ ብቻ ሳይሆን በአገራቸው የሚኖሩትን የውጭ ዜጎች የሚስብና የሚያስደምም፤ ከሀገሪቱ ውጪ ያለውንም ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ቀልብ የሚማርክ ነው። ባጠቃላይ፥ ዕለቱ እጅግ ታላቅና የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ ቀን ነው።

መቸም “ዞሮ ዞሮ ከቤት፥ ኖሮ ኖሮ ከመሬት’’ ነውና፥ ወደ እኛው አገር መለስ ብለን ስንቃኝ ደግሞ የምናይአው ምስል የተገላቢጣሹ ነው ። 

አይረቀቅ የለም ሕገ መንግስቱ በወረቀት ላይ ብቻ ለይስሙላ የተቀመጠ እንጂ የሕዝብን መብትና ነጻነት በሚያስከብር መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ በተግባር አይተረጎምም። 

አሁን ያለው አምባገነኑ የወያኔ መንግሥት ለራሱ እኩይ ጥቅም እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልቆመ ስለተረዳው ለሕገ መንግስቱ የመገዛትም ሆነ የማክበርና የመፈፀም አዝማሚያ ጨርሶ አይታይበትም።

ይባስ ብሎ እያደር ከመሻሻል ፋንታ የሕዝብን መብት የሚረግጥና የሚያንቋሽሽ ሕግና ደንብ   በማውጣት ሕዝቡ ያለፍላጎቱ በግድ እንዲቀበለው በመሣሪያ ኃይል እያስጨነቀና እየጨቆነ እየገደለም ይገኛል። 

ታዲያ መንግሥት ራሱ ለሕዝብ መብትና ነጻነት የሚቆም ሥርዓት ሳያበጅና ሳያከብር ‘ተቀበል’ የሚለው ይህ “ሕገ መንግስት” አክብሮትና ልዕልና ሊሰጠው የሚችለው በምን መልኩ ነው? 

አቤት!መሪዎቻችን የሕዝብን ነፃነትና መብት የሚያከብሩበት ለሕዝብ የሚቆም ሕገመንግሥት የሚያወጡበትና አክብረው የሚያከብሩበት ቀን የሚመጣው ከቶ መቼ ይሆን? 

በዛሬው ዓምዴ በዋናነት ያወሳሁት የኖርወይ የነፃነት ቀንና ታሪክ እያስጎመዠኝ፤ይህ የከበረ ዕድል በአገሬና ለአገሬ ሕዝብ እውን ሆኖ ለማየት እናፍቃለሁ። 

ከዚህ የተነሣ የኖርወይን “ሰትነ ማይ” 17ኛውን መይ ብመኘው የቅንዓት ያስመስልብኝ ይሆ?? ለ2015ኛው አዲስ የነጻነት ቀን በቸር ያገናኘን በማለት ከወዲሁ ልሰናበታችሁ።   
                    
                                ምናሴ መስፍን
                                



No comments:

Post a Comment