Sunday, June 29, 2014

መዝገቦቹ መልሰው ተቀራረቡ የእምነት ክህደት ቃል በኃይል አስፈርመዋቸዋል

መዝገቦቹ መልሰው ተቀራረቡ
የእምነት ክህደት ቃል በኃይል አስፈርመዋቸዋል
ጽዮን ግርማ
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በስድስቱ ጦማሪያንና በሦስቱን ጋዜጠኞች ላይ የፌደራል ፖሊስ የተለያየ ምክንያት እየሰጠ ቀጠሮ የሚያራዝመውን ሁለት መዝገብ አንዴ ሲያቀራርበው መልሶ ደግሞ ሲያራርቀው ቆይቶ አሁን ደግሞ መዝገቦቹን መልሶ አቀራርቧቸዋል፡፡እስረኞቹ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ኹኔታ ፖሊስ ያረቀቀውን የእምነት ክህድት ቃል ተገደው እንዲፈርሙ አድርጓቸዋል፡፡
የሦስቱ ብሎገሮች አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ቀጠሮ ለዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ የሚል የነበረ ሲኾን ከጠዋት ጀምሮ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ቤተሰብ፣ጓደኞቻቸው፣ጋዜጠኞች፣ዲፕሎማቶችና የወጣቶች ደጋፊዎች በአጠቃላይ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ ሰው ከችሎት ውስጥ የሚሰማውን አዲስ ነገር ለመጠበቅ በግቢው ውስጥ ቆመው ነበር፡፡ ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ የእስረኞቹ ጠበቃ አቶ አመኃ መኮንን ተጠርተው የመዝግብ ቤት ጸሐፊዋ ስለሌለች ችሎቱ ለከሰዓት በኋላ እንደተዛወረ ይነገራቸዋል፡፡ እርሳቸውም ችሎቱን ለመከታተል ለቆመው ሰው መልዕክቱን ያስተላልፋሉ፡፡ ጥቂት ሰዎችም ይህን መልዕክት ሰምተው ግቢውን ለቀው ይወጣሉ ብዙኃኑ ግን እዛው እንደቆሙ መጨረሻውን ለማየት መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡


ሠላሳ ደቂቃ ያህል እንደተቆጠረ የእስረኞቹ መምጣት በጉምጉምታ መወራት ጀመረ፡፡ሁሉም ሰው ወደ ጓሮው በር ዐይኑን ተክሎ ቀረ፡፡ አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ ማኅሌት ፋንታሁ ከካቴና ውጪ ኾና እንደተለመደው በከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ ታጅበው ወደ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ግቢው ፊታቸው ላይ የጥንካሬ መንፈስ የነበረ ሲኾን ተሰበሰበውም ሕዝብ በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው፡፡በዚህ መካከል እስረኞቹን አጅበው የመጡት ፖሊሶች ወደተሰበሰበው ሰው ዘለው በመግባት ፎቶ ስታነሳ ነበር ያሏትን ምኞት መኮንንን (የሰማያዊው ፓርቲ አባል) የተባለች ወጣት የያዘችውን ስልክ ቀምተው እየጎተቱ ወሰዷት፡፡ፖሊሶች በወጣቷ ላይ የሚፈጽሙት ማንገላት ያስቆጣው ዮናታን ተስፋዬ የተባለ ሌላ ወጣት ድርጊቱን በማውገዝ ለመገላገል ሲጠጋ እርሱንም ጨምረው ወስደውታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ይህን ችሎት ማየት ከጀመረ ወዲህ እስረኞቹን አጅበው የሚመጡት ፖሊሶች ቀጠሮ ባለ ቀን ሁሉ ችሎት ለመከታተል የሚመጣውን ሰው ሲያንገላቱ፣ሲሰድቡና ሲዘልፉ ልክ እንደ መብታቸው የሚቆጥሩት ሲኾን እዛ ግቢው ውስጥ የተገኘው ሰው ችሎት ውስጥ ገብቶ በሚገባ መቀመጫ ቦታ ተሰጥቶት ችሎት የመከታተል መብት እንዳለው ቅንጣት ታክል አስበውት የሚያውቁ አይመስል፡፡ እንዲኹም ከችሎቱ ውጪ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥም ቢኾን ‹‹ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው›› የሚል ማስጠንቀቂያ እስካልተለጠፈ ድረስ ከሁለት ሰው በላይ የኾነ ማንም ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ላይ ፎቶ የማንሳት ሙሉ መብት እንዳለ የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ በአጠቃላይ በዛ ቦታ ላይ ከእነርሱ ውጪ ሌላ ሰው የመቆም መብት ጭምር እንደሌለው ጠንቅቀው ስሚያውቁ ወደ ተሰበሰበው ሰው ተመልሰው፤‹‹ሁላችሁም ግቢውን ለቃችሁ ውጡ›› ሲሉ ትእዛዝ ሰጡ፡፡
ከፊት ለፊት ቆመው የነበሩት ሰዎች ከግቢው ላለመውጣት እንቢተኝነታቸውን አሳዩ፡፡በተለይ በእስር ላይ የምትገኛው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እህት እስከዳር ዓለሙ፣አባቷ አቶ ዓለሙ እና ሌሎች ወጣቶች አንድ ላይ ኾነው ግቢ ውስጥ መቆም መብት እንዳላቸው በመግለጽ ለመውጣት ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀሩ፡፡ የፖሊሶቹ ማስፈራሪያና ዘለፋ ግን ቀጠለ ሕዝቡ ግቢውን ለቆ የማይወጣ ከኾነ አድማ በታኝ ፖሊስ እንደሚጠሩ ጭምር በመግለጽ ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ፎቶ ማንሳት የተከለከለ እንደኾነ እና እንኳን ሰውን መሬቱንም ጭምር ማንሳት እንደማይቻል በማስፈራራት ጭምር በመግለጽ ሰውን ከግቢው ውስጥ ገፍተው ወደ ውች አስወጡት፡፡
ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2006 ዓ.ም ውሎ በነበረውና ከዚያም ቀጥሎ በነበረው ችሎት ላይ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወከለው ቤተሰብ አባል ወደ ችሎት እዲገባለት ተደርጎ የነበረ ሲኾን አሁን ግን ይህም መብት ተከልክሎ ችሎት ውስጥ በእስረኞቹ በኩል ከጠበቃቸው ከአቶ አመሐ መኮንን በስተቀር ማንም ችሎት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ችሎት ከገቡም በኋላ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጠማሪ ሃያ ስምንት ቀን እንዲፈቀድለት የጠየቀ ሲኾን ፍርድ ቤቱ፤‹‹ከዚህ በኋላ የሚሰጣችሁ ሃያ ስምንት ቀን የለም ዐሥራ አራት ቀን ይበቃችኋል፡፡ ችሎቱም ከዚህ በኋላ እሁድ ስለማይሰየም ቀኑ አንድ ቀን ተቀይሮ ሰኞ ሐምሎ 7 ቀን 2006 ዓ.ም›› ሲል ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የጊዜ ቀጠሮው መዝገብ ሲከፈት የአቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና የማኅሌት ፋንታሁንን ጉዳይ የያዘው መዝገብ ከሌሎቹ ከስድስቱ አስረኞች ጋራ በአንድ ቀን ይለያይ የነበረ ሲኾን በመካከሉ አንዲት ዳኛ የሃያ ስምንት ቀን ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ጉዳዩ በዐሥራ አምስት ቀን ተለያይቶ እንደነበር ይታወሳል አሁን ደግሞ መዝገቦቹ መልሰው ተቀራርበዋል፡፡ የስድስቱ ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን ይታያል የሦስቱ ደግሞ ሰኞ ሐምሌ ሰባት ቀን፡፡
በዛሬው ቀጠሮ በፍቃዱ ኃይሉ ያላመነበትን የእምነት ክህደት በኃይል እንዲፈርም መገደዱን ተናግሯል፡፡ እንደምንጮች ገለጻ ከኾነ አብዛኞቹን እስረኞች በከፍተኛ ጫናና በድብደባ በመርማሪ ፖሊሶች የተረቀቀውንና በእነርሱ ሐሳብ የተዘጋጀ የእምነት ክህደት ቃል ላይ ‹‹የሰጠሁት ቃል የኔ ነው ጥፋተኛ ነኝ›› ብለው እንዲፈርሙ ተደርጓል፡፡
የፍርድ ቤቱ መዝገቡን ማጠጋጋትና የእምነት ክህደት ቃሉ ፊርማ እስረኞቹን ለመክሰስ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ማሳያዎች በሚል በሕግ ባለሞያዎች ተገምቷል፡፡
(ፎቶዎቹ ከታምሩ ጽጌ ገጽ ላይ የተገኙ ናቸው)
Tsion Girma's photo.
Tsion Girma's photo.
Tsion Girma's photo.

No comments:

Post a Comment