Thursday, December 5, 2013

ስሟ በውቅያኖስ ተሰይሞላት እንዳልነበር


ስሟ በውቅያኖስ ተሰይሞላት እንዳልነበር

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ታሪክ ባለቤት ናት ሲባል አንዳንድ ኢትዮጵያዊ እንዲሁ ሀገራችንን ስለምንወድ ብቻ የሚወራ ይመስለው ይሆናል። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም፡፡ በእውነትም አገራችን የሚያኮራ ታሪክና ገድል ያላት ጥንታዊት አገር ነች፡፡
ባንድ ወቅት የደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ኢትዮፒክ ውቅያኖስ ይባል እንደነበር ስንቶቻችን እናውቅ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይሄ እድሜ ጠገብ ውቅያኖስ በእርግጥም የደቡቡ ክፍል “ኢትዮፒክ ውቅያኖስ” ይባል እንደነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ያሰምሩበታል፡፡ ይህ ደቡባዊ ያትላንቲክ ውቅያኖስ ክፍል እስከ አስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ባገራችን ስም ስያሜ ይጠራ እንደነበርም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ይህን ለምሳሌ ያህል በመጥቀስ ያንድ ወቅት ታላቅ ሕዝብና አገር ባለቤቶች እንደነበርን ለማሳየት ሞከርኩ እንጂ፤ የኢትዮጵያን ታላቅነት በዝርዝር ማሳየት ካስፈለገ ብዙ ሌሎች ምሳሌዎችን መጨመር ይቻላል፡፡ ኢየሩሳሌም ያሉትን ገዳማት ጨምሮ ባገራችን ያሉ ብዙ ጥንታዊ ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ስፍራዎች እንቁ ጌጦቻችንና መታወቂያችን ናቸው፡፡  በወርቃማው የፈርኦን ዘመን እኩል ሥልጣኔ የነበረን ታላቅ ሕዝቦች እንደ ነበርን፤ ያክሱም ሐውልት ቋሚ ሕያው ምስክር ነው፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያት ክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተ መንግስቶች፣ የሶፍ ኡመር ዋሻና የመሳሰሉት ድንቅ የታሪክና የተፈጥሮ ቅርሶቻችን መኩሪያዎቻችን ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን የአፍሪካ የነፃነት ምልክትና አርማ እንዳልነበረች ሁሉ፤ ዛሬ በኛ ትውልድ ዘመን፤ ፔትሮ ዶላር ያሰከራቸው አረቦች መቀለጃና መጫወቻ ሆናለች፡፡ ለዚህ ደሞ ማረጋገጫው በቅርቡ በሳውዲ አረቢያ መንግስትና ወሮበሎች አማካኝነት በዜጎቻችን ላይ የደርሰው ውርደትና ስቃይ ነው፡፡ ዜጎቻችን ተገለዋል፣ ታስረዋል፣ ተቀጥቅጠዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ተደፍረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ በደልና ውርደት በታሪኳ ውስጥ አይታይም ሰምታም አታውቅም፡፡

የወያኔ ሹማምንት ከድሃ ሕዝባችን ላይ እየዘረፉ በውጭ ባንኮች ውስጥ ያከማቹትን ገንዘብ የትየለሌ ሆኗል፡፡ ለዚህ ምሳሌው የነአዜብ ጎላና የመሳሰሉት የውጭ ባንክ ገንዘብ ክምችት ነው፡፡ ድሮ በነቢልጌት የገንዘብ መጠን እንደመም እንዳልነበረ ሁሉ፤ ዛሬ ደሞ በራሳችን ብር ጌቶች በነአዜብ ቱጃርነት መደመም ጀምረናል፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ ዛሬ መሬታችን ለውጭ ባለሀብቶች እየተቸበቸበ፣ ሕዝባችንን ጦም አዳሪ ያደረገ የወያኔ አስከፊ ስርአት አለ፡፡  ባለመሬቱ ያገር ሰው እይተፈናቅል እነካራቹሪና አረብ ቱጃሮች እርስቱን የመበዝበዣ መሳሪያ አድርገውታል፡፡ የሳውዲ እስታር የተባለው ኩባንያ አገራችን ውስጥ ትልቅ የርሻ ቦታ ይዞ የኛን ዜጎች ደሞ የገላል፣ ያስራል፣ ይዘርፋል፣ ይደፍራል….

የወገኖቻችንን ጉዳት የተመለከተው የአዲስ አበባ ህዝብ የሳውዲን መንግስት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በወጣበት ጊዜ፤ መንግስት ተብዬው ሰልፉን አግዶ ካረቦቹ ጎን ተሰለፈ፡፡ ይሄኔ ነው ባገር ቤትም በውጪም ያለነው ሁሉ፣ ለዚህ ውግናችን ማን ይድረስለት ማን ያስጥለው ከጅቦቹ እያልን ጩኸት የጀመርነው፡፡  

 ኢትዮጵያ የታሪክ ባለሀብት ብቻ አይደለችም፡፡ አሁንም ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብናየው
እንዃን የብዙ ሙህራን ባለቤት ናት ። የሀገራችን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁኔታ አስገድዶቸው
አብዛኞቹ ከአገራቸው ተሰደው ባእድ አገርን እያገለገሉ የሚኖሩ ይገኛሉ።  የአገራቸው
ጥፋትና ጉዳት ውስጣቸውን እየበላ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሚመለከተው ክፍል ያስታዉቃሉ፣ የጮሃሉ፣ ይታገላሉ… ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ፍቅር ናፍቆት ውስጣቸው እየተቃጠለ የሚሰቃ ብዙዎች ናቸው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በላይ ውርደትን ለመቀበል ህሊናችንን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ በኳስ ላይያሳየነውን አንድነት ግማሹን እንኳን አምባገነኖችን ለማስወገድ ፋይዳ ብንጠቀምበት፤ የደስታችንን ምንጭ በራሳችንን እጅ እንደጨበጥን ይቆጠረ ነበር፡፡ ስለዚህ ህብረታችንን
ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ማጠንከር ይኖርብናል፡፡የዚህችን ታሪካዊ ሀገር ክብር የማስመለስ

ብሔራዊ ግዴታ እሁላችንም ዘንድ አለና መጠንከር አለብን ።

                                                 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር


ከምናሴ መስፍን
ከኖሪቤ ኦስሎ

No comments:

Post a Comment