Sunday, February 15, 2015

የምርጫ ሂደቱ በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ችግር እየደረሰበት ነው! ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ሰማያዊ ፓርቲ በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ የሚያበቃውን ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ነፃና ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመሆን ነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ የሚል መርሀ ግብር በማዘጋጀት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ከተደረጉት እንቅስቃሴዎችም በተጨማሪ ምርጫ ቦርድና የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማት በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩና የፖለቲካ ምህዳሩም ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ፍትኃዊ እሰኪሆን ድረስ የነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ ዘመቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች እጩ ተወዳዳሪዎችን ለማስመዝገብ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የምርጫ አካባቢዎች በዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን ላይ በገዢው ፓርቲ አባላትና በምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ከፍተኛ እንግልትና እንቅፋት የተፈጠሩባቸው ሲሆን ለአብነት ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡



1. በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እጩ ተመዝጋቢዎች የተወለዱበት ዞን መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን ምስክር አምጡ በማለት እንዳይመዘገቡ ተደርገዋል፡፡

2. በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች በሙሉ የምርጫ አስፈፃሚዎች ፅ/ቤቶችን ዘግተው በመጥፋታቸው ምክንያት መመዝገብ በተደጋጋሚ የሄዱ እጩ ተመዝጋቢዎች ሳይመዘገቡ ጊዜው እንዲያልፍባቸው ተደርገዋል፡፡


3. በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በምርጫ አዋጁ መሰረት 1 እጩ ተመዝጋቢ ቅሬታ እስካልወቀረበበት ድረስ የመመዝገብ መብት እንዳለው እየታወቀ ነገር ግን የምርጫ ፅ/ቤት ሃላፊዎች የሌላ ፓርቲ አባላት ናችሁ ከፓርቲያችሁ መልቀቂያ ካላመጣችሁ በሚል ምክንያት በርካታ የፓርቲያችን እጩዎች ሳይመዘግቡ መልሰዋል፡፡

4. በሰሜን ሸዋ፤ በሲዳማ፤ ጋምቤላ፤ ጋሞጎፋ፤ በምስራቅና በምእራብ ጎጃም አካባቢዎች እጩ ተመዝጋቢዎችን በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በማስፈራራት፤በአካባቢ ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች በማሰወገዝ ራሳቸውን ከእጩነት እንዲያገሉ ተፅእኖና ግፊት ተደርጎባቸዋል፡፡

5. በደቡብ ክልል የገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች እጩዎችን ሊያስመዘግቡ የሄዱ ተወካዮችን በማሰርና በእጃቸው የሚገኘውን የእጩዎች ማስመዝገቢያ ደብዳቤዎች በመንጠቅ የምዝገባ ጊዜው እንዲያልፍባቸው ተደርጓል፡፡

6. በሰሜን ጎንደር፤ በሲዳማና በከምባታ ዞኖች የፓርቲው እጩ አባላት በታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡

7. በደቡብ ኦሞ ዞን የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተው የተመዘገቡ የፓርቲያችን እጩዎች በ05/06/07(ማለትም የምዝገባው ጊዜ ካለቀ በኋላ)በደ/ቁ-አ573/ፖአ/ጠ470 ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት በተፃፈ ደብዳቤ 18 የክልል ምክር ቤትና 6የተወካዮች ምክር ቤት በድምሩ24 እጩዎች እንዲሰረዙ ተደርጓል፡፡

እነዚህና ሌሎችም ጥፋቶች የሚፈፀሙት ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሀዊ በሆነ የምርጫ ሜዳ እንዳይሳተፉ በማድረግ የአምባገነናዊን መንግስት የስልጣን ዘመን ለማስረዘም በዕቅድ የተፈፀሙ ድርጊቶች መሆናቸውን ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም በማለፍ ፓርቲያችን ለመንግስትነት የሚያበቃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እጩ ተወዳዳሪዎችን በመላ የሐገራችን ክፍሎች አስመዝግቧል፡፡

ገዥው ፓርቲ በስልጣን ለመቆየት እንደ ስልት የያዘው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲያጡ በብቸኝነት በተቆጣጠራቸው የመንግስት የመገናኛ ዘዴዎች ሥም ማጉደፍና ሕዝብም በምርጫው እምነት እንዲያጣ በማድረግ ከራሱ ደጋፊዎች ውጭ ሌሎች ዜጎች በንቃት እንዳይሳተፉ ማድረግን ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ በገዥው ፓርቲ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሳይዘናጋ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ በንቃት እንዲሳተፍና የመራጭነት ካርዱንም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ከህገ ወጥ አሰራር እንዲቆጠቡ ፓርቲያችን በአፅንኦት እያሳሰበ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመሰረተውን ትብብር በማጠናከርና በምርጫውም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ውጤት ለማምጣት ሰማያዊ ፓርቲ ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን ያሳውቃል፡፡

የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም

አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment