ገብረመድህን አርኣያ
ፐርዝ፤ አውስትራሊያ
ይህ ጽሑፍ ትኩረት የሚሰጠው በትግል በረሃ በነበርንበት ወቅት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት.) በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖቶች ላይ ሲከተል የነበረውን አቋሙን ተቀብሮ ከነበረበት ጉድጓድ አውጥቼ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እነማን ናቸው የሚለውን ታሪካቸውን እና የተፈጸመውን ጸረ-እምነት ግፍ በአጭሩ ለማሳወቅ ነው።
ህ.ወ.ሓ.ት. ገና ሲፈጠርና ተ.ሓ.ህ.ት. ተብሎ እንደተመሰረተ ሙልጭ ያለ ጸረ-ዲሞክራሲ ድርጅት ነው። በጸረ-ኢትዮጵያነትና በጸረ- ሕዝብነት የተሰማራ ቅጥረኛ ድርጅት መሆኑን ብዙ ጊዜ በጽሑፍና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህዝብ ተናግሬአለሁ። የአሁኑ ጽሑፌ ህ.ወ.ሓ.ት. በሃይማኖት ላይ ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ ገና ከመጀመሪያ ትግሉ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የነበረውን ጸረ- ሃይማኖት ተግባራቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ አውቆታል። እኔ ደግሞ የራሴን ልበል።
በ1969 መጀመሪያ ጀምሮ “ወይን” በሚለው የድርጅቱ ልሳን መጽሔት ላይ በተደጋጋሚ “የክርስትና ሃይማኖትና አማራው” በሚል ርእስ ተጽፎ የሚወጣው ጽሑፍ፣ “የክርስትና ሃይማኖት የአማራው ዋና መሳሪያና የግዛቱን ህልውና ማስጠበቂያ ነው፣ በመሆኑም የትግላችን ጠላት አማራውና መሳሪያው የተዋህዶ ክርስትና ስለሆኑ አብረው እንዲጠፉ ማድረግ አለብን” እያለ ያትት ነበር። ይህንን መጽሔት በሰፊው ለታጋዩና ለአባላቱ በማሰራጨት ሰፊ ቅስቀሳ አካሂዶበታል። በነሐሴ 1969 “ወይን” መጽሔት አማርኛ ቋንቋም አብሮ መጥፋት እንዳለበት ሃተታ ይዞ ወጥቷል።